ኢትዮጵያ መድን የመስመር አጥቂ አስፈረመ

የአሰልጣኝ ገብረመድህን ኃይሌው ኢትዮጵያ መድን የአምበሉን ውል ሲያራዝም የመስመር አጥቂም ወደ ክለቡ ቀላቅሏል።

በፕሪምየር ሊጉ ባደገበት ዓመት የሦስተኛ ደረጃን በመያዝ የፈፀመው የገብረመድህን ኃይሌው ኢትዮጵያ መድን በዛሬው ዕለት ወደ ዝውውር በመግባት ሙሴ ካባላን ማስፈረሙ ይታወሳል። ክለቡ ከሰዓታት በፊትም የነባር ተጫዋቹን ውል ሲያድስ አንድ ተጫዋችም ማስፈረሙን ድረ ገፃችን አረጋግጣለች።
\"\"
የክለቡ አዲሱ ፈራሚ አቡበከር ወንድሙ ነው። የቀድሞው የሀላባ ከተማ እና አዲስ አበባ የመስመር አጥቂ ያለፉትን ሁለት የውድድር ዓመታት በአዳማ ከተማ ቆይታ ካደረገ በኋላ ወደ ኢትዮጵያ መድን ለማምራት ከክለቡ ጋር ባደረገው ድርድር ለቀጣዩ አንድ ዓመት በክለቡ ለመጫወት በዛሬው ዕለት ፊርማውን አኑሯል።
\"\"
አብዱልከሪም መሐመድ በክለቡ ውሉን አድሷል። የቀድሞው የደበብ ፓሊስ ፣ ሐዋሳ ከተማ ፣ ሲዳማ ቡና ፣ ኢትዮጵያ ቡና ፣ ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ፋሲል ከነማ የመስመር ተከላካይ ስፍራ ተጫዋች ያለፈውን ዓመት በመድን በአምበልነት ጭምርን ክለቡን ካገለገለ ሲሆን ለተጨማሪ አንድ ዓመትንም በክለቡ ውሉን አራዝሟል።