ሪፖርት | መቐለ ከተማ የመጀመርያ የሊግ ነጥቡን አሳክቷል

የኢትዮዽያ ፕሪምየር ሊግ የ2010 የውድድር ዘመን የመክፈቻ እለት ጨዋታዎች በሶስት የሀገሪቱ ከተሞች ተካሂደዋል፡፡ ከነዚህም መካከል አርባምንጭ ላይ አርባምንጭ ከተማ ከ መቐለ ከተማ ያገናኘው ጨዋታ ያል ጎል በአቻ ውጤት ተጠናቋል።

ለአመታት የአርባምንጭ ከተማ ሜዳ ለራሱ ለአርባምንጭም ሆነ ለተቃራኒ ተጋጣሚ ቡድኖች ኳስ ለመጫወት ሜዳው አመቺ አይደለም የሚል ቅሬታ ሲስተናገድበት ቆይቷል፡፡ ፌዴሬሽኑም ሜዳው ጥሩ አለመሆኑን ተከትሎ ተደጋጋሚ ማስጠንቀቂያ ለክለቡ መላኩ የሚታወስ ነው፡፡ በዛሬው ጨዋታ ይህ ሜዳ አስፈላጊው ጥገና ተደርጎለት ለእንቅስቃሴ አመቺ ሆኖ ታይቷል፡፡

መቐለ ከተማ ጨዋታው ሊጀመር 20 ደቂቃ ሲቀረው ዘግይተው ወደ ሜዳ የመጡበት ሁኔታ ከጨዋታው መጀመር በፊት አነጋጋሪ የነበር ክስተት ነበር። አርባምንጭ ከተማ በሜዳው ጨዋታ ሲኖረው በርከት ብሎ የሚገኘው ደጋፊው ዛሬም በብዛት ነበር ክለቡን ለመደገፍ ወደ ሜዳ የመጣው። በጣም አስገራሚው ግን ከመቐለ ፣ አአ እና ወላይታ ሶዶ የመጡ የመቐለ ከተማ ደጋፊዎች ለስታድየሙ ሌላ ድምቀቶች ነበሩ።

በፕሪምየር ሊጉ በአንፃራዊነት ረጅም አመት ልምድ ያለው አርባምንጭ እና በሊጉ ታሪክ የመጀመርያ ተሳታፊ ሆኖ በቀረበው መቐለ ከተማ መካከል የተደረገ ጨዋታ ከመሆኑ አንፃር ብዙዎች ቅድሚያ የማሸነፍ ግምት የሰጡት ለአርባምንጭ ቢሆንም ሜዳ ላይ በተመለከትነው እንቅስቃሴ መቐለ ከተማ የተሻለ ሆኖ ታይቷል፡፡
ፌደራል ዳኛ ይርጋለም ወ/ጊዮርጊስ በጥሩ ብቃት በዋና ዳኝነት የመሩት የዛሬው ጨዋታ አሰልቺ ፣ ያልተሳኩ ቅብብሎች የበረከቱበት እና ኳሶች በተደጋጋሚ የሚባክኑበት እንቅስቃሴ ነበር፡፡ በዘጠና ደቂቃ ውስጥ ለጎል የቀረበ ሙከራ የተመለከትነውም ሁለት ጊዜ ብቻ መሆኑም ጨዋታውን በሚገባ የሚገልጸው ነው፡፡ ለዚህም እንደምክንያት ማንሳት የሚቻለው አርባምንጭ በጨዋታው ላይ በደቡብ ካስቴል አሸናፊ ሆኖ ከመጣበት ጥንካሬ እጅግ ተዳክሞ የቀረበ ከመሆኑ በተጨማሪ እና መቐለ ከተማ ከሜዳ ውጭ እንደመጫወቱ እና ለሊጉ አዲስ እንደመሆኑ መከላከልን መሰረት አድርጎ መግባቱ በጨዋታው ላይ ማራኪ እንቅስቃሴ እንዳይታይ አድርጎታል።

