ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ | የ29ኛ ሳምንት ምርጥ 11

በ29ኛው የሊጉ የጨዋታ ሳምንት ላይ ጎልተው የወጡ ተጨዋቾች እና አሰልጣኝን የመረጥንበት የሳምንቱ ምርጥ ቡድን ይህንን ይመስላል።

አሰላለፍ 4-2-3-1

ግብ ጠባቂ

ቢኒያም ገነቱ – ወላይታ ድቻ

ወላይታ ድቻ በሊጉ ለመቆየት ወሳኝ በነበረው የወልቂጤው ጨዋታ ላይ በመታተር ሜዳ ላይ ጥሩ ቆይታን ያደረገው ግብ ጠባቂው ቢኒያም ገነቱ ድርሻው ከፍ ያለ ነበር። የተደረጉ ሙከራዎችን በድግግሞሽ ከማክሸፍ በተጨማሪ የጌታነህ ከበደን የፍፁም ቅጣት ምት መመለስ በመቻሉ በምርጥ ስብስባችን ልናካትተው ችለናል።

\"\"

ተከላካዮች

ዓለምብርሀን ይግዛው – ፋሲል ከነማ

ፋሲል ከነማ በርካታ ተጫዋቾቹን በጉዳት እና በተለያዩ ምክንያቶች ሳይዝ በገባበት የኢትዮ ኤሌክትሪኩ ጨዋታው ቡድኑ በተጋጣሚው የመስመር አጨዋወት ሲፈተን ወጣቱ ተጫዋች መስመሩን በአግባቡ ተቆጣጥሯል። ከዚህም አልፎም ቡድኑ መሪ የሆነበትን ግብ እንዲያገኝ በማስቻሉ ከተሰለፈበት የግራ መስመር ወደተለመደው የቀኝ ቦታው መልሰን መርጠነዋል።

ውሀብ አዳማስ – ወልቂጤ ከተማ

ሰራተኞቹ ዘንድሮ በሊጉ ከቆዩ ወሳኝነት የነበረው ከወላይታ ድቻ ነጥብ የተጋሩበት ጨዋታ ነበር። በጨዋታው ግብ ሳያስተናግዱ ከወራጅ ቀጠናው ቀና ያሉበት ነጥብ እንዲመዘገብ ውሀብ አዳምስ በንቃት የመከላከል ወረዳውን ከመቆጣጠር ባለፈ ወደ ፊት ወጣ ብሎ በጥሩ ጊዜ አጠባበቅ ጥቃቶችን ከጅምሩ ሲያቋርጥ የነበረበት አኳኋን እጅግ አስፈላጊ ነበር።

ሚሊዮን ሰለሞን – አዳማ ከተማ

የአዳማ ከተማ የኋላ ደጀን የሆነው ሚሊዮን በተረጋጋ እና በከፍተኛ የራስ መተማመን የሚያደርጋቸው እንቅስቃሴዎች በብዙዎች ዘንድ አድናቆት እያስተረፉለት ነው። ተከላካዩ ባለፈው የጨዋታ ሳምንት ቡድኑ ኢትዮጵያ መድንን 3-0 ሲረታ የመድን የአጥቂ ክፍል የጠሩ የግብ ዕድሎችን እንዳይፈጥር በተለይም የሚገባቸው ጊዜያቸውን የጠበቁ ሸርታቴዎች ወሳኝ ሚና ነበራቸው።

ደስታ ዮሐንስ – አዳማ ከተማ

አዳማ ከተማ መድንን 3-0 ሲረታ እንደ ቡድን አጋሩ ሚሊዮን ሁሉ ደስታ ዮሐንስም የተሳካ ቀን ማሳለፍ ችሏል። ለቡድኑ የመስመር ጥቃት ሁነኛ መሳሪያ የሆነው ተከላካዩ መስዑድ መሐመድ ከማዕዘን ያሻገረለትን ኳስ ከሳጥን ውጪ አክርሮ በመምታት በውድድሩ ከታዩ ድንቅ ግቦች አንዱን ማስቆጠር ችሏል። ከውጤታማነቱ ባሻገር ያደረገው እንቅስቃሴም በቦታው ያለ ተቀናቃኝ ተመራጭ ያደርገዋል።

\"\"
አማካዮች

ናትናኤል ዘለቀ – ቅዱስ ጊዮርጊስ

ፈረሠኞቹ የውድድሩ አሸናፊ መሆናቸውን ባረጋገጡበት የሀዲያ ሆሳዕናው ጨዋታ ናትናኤል ዘለቀ መሃል ሜዳው ላይ በሚያደርጋቸው ቅብብሎች የሚፈጥራቸው የግንኙነት መስመሮች ስኬታማ ነበሩ። ቡድኑ በኳስ ቁጥጥሩ የበላይነቱን እንዲወስድ እና በርካታ የግብ ዕድሎችን እንዲፈጥር ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያደረገው አማካዩ ቸርነት ጉግሣ ላስቆጠራት ግብም በድንቅ ዕይታ አመቻችቶ ማቀበል ችሏል።

