ሪፖርት | አርባምንጭ ከተማ ወደ ከፍተኛ ሊግ ወርዷል

እጅግ ወሳኝ በነበረው ጨዋታ አርባምንጭ ከተማ 32 የግብ ሙከራዎችን ቢያደርግም ሀዋሳ ከተማን ማሸነፍ ሳይችል ቀርቶ ፕሪምየር ሊጉን ለመሰናበት ተገዷል።

ካሳለፍነው ሳምንት አሰላለፍ አንፃር ሀዋሳ ከተማ ፀጋአብ ዮሐንስን ቅጣት ላይ በሚገኘው በረከት ሳሙኤል ዳንኤል ደርቤ እና እዮብ አለማየሁን ደግሞ በተባረክ ሄፋሞ እና ኤፍሬም አሻሞ ምትክ ተጠቅሟል። በአርባምንጮች በኩል ደግሞ ይስሀቅ ተገኝ ፣ መሪሁን መስቀለ ፣ አሸናፊ ኤልያስ እና ኤሪክ ካፓይቶ አርፈው መኮንን መርዶኪዮስ ፣ አቡበከር ሸሚል ፣ በላይ ገዛኸኝ እና ተመስገን ደረሰ ጨዋታውን ጀምረዋል።

በጥሩ ግለት በተጀመረው ጨዋታ ገና በ2ኛው ደቂቃ ተመስገን ደረሰ ከተከላካዮች ጀርባ የጣለውን ጥሩ ኳስ በላይ ገዛኸኝ ሞክሮ አላዛር ማርቆስ አምክኖበታል። ውጤቱን በአስገዳጅ ሁኔታ የሚፈልጉት አዞዎቹ በቁጥር በርክተው በሀዋሳ ሜዳ ላይ ቅብብሎችን በመከወን ጫና ለመፍጠር ሲሞክሩ ሀዋሳዎች ረዘም ባሉ ኳሶች በቀጥተኛ ጥቃት ወደ አርባምንጭ ሜዳ ለመድረስ ጥረዋል። ሆኖም ዕድሎችን በመፍጠር የተሻሉ የነበሩት አርባምንጮች በኩል 12ኛው ደቂቃ ላይ ተመስገን ደረሰ በቀኝ መስመር ያደረሰውን ኳስ አህመድ ሁሴን ሰለሞን ወዴሳን በማለፍ ግብ አድርጎት መሪ ሆነዋል።

\"\"

የሀዋሳ ከተማ የመልሶ ማጥቃት ጥረቶች እና በቀኝ ከዳንኤል ደርቤ የሚነሱ ኳሶች ለጎሉ ምላሽ ለመስጠት ቀጥለው ሲታዩ አዞዎቹም በበላይ ገዛኸኝ ምቶች ልዩነቱን ለማስፋት ሞክረዋል። ሆኖም 23ኛው ደቂቃ ላይ ከቀኝ መስመር ሙጂብ ቃሲም ያሻገረውን ኳስ የበርናንድ ኦቻንግ መዛናጋት ታክሎበት እዮብ ዓለማየሁ ከመረብ አገናኝቶታል። ይህ የተከላካዮች አለመረጋጋት 28ኛው ደቂቃ ላይም ተደግሞ ዓሊ ሱለይማን ሳጥን ውስጥ ያገኘው ዕድል ለጥቂት ወደ ላይ ተነስቶበታል።

አርባምንጮች በላይ ገዛኸኝ በቀኝ ሳጥን ውስጥ ገብቶ 29ኛው ደቂቃ ላይ ሌላ ኢላማውን የጠበቀ ሙከራ ያደረገበትን አጋጣሚ ጨምሮ ተደጋጋሚ ኳሶችን ጠንከር ባሉ ምቶች ለማስቆጠር ሲሞክሩ የሀዋሳ ተከላካዮች ተደርበው በማውጣት መክተዋል። ሀዋሳዎችም ከቀደመው የመልሶ ማጥቃት ጥረት በተጨማሪ የኳስ ቁጥጥራቸውን በማሳደግ የእንቅስቃሴ ብልጫ ወስደዋል። ጨዋታው ሊጋመስ ሲል ግን 41ኛ ደቂቃ ላይ እምብዛም ማጥቃት ተሳትፎ ያልነበረው ወርቅይታደስ አበበ በቀኝ ሳጥን ውስጥ ደርሶ የመለሰለትን ኳስ አጋማሹን ጥሩ የተንቀሳቀሰው ተመስገን ደረሰ በማይታመን መልኩ አምክኖታል።

