የአሰልጣኞች አስተያየት | ወልቂጤ ከተማ 1-1 አዳማ ከተማ

\”አማካዮቻችን በጉዳት ወጥተውብናል ፤ አጥቂዎቻችንም በጉዳት ወጥተዋል። በዚህ መሃል ይሄን ውጤት በማግኘታችን በእውነት እግዚአብሔር የተመሰገነ ይሁን\” አሰልጣኝ ገብረክርስቶስ ቢራራ

\”ለማንም ብለን አይደለም የተጫወትነው እኛን የቀጠረን አዳማ ነው። የአዳማ ሕዝብ ያየናል። እግርኳስ ሁሌም እንደዚህ ፍትሃዊ ሲሆን ጥሩ ነው\” አሰልጣኝ ይታገሱ እንዳለ

ወልቂጤ ከተማ ከአዳማ ከተማ ጋር 1ለ1 በመለያየት በፕሪምየር ሊጉ መቆየቱን ካረጋገጠ በኋላ የሁለቱም ቡድኖች አሰልጣኞች ለሶከር ኢትዮጵያ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

አሰልጣኝ ገብረክርስቶስ ቢራራ – ወልቂጤ ከተማ

ስለ ጨዋታው…

በጣም ከባድ ጨዋታ ነው። ምክንያቱም ተጫዋቾቼ ውጥረት ላይ ስለነበሩ በነበረን ብቃትም አልተጫወትንም። በየጨዋታው ጥንቃቄን ይመርጣሉ እና እንደፈለግነው አልነበረም።

\"\"

በወራጅ ቀጠናው ስለነበረው ውጥረት…

በጣም ከባድ ነው። የእግርኳስ አሰልጣኝ ስትሆን ብዙ ነገር ነው የምታየው። ለእንደኛ ዓይነት በብዙ ችግር ውስጥ ያለ ቡድን ደግሞ በብዙ ነገር ነው የሚቸገረው። አማካዮቻችን በጉዳት ወጥተውብናል ፤ አጥቂዎቻችንም በጉዳት ወጥተዋል። በዚህ መሃል ይሄን ውጤት በማግኘታችን በእውነት እግዚአብሔር የተመሰገነ ይሁን።

በወልቂጤ በኩል ወደፊት ቢሻሻል ስለሚሉት ነገር….

እኔ ማኅበረሰቡን ያማከለ ቡድን ይሠራሉ ብዬ አስባለሁ። ከተነጋገርንባቸው ጉዳዮች ውስጥ አንዱ ትልቁ ነገር ሁሉን አቀፍ ለማድረግ ተነስቷል። የዞኑ አስተዳደርም ሆነ የከተማው ከንቲባ ተገኝተዋል ፤ በቀጣይ በቀጣይ ዓመት እነዚህ ችግሮች እንዳይኖሩ ለማስተካከል ቃል ገብተዋል።

አሰልጣኝ ይታገሡ እንዳለ – አዳማ ከተማ

ስለ ጨዋታው…

በመጀመሪያ ግብ አስቆጥረዋል ከዛ በኋላ በጣም አስጨናቂ ጨዋታ ነበር ፤ የአቅማችንን አድርገናል።

\"\"

ስለ ወሳኞቹ ጨዋታዎች…

ሁሌ እንደምለው ኳስ እንደዚህ መሆን አለበት ብዬ አስባለሁ። ሁሉም ዕድሉን በራሱ ነው የሚወስነው እና እኛ ይሄ ጨዋታ ያስፈልገናል። ለማንም ብለን አይደለም የተጫወትነው እኛን የቀጠረን አዳማ ነው። የአዳማ ሕዝብ ያየናል። እግርኳስ ሁሌም እንደዚህ ፍትሃዊ ሲሆን ጥሩ ነው። እነሱ በራሳቸው ዕድል ነው የሚወስኑት እኛም ለራሳችን ብለን ነው የተጫወትነው። ይህንን ጨዋታ ብናሸንፍ 4ኛ ያስወጣን ነበር እና የቻልነውን ሁሉ አድርገናል።

በወጣቶች ስለተገነባው ቡድናቸው…

ሁሌ የምለው ወጣቶችን ሰዓት መግደያ ወይም ደሞ ካለቀ በኋላ ሳይሆን የማስገባቸው ውጤት እንዲያመጡልኝ ነው። ይህ ደግሞ ዓመቱን አዋጥቶኛል ብዬ አስባለሁ። በሚቀጥለው ዓመት እነዚህ ልምድ ያገኛሉና የተሻለ ቡድን ይዘን እንመጣለን ብዬ አስባለሁ።