የሴካፋ ከ18 ዓመት በታች የሴቶች ዋንጫ ውድድር የሀገር ለውጥ ተደርጎበታል

ኢትዮጵያን ተሳታፊ የሚያደርገው የሴካፋ ከ18 ዓመት በታች የሴቶች ዋንጫ ውድድር የሀገር ለውጥ ተደርጎበት ከአስር ቀናት በኋላ ይጀመራል።

በምስራቅ እና መካከለኛው አፍሪካ (ሴካፋ) አማካኝነት የሚደረገው የሴካፋ ከ18 ዓመት በታች የሴቶች ዋንጫ ውድድር ዘንድሮ በኬኒያ አስተናጋጅነት እንደሚደረግ ከወር በፊት ተጠቁሞ ሀገራት ዝግጅታቸውን ሲያደርጉ የሰነበቱ ቢሆንም በበጀት እና መሰል ምክንያቶች ውድድሩ ለሁለት ጊዜያት ያህል ከተራዘመ በኋላ በመጨረሻም ውድድሩ ላይደረግ የሚችልበት ዕድልም እንዳለ መገለፁ ይታወሳል።
\"\"
የውድድሩ የበላይ አካል ሴካፋ ባደረገው ስብሰባ በኬኒያ ሊደረግ የነበረው ይህ ውድድር የሀገር ለውጥ በማድረግ በታንዛኒያ ዳሬ ሰላም እንዲደረግ ስለመወሰኑ ታውቋል። የቦታ ለውጥ ሊደረግበት የቻለበትን ምክንያት አወዳዳሪው አካል ይፋ ባያደርግም ቀደም ብላ ውድድሩን ልታስተናግድ የተመረጠችው ኬኒያ ግን በሀገሪቱ በሚደረገው የትምህርት ቤቶች ውድድር እና ወቅቱም የፈተና መሆኑን ተከትሎ ከውድድሩ ራሷን ስለማግለሏ ተሰምቷል።
\"\"
ውድድሩ በታንዛኒያ ዳሬ ሰላም ከሐምሌ 18 ጀምሮ እስከ ነሐሴ 1/2015 ድረስ ለአስራ አራት ቀናቶች እየተደረገ የሚቆይ ሲሆን ሀገራችን ኢትዮጵያን ጨምሮ ታንዛኒያ ፣ ዩጋንዳ ፣ ብሩንዲ ፣ ሩዋንዳ እና ዛንዚባር በውድድሩ ተካፋይ እንደሚሆኑ ይጠበቃል።