መረጃዎች | ያለመውረድ ፍልሚያው ፍፃሜ

ነገ ሦስተኛውን ወራጅ የሚለዩትን ሁለት ጨዋታዎች የተመለከቱ መረጃዎችን እንደሚከተለው አቅርበናል።

ሀዋሳ ከተማ ከ አርባምንጭ ከተማ

ሀዋሳ ከተማን ደረጃውን ለማሻሻል አርባምንጭ ከተማ ደግሞ በሊጉ ለመቆየት የሚያደርጉት ተጠባቂ ጨዋታ 09:00 ላይ በአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ስታዲየም ይከናወናል።

ሀዋሳ ከተማዎች ባለፈው ሳምንት በባህርዳር ከተማ የአንድ ለባዶ ሽንፈት ከገጠማቸው በኋላ የስድስት ጨዋታዎች ያለመሸነፍ ጉዟቸው መገታቱ ይታወሳል። ሽንፈቱ ተከትሎም ደረጃቸው ለማሻሻል የነበረባቸው ዕድል አባክነዋል። በነገው ጨዋታም አሁንም ደረጃቸውን አሻሽለው ዓመቱን የመጨረስ ዕድል ስላላቸው ለጨዋታው አናሳ ግምት ሰጥተው ይገባሉ ተብሎ አይጠበቅም። ሀዋሳዎች በሊጉ ጠንካራ የተከላካይ ክፍል ካላቸው ቡድኖች ውስጥ ይጠቀሳሉ። ምንም እንኳ በመጨረሻዎቹ አራት ጨዋታዎችም አራት ግቦች ቢያስተናግዱም በውድድር ዓመቱ በስምንት ጨዋታዎች ላይ ግቡን ያላስደፈረ እና በቀላሉ ለጥቃት የማይጋለጥ አደረጃጀት እንዳላቸው አስመስክረዋል። የነገው ተጋጣሚያቸውም በሊጉ ለመትረፍ ያላቸውን ሁሉ አሟጠው ይጠቀማሉ ተብለው የሚጠበቁት አዞዎቹ ስለሆኑ ተከታታይ ነጥቦች ጥለው ዓመቱን ላለማገባደድ ጠንክረው መቅረብ ይጠበቅባቸዋል።

\"\"

አርባምንጭ ከተማዎች ያላቸውን የመትረፍ ዕድል ለመጠቀም የሞት ሽረት ትግል እንደሚያደርጉ ግልፅ ነው። የባለፉት ጨዋታዎች ቁጥሮቻቸውም ቡድኑ ምን ያህል እንደተሻሻለ ቁልጭ አድርገው ያሳያሉ። ቡድኑ በፈረሰኞቹ ከተሸነፈ በኋላ ባደረጋቸው ሰባት ጨዋታዎች ሽንፈት አልቀመሰም። እሱም ብቻ ሳይሆን በተጠቀሱት ጨዋታዎች አስር ግቦች አስቆጥሮ በሦስት ጨዋታዎች ግብ ሳይቆጠርበት ወጥቷል። አዞዎቹ የነገው ጨዋታ የዓመቱ ትልቁ መርሀ-ግብራቸው ስለሆነ በሥነ-ልቦና ረገድ ትልቅ ዝግጅት ማድረግ ይጠቅባቸዋል። ምንም እንኳ የመትረፋቸው ጉዳይ ለመወሰን የወልቂጤ ከተማን ውጤት መጠበቅ ግድ ቢላቸውም ቀድመው የራሳቸው የቤት ስራ መስራት ስላለባቸውም ለነገው ጨዋታ ልዩ ትኩረት ማድረጋቸው አይቀሪ ነው።

በነገው ጨዋታም በጥሩ አቋም የነበረውን ቀጥተኛ የማጥቃት አጨዋወታቸው ላይ ለውጥ ማድረግ ወይም የበለጠ ጥራትና ጥንካሬ ማላበስ ግድ ይላቸዋል። ለምን ቢባል በግዙፍ ተጫዋቾች የተዋቀረውን የሀዋሳ የተከላካይ መስመር በቀጥተኛ እና ረዣዥም ኳሶች ለመስበር አዳጋች ነው ተብሎ ስለሚታሰብ ነው።

በጨዋታው ሀዋሳዎች ተባረክ ሄፋሞ እና በረከት ሳሙኤልን በቅጣት ላውረንስ ላርቴ እና ብርሀኑ አሻሞን በጉዳት ምክንያት አያሰልፉም። አርባምንጭ ከተማዎች ግን በቅጣትም ሆነ በጉዳት የሚያጡት ተጫዋች አይኖርም።

ሁለቱ ቡድኖች እስካሁን በሊጉ 17 ጊዜ የመገናኘት ታሪክ አላቸው። ከዚህ ውስጥ ሰባቱ ጨዋታዎች በአቻ ውጤት ሲጠናቀቁ ሀዋሳ ከተማ ስድስት ጊዜ አርባምንጭ ደግሞ አራት ጊዜ ድል ቀንቷቸዋል። በጨዋታዎቹ ከተቆጠሩ ግቦች 19ኙ የሀዋሳ 15ቱ ደግሞ የአርባምንጭ ሆነው ተመዝግበዋል።

ወልቂጤ ከተማ ከ አዳማ ከተማ

በሊጉ የመቆየት ዕድላቸው ራሳቸውን ለመወሰን የሚጫወቱት ወልቂጤዎች እና አዳማ ከተማ የሚያደርጉት ጨዋታ 09:00 ላይ በአዳማ አበበ ቢቂላ ስታዲየም ይደረጋል።

