​ማራቶን ትጥቅ አምራች ኩባንያ ወደ ኢትዮጵያ ገበያ ገብቷል

የቱርኩ የስፖርት ትጥቅ አምራች ድርጅት ማራቶን ከጎ ቴዲ ስፖርት ጋር ዛሬ በሞናርክ ሆቴል የውል ስምምነት ፈፅሟል፡፡ ድርጅቱ ጎ ቴዲ ስፖርት በኢትዮጵያ ወኪል እንዲሆን የተስማማ ሲሆን የተለያዩ የስፖርት ትጥቆችን በወኪሉ በኩል ወደ ኢትዮጵያ ገበያ እንደሚያቀርብ ተነግሯል፡፡

በፊርማ ስነ-ስርዓቱ ላይ የጎ ቴዲ ስፖርት ባለቤት አቶ ቴዎድሮስ ታደለ የማራቶን ፕሬዝደንት ጄላል ካያ እና የማርኬቲንግ ዳይሬክተር የሆነችው ነዘሃት አክሶይ እንዲሁም በኢትዮጵያ እና በአፍሪካ ህብረት ቋሚ የቱርክ አምባሳደር ፋቲ ኡሉሶይ ተገኝተዋል፡፡

ጎ ቴዲ ስፖርት ከተመሰረተ አምስት ዓመታት ያለፉትን ሲሆን ከምስረታው ጀምሮ የስፖርት ትጥቆችን ለኢትዮጵያ የወንዶች እና የሴቶች ብሄራዊ ቡድኖች ፣ ለኢትዮጵያ ቡና እና ለተለያዩ የፌዴራል እና የክልል የስፖርት ማእከላት ሲያቀርብ እንደነበረ የድርጅቱ ባለቤት አቶ ቴዎድሮስ ተናግረዋል፡፡ “ከምስረታችን ጀምሮ ትጥቆችን ለተለያዩ ክለቦች እና ብሄራዊ ቡድኑ አቅርበናል፡፡ የዛሬዋ ቀን ለእኛ የተለየች ነች፡፡ ጥራት ያላቸውን ትጥቆችን ለማቅረብ ለማራቶን ጋር ስምምነት ላይ ደርሰናል፡፡ ማራቶን በዓለም ከሚታወቁ ብራንዶች አንዱ ነው፡፡” ብለዋል።

በ1992 በኢስታንቡል የተመሰረተው ማራቶን ኢትዮጵያን ጨምሮ ለ47 ሃገራት የስፖርት ትጥቆችን ያቀረባል፡፡ ድርጅቱ ትጥቆቹን በምስራቅ አውሮፓ ለሚገኙ ክለቦች እና ለሳውዲ አረቢያዎቹ አል ኢቲሃድ ጅዳ እና አል ናስር ማቅረብ ችሏል፡፡ የድርጅቱ ፕሬዝደንት ካያ በንግግራቸው ጥራት ያላቸው ትጥቆችን ለኢትዮጵያ ማቅረብ ከጎ ቴዲ ስፖርት ጋር መስማማታቸው እንዳስደሰታቸው ተናግረዋል፡፡ “ቴዲ በኢትዮጵያ ኦፊሴላዊ ወኪላችን በመሆን አብሮን ለመስራት በመፈለጉ ደስተኛ ነን፡፡ አሁን የፈፀምነው ውል በአፍሪካም የመጀመሪያው ነው፡፡ ስለዚህም የተለየ ቦታ እንሰጠዋለን፡፡” ያሉ ሲሆን ማራቶን አቅርቦቱን በማስፋት የስፖርት ትጥቅ ማምረቻ ትልቅ ፋብሪካ ለማቋቋምም በእቅድ ደረጃ ይዟል፡፡

መገኛቸውን ከአውስትራሊያ እና አውሮፓ ያደረጉ የስፖርት ትጥቅ አምራች ድርጅቶች በቅርቡ በሁሉም እርከን ላይ ለሚገኙ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድኖች ትጥቅ ለማቅረብ ሲወዳደሩ ተመልክተናል፡፡ የጣሊያኑ ኤሪያ አሸናፊ በመሆን ስራውን የጠቀለለ ሲሆን ለደደቢት ጥቅት በማቅረብ ላይ ይገኛል። ለሲዳማ ቡናም ትጥቅ ለማቅረብ በድርድር ላይ ይገኛል፡፡ ማራቶንም በኦፊሴላዊ ወኪሉ በኩል መሰል ተመሳሳይ ውሎችን ይፈፅማል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *