​ቻምፒየንስ ሊግ፡ ዋይዳድ እና አህሊ የመልስ ጨዋታቸውን ዛሬ ምሽት ያደርጋሉ

የካፍ ቶታል ቻምፒየንስ ሊግ የ2017 የውድድር ዘመን አሸናፊ ዛሬ ምሽት ካዛብላንካ ላይ በሚደረገው የመልስ ጨዋታ ይለያል፡፡ ዋይዳድ ካዛብላንካ እና አል አህሊ በፍፃሜ ጨዋታ የተገናኙ ሲሆን ከሳምንት በፊት አሌክሳንድሪያ ላይ 1-1 አቻ መለያየታቸው ይታወቃል፡፡

የመልሱ የፍፃሜ ጨዋታ እጅግ በጣም ተጠባቂ እንዲሆን ካስቻሉት ነገሮች አንዱ ሁለቱም ክለቦች አሸናፊ ለመሆን አሁንም የሰፋ እድል መያዛቸው ነው፡፡ ዋይዳድ ከሜዳው ውጪ የአቻ ውጤትን ይዞ እንደመመለሱ በሜዳው ደግሞ ያደረጋቸውን የቻምፒየንስ ሊግ ጨዋታዎች እንደማሸነፉ ዋንጫውን ለማንሳት ቅድመ ግምት ቢሰጠውም ሃያሉ የካይሮው ክለብ አል አህሊ በፈተና የተሞሉ ጨዋታዎችን በድል ሲወጣ መመልከት የተለመደ መሆኑን ተክተሎ ክለቡ በቀላሉ እጅ እንደማይሰጥ ይጠበቃል፡፡

በመጀመሪያው ጨዋታ ሞሜን ዛካሪያ እና አሽራፍ ቤንሻሪኪ ግቦች ማስቆጠራቸውን ይታወሳል፡፡ የዋይዳድ የአጥቂ አማካይ የሆነው ቤንሻሪኪ የክለቡ ሁለት ወሳኝ አጥቂዎች ዊሊያም ጄቦር እና ፋብሪስ ኦንዳማ መልቀቃቸውን እንዲሁም የ2016 የቻን ኮከብ ግብ አስቆጣሪ ቺሶማ ቺካታራ ከአሰልጣኝ ሁሴን አሞታ ጋር በገባው ቅራኔ ምክንያት በሃሰተኛ 9 ቁጥር ሚና ክለቡን በእጅጉ እየጠቀመ ይገኛል፡፡ አምስት የቻምፒየንስ ሊግ ግቦችን በስሙ ያስመዘገበው ቤንሻሪኪ በጨዋታው ላይ ላይ የመስመር አማካዩ መሃመድ ኦንዠም በጉዳት አለመኖሩ ጫና እንዳያሰድርበት ያሰጋል፡፡ ኦንዠም ለዋይዳድ ስኬታማነት ቁልፍ ሚናን የተጫወተ ተጫዋች እንደመሆኑ የሱ አለመኖር ያለጥርጥር ለዋይዳድ ጉዳት አለው፡፡ በአንፃሩ አህሊ የአምበሉን ሆሳም አሹር እና የግራ መስመር ተከላካዩን አሊ ማሎልን ግልጋሎት አያገኝም፡፡ አሹር ከተጎዳ አንድ ወር ያለፈው ሲሆን አህሊ በተለይ በመስመር ማጥቃቱ ላይ የተዋጣለን እንዲሆን ተጠቃሽ እንቅስቃሴ የሚያሳየው የቱኒዚያው ኢንተርናሽናል ማሎል አለመኖር ለሆሳም ኤል ባድሪ አሳሳቢ ነው፡፡

የኳስ ቁጥጥር ብልጫን መሰረት ያደረገ እንቅስቃሴ ከሚያደርገው አህሊ ጋር የሚጫወተው ዋይዳድ እንደመጀመሪያው ጨዋታ መከላከልን ብቻ መሰረት ያደረገ ጨዋታ ይከተላል ተብሎ አይጠበቅም፡፡ አሰልጣኝ ሁሴንም ይህንኑ ደግፈዋል፡፡ ጨዋታው ያለግብ ለማጠናቀቅ መሞከር እራስን እንደማጥፋት የሚቆጠር መሆኑን የሚጠቁሙት ሁሴን አህሊን አጥቅተው ለመጫወት ቃል ቀብተዋል፡፡ አሰልጣኝ ሆሳም በበኩላቸውን ዋይዳድ በሜዳው የአጨዋወት ለውጥ ማሳየት እንዳይቀር በመገመት ክለባቸው በሚፈጠሩ ክፍተቶች ግብ ለማስቆጠር እንደማይቸገር ተማምነዋል፡፡

እረቡ እለት የአል አህሊ ደጋፊዎች በክለቡ የልምምድ ማዕከል በመሄድ ተጫዋቾቻቸውን ሲያበረታቱ ታይተዋል፡፡ በርካታ ቁጥር ያላቸው ደጋፊዎች በልምምድ ሜዳው በመገኘታቸው አህሊ ልምምዱን ለመሰረዝ ተገዷል፡፡ በአንፃሩ በስታደ መሃመድ አምስተኛ በሚደረጉ ጨዋታዎች ቡድናቸውን ከማበረታት ቀርተው የማይታወቁት የዋይዳድ ደጋፊዎች ለፍፃሜ ጨዋታ ድምቀትን ይሰጣሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ከቀናት በፊት የፍፃሜ ጨዋታ መግቢያ ትኬት ሲሸጥ በርካታ ሺህ ደጋፊዎች ለመግዛት መምጣታቸው እና ደጋፊዎች በተፈጠረው መጨናነቅ መጎዳታቸው ታይቷል፡፡

ጨዋታውን በመሃል ዳኝነት የሚመሩት ጋምቢያዊው ሁለት ግዜ የአፍሪካ የአመቱ ምርጥ አርቢትር ሆኖ የተመረጠው ባካሪ ፓፓ ጋሳማ ነው፡፡ ጨዋታው በሱፐርስፖርት 9 እና 5 እንዲሁም በቤን ስፖርትስ 1 ኤችዲ ላይ የቀጥታ ስርጭት ሽፋን ያገኛል፡፡


እውነታዎች
ለመጨረሻ ግዜ የካፍ ቻምፒየንስ ሊግን ያሸነፈው የሞሮኮ ክለብ ራጃ ካዛብላንካ ሲሆን እሱም በ1999 ነበር፡፡ ለመጨረሻ ግዜ የቻምፒየንስ ሊጉ አሸናፊ የሆነው የግብፅ ክለብ አል አህሊ በ2013 ነው፡፡

ዋይዳድ ካዛብላንካ በ1992 የቻምፒየንስ ሊጉ አሸናፊ ሲሆን አል አህሊ ስምንት ግዜ ውድድሩን ማሸነፍ የቻለ ክለብ ነው፡፡

ዋይዳድ ለመጨረሻ ግዜ ለፍፃሜ የደረሰው በ2011 ሲሆን በቱኒዚያው ኤስፔራንስ ደ ቱኒዝ ተሸንፎ ዋንጫው አጥቷል፡፡

ከ1997 ወዲህ በተደረጉ የቻምፒየንስ ሊጉ ውድድሮች የሰሜን አፍሪካ ክለቦች 11 ዋንጫዎችን ማሸነፍ ችለዋል፡፡

5፡00 – ዋይዳድ አትሌቲክ ክለብ ከ አል አህሊ (ስታደ መሃመድ አምስተኛ)

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *