አንድ የዋልያዎቹ ተጫዋች ወደ አሜሪካ አይጓዝም

ዑመድ ኡኩሪ ወደ አሜሪካ ከሚያቀናው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ልዑክ ውጪ መሆኑ ታውቋል።
\"\"
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ወደ አሜሪካ በማቅናት የጉብኝት የወዳጅነት ጨዋታዎችን ከጉያና አቻው እና ከአትላንታ ሮቨርስ ክለብ ጋር እንደሚያደርግ ይታወቃል። ከብሔራዊ ቡድኑ አባላት ምክትል አሠልጣኙ ደግአረገ ይግዛው እና አጥቂው ዳዋ ሆቴሳ በቪዛ ምክንያት ከጉዞ እንደቀሩ ከቀናት በፊት ዘገባ አቅርበን የነበረ ሲሆን አሁን የዝግጅት ክፍላችን በደረሳት መረጃ መሠረት ደግሞ ሌላኛው አጥቂ ዑመድ ኡኩሪ ከጉዞ ውጪ ሆኗል።
\"\"
በቡድኑ ልዑክ የሚገኙ ጥቂት ሰዎች ትናንት ረፋድ እና ዛሬ ረፋድ ወደ አሜሪካ ጉዞ ያደረጉ ሲሆን በርካታ ተጫዋቾች የሚገኙበት ስብስብ ደግሞ ዛሬ ምሽት 4 ሰዓት ወደ ስፍራው የሚያቀና ይሆናል። በሁለት ቀን በሦስት ቡድን ወደ ስፍራው ከሚያቀናው ዝርዝር ውስጥ ደግሞ በኦማን ሊግ የውድድር ዓመቱን ያሳለፈው ዑመድ ኡኩሪ ከጉዞ ዶክመንቶች አለመሟለት (ፓስፖርት) ጋር በተያያዘ እንደሌለ አውቀናል። ተጫዋቹ እስከ ዓርብ ከቡድኑ ጋር አዳማ ላይ ልምምድ ሲሰራ የነበረ ቢሆንም በትናንትናው ዕለት ግን ልምምድ እንዳልሰራም ሰምተናል።