ወልቂጤዎች የመትረፍ ዕድላቸውን ራሳቸው የመወሰን ስልጣን ይዘው ወደ ነገው ጨዋታ ይቀርባሉ። ሆኖም ቡድናቸው በጥሩ ወቅታዊ አቋም አይገኝም ፤ መድንን ካሸነፉ በኋላ ሁለት አቻ እና አንድ ሽንፈት አስመዝግበው ማግኘት ከሚገባቸው ዘጠኝ ነጥቦች ሁለቱን ብቻ አሳክተዋል።

ከፍተኛ የሆነ ግብ የማስቆጠር ችግር ያለባቸውና ከባለፉት አራት ጨዋታዎች በአንዱ ብቻ ግብ ያስቆጠሩት ሰራተኞቹ በነገው ወሳኝ ጨዋታ ይህንን ችግር በቀዳሚነት መቅረፍ ይጠበቅባቸዋል።
ከዚህ በፊት በጌታነህ ከበደ ላይ ብቻ ጥገኛ የነበረው እና ሌላ የግብ አማራጭ ያልነበረው ቡድኑ በነገው ወሳኝ ጨዋታ ሌሎች የግብ ምንጮች ማበጀት ይጠበቅበታል። ከዚህ በተጨማሪ ለኋላ መስመሩ ጥሩ እገዛ እንዲደረግ እና ለመከላከል አደረጃጀቱ ጥሩ ሽፋን እንዲሰጡ ያስቻላቸውን አጨዋወት ላይ የተሻለ የማጥቃት አጨዋወት አክለው ሚዛናዊ አቀራረብ ይዘው መቅረብ አለባቸው።

\"\"

ቡድኑ ከሌላው ክፍሎች በተለየ ጠንካራ የተከላካይ ክፍል አለው። ጥምረቱም ከመጨረሻዎቹ አራት የሊግ ጨዋታዎች ሁለት ግቦች ብቻ አስተናግዶ በሦስት ጨዋታዎች መረቡን ሳያስደፍር ወጥቷል። ምንም እንኳ የተከላካይ ክፍሉ ጠንካራ ቢሆንም አዳማ ከተማም በተመሳሳይ በጥሩ ወቅታዊ አቋም ላይ የሚገኝ የማጥቃት ጥምረት ያለው ቡድን እንደመሆኑ በነገው ጨዋታ ብርቱ ፉክክር ይጠብቀዋል ተብሎ ይታመናል። ወልቂጤዎች በነገው ጨዋታ በሦስት ጨዋታዎች ስምንት ግቦችን ያስቆጠረው የተጋጣሚያቸው የአጥቂ ክፍል ተቋቁመው ግብ የማስቆጠር አቅማቸው ማሳደግ ከቻሉ ዕድላቸውን ተጠቅመው በሊጉ የሚቆዩ ይሆናል።

አዳማ ከተማ ሳይጠበቅ በለገጣፎ ለገዳዲ ከተሸነፈ በኋላ አንሰራርቶ በተከታታይ ሦስት ጨዋታዎች ላይ ሽንፈት አልቀመሰም። ከማሸነፉም በላይ ትኩረት የሚስበው ጉዳይ ደግሞ ያስቆጠራቸው ግቦች ብዛት ነው። በተጠቀሱት ጨዋታዎች ስምንት ግቦች አስቆጥሯል ፤ ቡድኑ በጨዋታ በአማካይ 2.6 ግቦች እያስቆጠረ አሸንፏል።

ከዛ በፊት አምስት ድል አልባ ጨዋታዎች ያሳለፉት በይታጉሱ እንዳለ የሚመሩት አዳማዎች በመጨረሻ ሦስት ተከታታይ ጨዋታዎች የሰበሰቧቸው ነጥቦች ደረጃቸውን እንዲያሻሽሉ ረድተዋቸዋል።
የነገው ጨዋታ ማሸነፍም ደረጃቸው ከፍ ሊያደርግላቸው ስለሚችል ቀላል ግምት እንደማይሰጡት ዕሙን ነው። ሁለቱም ቡድኖች በመጀመርያው ዙር ያደረጉት ጨዋታ በአዳማ ከተማ የሦስት ለአንድ አሸናፊነት መጠናቀቁ ይታወሳል።

በወሳኙ ጨዋታ የወልቂጤ ከተማዎቹ የኋላሸት ሰለሞን ፣ ብዙዓየሁ ሰይፉ እና አፈወርቅ ኃይሉ በጉዳት ምክንያት አይሰለፉም። በአዳማ ከተማዎች በኩል ደግሞ በቅጣትም ሆነ በጉዳት የሚያጡት ተጫዋች ባይኖርም ዳዋ ሆቴሳ እና ዮሴፍ ታረቀኝ ከቡድኑ ጋር እንደማይገኙ ተሰምቷል።

በሊጉ የእርስ በርስ ግንኙነት ታሪካቸው አምስት ጨዋታዎችን ያደረጉት ሁለቱ ቡድኖች ሦስት ጊዜ ነጥብ ተጋርተው አንድ አንድ ጊዜ ተሸናንፈዋል። በጨዋታዎቹ ወልቂጤ ከተማ አራት እንዲሁም አዳማ ከተማ አምስት ግቦችን አስቆጥረዋል።