ጋቶች ፓኖም – ቅዱስ ጊዮርጊስ

ፈረሰኞቹ የሊጉን ዋንጫ ከፍ ባደረጉበት የሳምንቱ ጨዋታቸው ግዙፉ የመሐል ሜዳ ተጫዋች ለቡድኑ ውጤታማ መሆን የነበረው ድርሻ ቀላል የማይባል ነበር። መሐል ሜዳው ላይ ቡድኑ ብልጫ እንዳይወሰድ የተሰጠውን ሚና በአግባቡ ሲወጣ የታየው ተጫዋቹ በሳምንቱ ልቀው ከወጡ ተጫዋቾች በቦታው የተሻለ መሆን መቻሉን ተከትሎ በምርጫችን ሊካተት ችሏል።

አብስራ ተስፋዬ – ባህር ዳር ከተማ

ባህርዳር ከተማ በፕሪምየር ሊጉ ሁለተኛ ሆኖ ባጠናቀቀበት የሀዋሳው ጨዋታ ላይ በወጥነት ከጊዜ ጊዜ መሻሻሎችን እያስመለከተን የመጣው የመሐል ሜዳው አማካይ አብስራ ተስፋዬ ለቡድኑ ድል ሜዳ ላይ ጥሩ እንቅስቃሴ አድርጓል። ከእንቅስቃሴ በዘለለም ብቸኛዋን የማሸነፊያ ውብ ግብ ምንአልባትም የውድድር ዓመቱ ምርጥ ጎል በሚያሰኝ ሁኔታ ማስቆጠር ችሏል።

ቸርነት ጉግሳ – ቅዱስ ጊዮርጊስ

ቅዱስ ጊዮርጊስ 29ኛ የሊግ ዋንጫውን ማንሳቱን ባረጋገጠበት ጨዋታ የመስመር አጥቂው ዕረፍት የለሽ እንቅስቃሴ አድርጓል። ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል በተደጋጋሚ ራሱን ነፃ አድርጎ ለመግባት ያልተቸገረው እና በአንድ ለአንድ ግንኙነት ወቅትም ስኬታማ የነበረው ቸርነት ከፈጠራቸው የግብ ዕድሎች ባሻገር የቡድኑን የመጀመሪያ ግብም በስሙ አስመዝግቧል።

ኦሴይ ማዉሊ – ፋሲል ከነማ

በኤሌክትሪኩ ጨዋታ ከወትሮው የመጨረሻ አጥቂነት ቦታው ወደ ኋላ ሳብ ብሎ የተጫወተው ማዉሊ በቡድኑ አብዛኛው ጥቃቶች ላይ ቀጥተኛ ተሳትፎ ነበረው። በዚህ መነሻነትም አንድ ግብ አመቻችቶ አቀብሎ ሁለተኛውን ግብ ራሱ በማስቆጠሩ በምርጥ ቡድናችን ላይ በዕለቱ የነበረውን ሚና በመንተራስ ከፊት አጥቂው ጀርባ ያለው ቦታ ላይ ተጠቅመነዋል።

አጥቂ

ብሩክ በየነ – ኢትዮጵያ ቡና

ኢትዮጵያ ቡና መቻልን ገጥሞ 2-1 አሸንፎ ሲወጣ በትጋት የተሞላው የፊት የአጥቂው ግልጋሎት ቀላል የሚባል አልነበረም። ወደ መሐል ሜዳ በጥልቀት እየተሳበ የቅብብል አማራጮችን ይፈጥር የነበረው ብሩክ ከእንቅስቃሴው በዘለለ ሁለተኛዋን ግብ በድንቅ አጨራረስ ማስቆጠሩ ሊያስመርጠው ችሏል።

\"\"

አሰልጣኝ ዘሪሁን ሸንገታ

ቅዱስ ጊዮርጊስ የውድድር ዓመቱ ቻምፒዮን መሆኑን ባረጋገጠበት የሀዲያ ሆሳዕናው ጨዋታ ከድል ባሻገር በእንቅስቃሴ ያሳየው ብልጫ አሰልጣኝ ዘሪሁን ሸንገታን የሳምንቱ ምርጥ አሰልጣኝ አሰኝቷቸዋል። ክለባቸው በታሪኩ 29ኛውን ክብር ማሳካቱን ባወጀው በዚህ ድል ቡድኑ ጨዋታውን በቁርጠኝነት የቀረበበት መንገድ እና ተንሳሽነቱ ለአሰልጣኙ መመረጥ ሌላኛው ምክንያት ነው።

ተጠባባቂዎች

ፍሬው ጌታሁን – ድሬዳዋ ከተማ
ወልአማኑኤል ጌቱ – ኢትዮጵያ ቡና
ተስፋዬ ነጋሽ – ለገጣፎ ለገዳዲ
ካርሎስ ዳምጠው – ለገጣፎ ለገዳዲ
አቤል እያዩ – ፋሲል ከነማ
ዮሴፍ ታረቀኝ – አዳማ ከተማ
አማኑኤል አረቦ – ለገጣፎ ለገዳዲ
ቢኒያም ጌታቸው – ድሬዳዋ ከተማ