ሪፖርት | መቻል የውድድር ዓመቱን በግብ ተንበሽብሾ አጠናቋል

መቻሎች ለመጀመሪያ ጊዜ አራት ግቦች ባስቆጠሩበት ጨዋታ ለገጣፎ ለገዳዲን 4-1 መርታት ችለዋል።

\"\"

የምሽቱ መርሐግብር መቻልን ከለገጣፎ ለገዳዲ ሲያገናኝ መቻሎች በ29ኛው ሳምንት በኢትዮጵያ ቡና 2-1 ሲሸነፉ ከተጠቀሙት አሰላለፍ ዳግም ተፈራ ፣ ከነዓን ማርክነህ እና በረከት ደስታን በማሳረፍ በምትካቸው ውብሸት ጭላሎ ፣ በኃይሉ ግርማ እና ምንይሉ ወንድሙን በማስገባት ለጨዋታው ሲቀርቡ ለገጣፎዎች በበኩላቸው በተመሳሳይ ሳምንት ሲዳማ ቡናን 3-2 ሲረቱ ከተጠቀሙት አሰላለፍ የአምስት ተጫዋቾች ለውጥ አድርገዋል። በዚህም ሚኪያስ ዶጂ ፣ አቤል አየለ ፣ ኤልያስ አታሮ ፣ ሱራፌል አወል እና ኢብሳ በፍቃዱ በኮፊ ሜንሳህ ፣ በረከት ተሰማ ፣ ታምራት አየለ ፣ ቴዲ ንጉሡ እና ሱለይማን ትራኦሬ ተተክተው ጀምረዋል።

ለተመልካች ማራኪ ፉክክር በተደረገበት የመጀመሪያ አጋማሽ ጨዋታው በተጀመረ በ2ኛው ደቂቃ ግብ ተቆጥሮበታል። ምንይሉ ወንድሙ በሳጥኑ የግራ ጠርዝ ላይ ተከላካዩን ተስፋዬ ነጋሽን አታልሎ በመቀነስ እና ድንቅ ግብ በማስቆጠር መቻልን መሪ ማድረግ ችሏል።

ፈጣን የማጥቃት እንቅስቃሴዎች በቀጠሉበት ጨዋታ ለገጣፎዎች 16ኛው ደቂቃ ላይ አቻ ሆነዋል። ሱራፌል ዐወል ከረጅም ርቀት ከቅጣት ምት የግብ ጠባቂውን ውበሸት ጭላል እጅ ጥሳ የገባች ግሩም ግብ መረቡ ላይ ማሳረፍ ችሏል። ሆኖም ጨዋታው አቻ ከሆነ በኋላ እየተቀዛቀዘ ሄዶ ተጠቃሽ የማጥቃት እንቅስቃሴዎች ሳይደረጉበት አጋማሹ ተጠናቋል።

ከዕረፍት መልስ እጅግ ተሻሽለው በመቅረብ ስኬታማ አጋማሽ ያሳለፉት መቻሎች 50ኛው እና 55ኛው ደቂቃ ላይ እስራኤል እሸቱ ባደረጋቸው ሙከራዎች የተጋጣሚን የግብ ክልል መፈተሽ ሲችሉ 58ኛው ደቂቃ ላይ ጨዋታውን በድጋሚ መምራት ጀምረዋል። ግሩም ሀጎስ በኃይሉ ግርማ የተቀበለውን ኳስ ከሳጥን ውጪ በግራ እግሩ አክርሮ በመምታት ድንቅ ግብ ማስቆጠር ችሏል።

ጨዋታውን መምራት ከጀመሩ በኋላ እጅግ እየጋሉ የሄዱት መቻሎች በርካታ የግብ ዕድሎችን መፍጠር ሲችሉ 67ኛው ደቂቃ ላይ ዮዳሄ ዳዊት በቀኝ መስመር ከቅጣት ምት ያደረገውን ሙከራ በሁለተኛው አጋማሽ ተቀይሮ የገባው ግብ ጠባቂው በሽር ደሊል ሲመልስበት በአንድ ደቂቃ ልዩነት ግን ተጨማሪ ግብ አስቆጥረዋል። ምንይሉ ወንድሙ ከበኃይሉ ኃይለማርያም ጋር የተቀባበለውን ኳስ በመጨረሻም በግሩም አጨራረስ መረቡ ላይ አሳርፎታል።

በመጀመሪያው አጋማሽ ከነበራቸው እንቅስቃሴ እጅግ ተቀዛቅዘው የቀረቡት ለገጣፎዎች ይባስ ብሎም 73ኛው ደቂቃ ላይ በተዘናጉበት ቅፅበት 4ኛ ግብ ተቆጥሮባቸዋል። በኃይሉ ኃይለማርያም ወደ ግብ የመታውን ኳስ ባልተጠበቀ መንገድ ያገኘው ዮሐንስ መንግሥቱ ግብ አድርጎታል። በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎችም በመቻል በኩል ምንተስኖት አዳነ ጥሩ ሙከራ ማድረግ ችሎ ነበር። ጨዋታውም በመቻል 4-1 አሸናፊነት ተጠናቋል።

ከጨዋታው በኋላ በተሰጡ አስተያየቶች የመቻል አሰልጣኝ ፋሲል ተካልኝ በመጀመሪያ አጋማሽ አጀማመራቸው ጥሩ ቢሆንም በጥቅሉ ግን አጋማሹ እንዳሰቡት እንዳልነበር ከዕረፍት መልስ ግን ያደረጉት የታክቲክ እና የተጫዋች ለውጥ ስኬታማ እንደነበር በመጠቆም የመጨረሻው ጨዋታ በዚህ ውጤት በመዘጋቱ ደስተኛ እንደሆኑ ሲገልፁ የለገጣፎ አሰልጣኝ ዘማርያም ወልደጊዮርጊስ በበኩላቸው ዘንድሮ ወደ ፕሪሚየር ሊጉ ያደጉ ክለቦች ከእነርሱ እና ከኢትዮ ኤሌክትሪክ መማር እንዳለባቸው አበክረው በመግለፅ በሁለተኛው ዙር የሚታዩ መሻሻሎች እንደነበሩ እና በለገጣፎ የነበራቸው ቆይታ ጥሩ እንደነበር በመግለፅ ተጫዋቾቻቸውን አመስግነዋል።

\"\"