አሰልጣኝ ፀጋዬ ኪዳነማርያም ጨዋታውን በ4-2-3-1 አሰላለፍ ሲጀምሩ የዮሀንስ ሳህሌ መቐለ ከተማ በ4-5-1 በጥብቅ የመከላከል አቀራረብ ወደ ሜዳ ገብተዋል፡፡ አርባምንጮች በተጀራጀ ሁኔታ የጎል አጋጣሚ ለመፍጠር ሲያደርጉት የነበረውን ጥረትም ክፍተት ባለመስጠት ሲያከሽፉ ተስተውሏል፡፡ በዚህም አርባምንጮች ረጃጅም ኳሶችን ወደመጠቀም ግዴታ ውስጥ ቢገቡም አብዛኛዎቹ ኳሶች መድረሻው ሳይታወቅ ይባክን ነበር። በመጀመርያው አጋማሽ በዚህ መንገድ ከሳጥን ውጭ በሚጣሉ ረጅም ኳሶች አርባምንጭ የጎል አጋጣሚ የፈጠረው 38ኛው ደቂቃ ላይ ከወርቅይታደል አበበ የተሻገረውን ኳስ አለልኝ አዘነ በግንባሩ ገጭቶ ለጥቂት ብረቱን ታክኮ ከወጣው የጎል አጋጣሚ ውጪ የተፈጠረ ሌላ የጎል አጋጣሚ አልተፈጠረም። መቐለ ከተማዎች በአንፃሩ በራሳቸው የሜዳ ክልል ተገድበው ሲንቀሳቀሱ አልፎ አልፎ በመልሶ ማጥቃት ብቸኛ አጥቂ ሆኖ በተሰለፈው ዳይስት አቼምፖንግ አማካኝነት አደጋ ለመፍጠር ጥረት አድርገዋል፡፡
በሁለተኛ አጋማሽ አሰልጣኝ ፀጋዬ ኪዳነማርያም አሰላለፋቸውን ወደ 4-3-3 በመቀየር የማጥቃት እንቅስቃሴያቸውን ለማሻሻል ቢጥሩም ጠንካራ የነበረው የመቐለ ከነማ ተከላካዮች ጥምረትን ሰብረው ለመግባት ተስኗቸው ታይተዋል። ከሳጥን ውጭ ከቀኝ መስመር ላይ ላኪ ሳኒ ከርቀት የመታውና የግቡ አግዳሚ የመለሰው ሙከራም ብቸኛው የአዞዎቹ ተጠቃሽ ሙከራ ነበር።
መቐለ በጨዋታው የአቻ ውጤት ከመፈለጋቸው ጋር ተያይዞ በተደጋጋሚ ሰአት ሲያባክኑ የታዩ ሲሆን አንድም ኢላማውን የጠበቀ ሙከራ ሳያደርጉ ግባቸውንም ሳያስደፍሩ አንድ ነጥብ ከጨዋታው ይዘው ወጥተዋል፡፡ በጨዋታው ኢኳቶርያል ጊኒያዊው ግብ ጠባቂ ፊሊፕ ኢቮና ጥሩ እንቅስቃሴ ማሳየት ችሏል፡፡

በ2009 የውድድር አመት በሊጉ በ16 ጨዋታዎችን በአቻ ውጤት በማጠናቀቅ ቀዳሚ የነበረው አርባምንጭ ከተማ ዘንድሮም የመጀመርያ ጨዋታውን በሜዳው በአቻ ውጤት አጠናቋል። በአንፃሩ በኢትዮዽያ ፕሪምየር ሊግ የመጀመርያው ጨዋታውን ያደረገው መቐለ ከተማ በአቻ ውጤት ውድድሩን ጀምሯል፡፡


አሰስተያየቶች


አሰልጣኝ ፀጋዬ ኪዳነማርያም 

” በዛሬው ቡድናችን መሀል ሜዳ ላይ ኳሶችን ይዞ ለመጫወት ተቸግረን ነበር፡፡ መቐለ ጠንካራ የመከላከል አጨዋወት ወደ ሜዳ ይዞ በመግባቱ አስከፍተን ለመግባት ተቸግረናል፡፡ በውጤቱ አልተደሰትኩም፡፡ ሆኖም ለቀጣይ ትምህርት ሰጥቶን ያለፈ ነው፡፡ በቀጣይ አስተካክለን እንቀርባለን፡፡ “


አሰልጣኝ ዮሐንስ ሳህሌ 

“ለሁለታችንም ከባድ ጨዋታ ነበር፡፡ እኛ እነሱን አናውቃቸውም፤ እነሱም እኛን አያቁንም፡፡ የመጀመርያው 45 ደቂቃ የመተያያ ነበር፡፡ ለእኛ ከሜዳ ውጭ እንደመጫወታችን መጠን አቻ መውጣታችን ጥሩ ውጤት ነው። ወደ ሜዳ ከመግባታችን በፊት ለመከላከል ተዘጋጅተን ነው የመጣነው፡፡ ተጫዋቾቼም ልጆቼም ታክቲካሊ ጥሩ ነበሩ፡፡ እስከ መጨረሻው ድረስ ላደረጉት ተጋድሎም ምስጋና ይገባቸዋል፡፡  “

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *