ጥሪ የተደረገላቸው ተጫዋቾች እነ ማን ናቸው?

ለመጀመርያ ጊዜ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ጥሪ የተደረገላቸው ትውልደ ኢትዮጵያውያን ተጫዋቾችን ተዋወቋቸው።

የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ለአራት ትውልደ ኢትዮጵያውያን ተጫዋቾች ጥሪ ማድረጉን በማኅበራዊ ትስስር ገፁ ማስታወቁ ይታወሳል። ተጫዋቾቹም ማርክስ ቬላዶ ፀጋዬ ፣ ዳንኤል ስብሃቱ ፣ ሜቴዎስ ሩምሌይ እና ዳንኤል ንጉሤ መሆናቸው ተጠቅሷል። የተጠቀሱት አራት ተጫዋቾችም ቡድኑ ወደ አሜሪካ ካቀና በኋላ እንደሚቀላቀሉ ፌዴሬሽኑ አስታውቋል። እኛም ስለ ተጫዋቾቹ ጥቂት መረጃዎች ለማጋራት እንሞክራለን።
\"\"

የመጀመርያው የሃያ ሁለት ዓመቱ ትውልደ ካናዳዊ አጥቂ ማርክስ ቬላዶ ፀጋዬ ነው። ከኢትዮጵያዊ አባት እና ኤልሳልቫዶራዊት እናት የተገኘው ይህ ወጣት ተጫዋች ከዚ በፊት ለኤልሳቫዶር ከሀያ ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን መጫወት የቻለ ተጫዋች ነው። የእግርኳስ ሕይወቱ በዋናው ሊግ ተሳታፊ በሆነው ኤድመንተን ጀምሮ በአሁኑ ወቅት በካናዳ League 1 ontario ለሚሳተፈው ስክሮሶፒ የተሰኘ ክለብ በመጫወት ላይ ይገኛል።

ሁለተኛው በተመሳሳይ በአጥቂ ክፍል ላይ የሚጫወተው ዳንኤል ስብሃቱ ሲሆን ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ጥሪ የተደረገለት ተጫዋች ነው። በሁለተኛው የሊግ እርከን USL Championship በሚሳተፈው አታላንታ ዩናይትድ ሁለት በመጫወት ላይ የሚገኘው ይህ ተጫዋች በቡድኑ ተስፋ ከሚጣልባቸው ተጫዋቾች አንዱ ነው። በቅርቡም በሜጀር ሊግ ሶከር ተሳታፊ ለሚሆነው ዋናው ቡድን በቋሚነት ያገለግላል ተብሎ ተስፋ ተጥሎበታል።

ሌላው Bærum Sportsklubb ከተባለ በኖርዌይ ሁለተኛ የሊግ እርከን ከሚሳተፈው አንጋፋ ክለብ የተመረጠው የ21 ዓመት ግብ ጠባቂ ዳንኤል ንጉሤ ነው። በክለቡ የመጀመርያ ተመራጭ በመሆን እየተጫወተ የሚገኘው ይህ ተጫዋች በውድድር ዓመቱ በአስራ አንድ የሊግ ጨዋታዎች ላይ በቋሚነት ተጫውቷል። ተጫዋቹ ያለፉት ሁለት ዓመታት በፊንላንድ ሊግ ቆይታ በማድረግ ወደ ቀድሞ ክለቡ Bærum Sportsklubb ተመልሶ የቋሚነት ቦታውን ማስጠበቅ ችሏል። በሊጉም ተስፋ ከሚጣልባቸው ወጣት ተጫዋቾች ስሙ ይጠቀሳል።

\"\"
ማቴዎስ ሩምሌይ ሌላው ጥሪ የደረሰው ተጫዋች ነው። በኢትዮጵያ አዲስ አበባ የተወለደው እና ማርክ ሩምሌይ በተባለ ግለሰብ በማደጎ ወደ አሜሪካ ያቀናው ይህ ተጫዋች በሰባት ዓመቱ NFL\’s Punt, Pass & Kick National Championships በተባለ ውድድር ከተሳተፈ በኋላ ወደ እግር ኳስ እንደገባ ይናገራል። የመሃል እና የግራ መስመር ተከላካይ ሆኖ መጫወት የሚችለው ይህ ተጫዋች በአሁኑ ወቅት ጆርጅ ታውስ ሆያስ ለተባለ ቡድን በመጫወት ላይ ይገኛል።