ንግድ ባንክ ሁለት ተጨማሪ ተጫዋቾችን አስፈርሟል

በካፍ ቻምፒየንስ ሊግ የዞን የማጣሪያ ጨዋታውን ለማድረግ በሀዋሳ ዝግጅት ዛሬ የጀመረው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሁለት ተጨማሪ ተጫዋቾችን አስፈርሟል።

በአሰልጣኝ ብርሀኑ ግዛው የሚመራው እና በካፍ ቻምፒዮንስ ሊግ በዞን የማጣሪያ ጨዋታ ያለበት የወቅቱ የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ ቻምፒዮኑ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በዛሬው ዕለት በሀዋሳ አርቴፊሻል ሜዳ ለውድድሩ ዝግጅቱን የጀመረ ሲሆን ሁለት አዳዲስ ተጫዋቾችን ዛሬው ዕለት የግሉ አድርጓል።
\"\"
ትንቢት ሳመኤል የክለቡ አዲሷ ፈራሚ ሆናለች። ከሀዋሳ የጀመረው የእግር ኳስ ህይወቷ በመቀጠል ለመቐለ 70 እንደርታ ፣ ድሬዳዋ ከተማ እና በተጠናቀቀው የውድድር ዓመት በኢትዮ ኤሌክትሪክ ቆይታን ካደረገች በኋላ መዳረሻዋ ንግድ ባንክ ሆኗል። ሌላኛዋ አዲስ ፈራሚ ቤተልሄም አስረሳኸኝ ሆናለች። የቀድሞዋ የአዳማ ከተማ ፣ ጌዲኦ ዲላ እና ኤሌክትሪክ ተጫዋች አምስተኛ ፈራሚ ሆና ነው ንግድ ባንክን መቀላቀል የቻለችው። ክለቡ ከሁለቱ አዳዲሶች ባለፈ የምስራች ላቀውን ውልም አድሷል።
\"\"
ከቀናት በፊት ድርሻዬ መንዛን ፣ መሠሉ አበራ እና ሶፋኒት ተፈራን ያስፈረመው ክለቡ ከቀናት በኋላ የአሰልጣኝ ብርሀኑ ግዛውን ውል ማራዘምን ጨምሮ ከሀገር ውስጥ እና ከሀገር ውጪ ተጠባቂ ዝውውርን እንደሚፈፅም ለማረጋገጥ ቸለናል።