ሁለተኛውን አጋማሽ አዞዎቹ በተሻጋሪ ኳሶች እና የርቀት ሙከራዎች ጀምረዋል። ለግብ በቀረበው ቀዳሚ የቡድኑ ሙከራ 55ኛው ደቂቃ ላይ ተመስገን መላኩ ኤልያስ ከአህመድ ተቀብሎ ያሳለፈለትን ኳስ አክርሮ ቢሞክርም አላዛር ይዞበታል። ግብ ጠባቂው ከሦስት ደቂቃዎች በኋላም አህመድ ፀጋአብ ዮሐንስን አልፎ የመታውን ኳስ በተመሳሳይ ሁኔታ አድኖበታል። አዞዎቹ የማጥቃት ጥረታቸው ቀጥሎ ተደጋጋሚ ሙከራዎች አድርገዋል። ሆኖም ጎል የማስቆጠር ችኮላ እና የአላዛር ማርቆስ ብቃት ወሳኙን ግብ ከማግኘት አግዷቸዋል። በቀጣይ ደቂቃዎችም እንዲሁ የአቡበከር ሻሚል እና አህመድ ሁሴን ሙከራዎች ሳይሳኩ ቀርተዋል።

የአርባምንጭ ጫና ከ70ኛው ደቂቃ በኋላም ሲቀጥል 72ኛ ደቂቃ ላይ አበበከር ሻሚል ከሳጥን ውጪ ያደረገው ሙከራ በግቡ አግዳሚ ሲመለስ 74ኛው ደቂቃ ላይ ደግሞ አህመድ ሀሴን አላዛርን አልፎ ለማስቆጠር ያደረገው ጥረት ሳይሳካ ሲቀር ተቀይሮ የገባ ቡታቃ ሸመና መልሶ የመታውን ደግሞ ሰዒድ ሁሴን ከግብ ስር አውጥቶታል። ፍፁም ብልጫ የተወሰደባቸው ሀዋሳዎች ጨዋታው ወደ ማብቂያው ሲቃረብ ከሙጂብ ቃሲም እግር የሚነሱ ኢላማቸውን ያልጠበቁ ሙከራዎች ቢያደርጉም የአርባምንጭ ከተማ ለግብ የቀረቡ የማጥቃት ሂደቶች በጨዋታ ውጪ እንቅስቃሴዎች እና በደካማ ውሳኔዎች ታጅቦ ቀጥሎ ጨዋታው በ1-1 ውጤት ተጠናቋል። አርባምንጭ ከተማዎች እስከፍፃሜው ድረስ አንድ ጎል በማስቆጠር በሊጉ የመቆየት ዕድል የነበራቸው ቢሆንም ያባከኗቸው እጅግ በርካታ የግብ ዕድሎች እና ወልቂጤ ከተማ ከአዳማ ከተማ ጋር ነጥብ መጋራታቸውን ተከትሎ ከፕሪምየር ሊጉ ለመውረድ ተገደዋል።

\"\"

አሰልጣኝ በረከት ደሙ ጨዋታው ከተጠናቀቀ በኋላ ተጫዋቾች ለመትረፍ ከነበራቸው ጉጉት የመነጨውን ጫና መቋቋም እንዳልቻሉ እና ለከተማው ታዳጊዎች ተስፋ የነበረው ክለብ መውረድ እንዳሳዘናቸው ገልፀው በሂደቱ የክለቡ አመራሮች አፈፃፀም ጉድለት እንደነበር አበክረው አንስተዋል። አሰልጣኝ ዘርዓይ ሙሉ በበኩላቸው ደካማ የመከላከል አፈፃፀም እንደነበራቸው እና አርባምንጮች እንደውም ዕድለኛ እንዳልነበሩ ተናግረዋል።