ሪፖርት | ወልቂጤ ከተማ በሊጉ መቆየቱን አረጋግጧል

ውጥረቶች በተበራከቱበት ጨዋታ ወልቂጤ ከተማ ከአዳማ ከተማ ጋር 1-1 በሆነ የአቻ ውጤት በመለያየቱ በፕሪምየር ሊጉ መክረሙን አረጋግጧል።

ወልቂጤ ከተማ ከወላይታ ድቻ ጋር ነጥብ ከተጋራበት ጨዋታ የሦስት ተጫዋቾችን ቅያሪ አድርጓል። ፍፁም ግርማ ፣ ቡዙአየው ሰይፉ እና የኋላሸት ሠለሞንን በተስፋዬ መላኩ ፣ ተመስገን በጅሮንድ እና አቤል ነጋሽ ሲተኩ ከመድኑ ድላቸው አንፃር አዳማዎች በአራቱ ላይ ቅያሪ ሲያደርጉ አዲሱ ተስፋዬ ፣ መስዑድ መሐመድ ፣ ዮሴፍ ታረቀኝ እና ዳዋ ሆቴሳን በእዮብ ማቲያስ ፣ ቢኒያም አይተን ፣ ኤልያስ ለገሠ እና ቦና ዓሊ ተክተው ጀምረዋል።

ለወልቂጤ ከተማ በእጅጉ አስፈላጊነቱ ላቅ ባለው የሁለቱ ቡድኖች የመጀመሪያው አጋማሽ ጨዋታ ተመጣጣኝ የሜዳ ላይ እንቅስቃሴዎችን ብንመለከትን የመጀመሪያዎቹ የጨዋታው ደቂቃዎች ወልቂጤዎች በተሻለ የሽግግር አጨዋወት መቅረባቸው ብልጫውን እንዲይዙ አድርጓቸው ታይቷል። ከሁለቱ የመስመር ተጫዋቾቻቸው ወደ ውስጥ በሚጣሉ ኳሶች ግብን ለማስቆጠር ጥረት ያደረገው ቡድኑ 14ኛው ደቂቃ ላይ ጨዋታው እንደደረሰ ግብ አስቆጥሯል። ከቀኝ የአዳማ የሜዳ ክፍል አቡበከር ሳኒ ወደ ውስጥ ሲያሻማ የሰይድ ሀብታሙ የቦታ አጠባበቅ ስህተት ታክሎበት አቤል ነጋሽ በግንባር ገጭቶ ከመረብ ያገናኛት ኳስ ነች ወልቂጤን መሪ ማድረግ የቻለችው።

\"\"

ጎልን ካስተናገዱ በኋላ ከራስ ሜዳ በሚጀመር ንክኪ ወደ ተጋጣሚ የሜዳ ክፍል በጥሩ የጨዋታ መንገድ ለመጫወት የዳዱት አዳማ ከተማዎች በቢኒያም እና አድናን አማካኝነት ሙከራዎችን አድርገው ከጥቂት ደቂቃዎች መልስ የአቻ ግባቸውን አግኝተዋል። 26ኛው ደቂቃ ላይ ቦና በመስመር ለቢኒያም ሰጥቶት በመጨረሻም መሬት ለመሬት ተጫዋቹ ሲያሻግር አድናን ረሻድ ሳይቸገር ግብ አድርጓት ጨዋታው ወደ አቻነት ተሸጋግሯል። በቀሩት የጨዋታ ደቂቃዎች ቡድኖቹ ተጨማሪ ግቦችን ለማስቆጠር ጥረት ባይለያቸውም የመጨረሻ ውሳኔዎቻቸው ደካማ መሆን በመቻሉ ጨዋታው በ1ለ1 በሆነ አቻ ውጤት ወደ መልበሻ ክፍል አምርቷል።

ከዕረፍት ጨዋታው ተመልሶ ሲቀጥል ከመጀመሪያው አጋማሽ አንፃር መቀዛቀዞችን የጨዋታው ጅማሬ ቢያሳየንም በሒደት ቡድኖቹ በሙከራ ረገድ ደከም ያሉ ነገር ግን በእንቅስቃሴ እያደጉ የመጡበትን መንገድ አስተውለናል። ጨዋታውን ለመቆጣጠር አልመው መንቀሳቀስ የጀመሩት አዳማ ከተማዎች ቢሆኑም ሙከራዎችን በማድረጉ ግን ወልቂጤዎች ቀዳሚ ነበሩ። በሚጣሉ ተሻጋሪ ኳሶች ጌታነህ እና አቤልን ትኩረት አድርገው ሲጫወቱ የታዩት ወልቂጤ ከተማዎች አቤል ነጋሽ ከሳጥን ውጪ አክርሮ መቶ በቋሚ የግቡ ብረቱ ታካ በወጣችበት እና ጌታነህ ከበደ ከቅጣት አክርሮ በመታት እና በወጣችበት ቅፅበት አከታትለው ሙከራዎችን አድርገዋል።

መረጋጋቶች ባልተስተዋሉበት ቀጣዮቹ የጨዋታ ደቂቃዎች የኳስ ቁጥጥሩን ወደ ራሳቸው በማድረግ ሲጫወቱ የተመለከትናቸው እና የውሳኔ ችግሮችም በጉልህ ይስተዋልባቸው የነበሩት አዳማዎች ደስታ ዮሐንስ ከግራ አክርሮ መቶ ፋሪስ ዕላዊ ሲተፋው አድናን ባመከናት ያለቀለት ሙከራን አድርገው ነበር። ጥንቃቄ አዘል እንቅስቃሴዎች እየተስተዋሉ ቀጥለው ወልቂጤዎች በጨዋታው መጠናቀቂያ አቅራቢያ በአጥቂዎቻቸው አማካኝነት ወደ መሪነት ለመሸጋገር በትጋት መጫወት ቢችሉም የአዳማን የመከላከል አጥር ሰብሮ ለመግባት በእጅጉ በመፈተናቸው በመጨረሻም በሙከራዎች እምብዛም ያልደመቀው አጋማሽ 1ለ1 በሆነ የአቻ ውጤት ፍፃሜውን አግኝቷል። ውጤቱን ተከትሎም ወልቂጤ ከተማ ተፎካካሪው አርባምንጭ ነጥብ መጣሉን ተከትሎ ለከርሞ በሊጉ መክረሙን አረጋግጧል።

\"\"