​የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 4ኛ ሳምንት – የእሁድ ጨዋታዎች ቅድመ ዳሰሳ

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አራተኛ ሳምንት ጨዋታዎች እሁድ በአዲስ አበባ ፣ በጎንደር ፣ በመቐለ እና በሀዋሳ ከተሞች የሚቀጥሉ ይሆናል። ሊጉ የሚያስተናግዳቸውን አራት ጨዋታዎችን እንደሚከተለው ቃኝተናቸዋል።

ኢትዮ ኤሌትሪክ ከ ወልዋሎ ዓ.ዩ

ኢትዮ ኤሌክትሪክ ከወትሮው በተለየ መልካም አጀማመር ላይ ያለ ይመስላል። በሁለት ጨዋታዎች አራት ነጥብ ያሳካው ክለቡ አርባምንጭን ከተማን ከሜዳው ውጪ ማሸነፉ በብዙዎች ዘንድ ያልተጠበቀ ነበር። ለሊጉ እንግዳ የሆነው ወልዋሎ ዓ.ዩ እስካሁን ሽንፈት ባያስተናግድም ሙሉ ሶስት ነጥቦችን ያሳካበት ጨዋታ የለም። በዚህም መሰረት ከደረጋቸው ሶስት ጨዋታዎችም ሶስት ነጥቦችን መሰብሰብ ችሏል።

የኢትዮ ኤሌክትሪክ የመሀል  እና የአጥቂ ክፍል መሻሻል ለቡድኑ ጥሩ አጀማመር ምክንያት ሆኗል።  ሔኖክ ካሳሁን ለተከላካይ መስመሩ የሚሰጠው ሽፋን እንዲሁም የቀኝ መስመር አማካዩ አልሀሰን ካሉሻ ከፊት አጥቂው ዲዲዬ ለብሪ ጋር እያሳየ ያለው ጥምረት ለአሰልጣኝ ብርሀኑ ባዩ ቡድን ጥንካራን አላብሶታል። በዚህ ላይ የኃይሌ እሸቱ ከጉዳት መመለስ ደግሞ ለቡድኑ ተጨማሪ ጉልበት ይሆነዋል። ከሜዳ ውጪ በሚደረጉ ጨዋታዎች ላይ እንዳብዛኞቹ ክለቦች መከላከል ላይ ብቻ ተመርኩዞ የማይገባው ወልዋሎ ዓ.ዩ በነገውም ጨዋታ ተመሳሳይ አቀራረብ እንደሚኖረው ይጠበቃል። ቡድኑ እንደ ፕሪንስ ሰቨሪንሆ ያሉ የመስመር አጥቂዎችን በመጠቀም በፍጥነት ወደ ጎል ለመድረስ ይሞክራል። በጨዋታውም ጠንካራ የአማካይ ክፍል ፍልሚያ የሚጠበቅ ይሆናል።

የኢትዮ ኤሌክትሪኩ ግብ ጠባቂ ሱሊማን አቡ ከጉዳቱ ባለማገገሙ ይህ ጨዋታ ያልፈዋል። ተስፋዬ ዲባባን ከጉዳት መልስ በሚያገኙች ወልዋሎዎች በኩል ደግሞ ኤፍሬም ጌታቸው እና ብሩክ አየለ በጉዳት ለቢጫ ለባሾቹ የማይሰለፉ ይሆናል።

ፌ/ዳ ይርጋለም ወ/ጊዮርጊስ በመሀል ዳኝነት እንዲሁም ኢ/ዳ ክንዴ ሙሴ እና ፌ/ዳ አንድነት ዳኛቸው በረዳት ዳኝነት ጨዋታውን እንደሚመሩት ይጠበቃል።

ፋሲል ከተማ ከ ወልድያ

ሳምንት ወደ ጅማ ተጉዞ ጅማ አባጅፋርን በፊሊፕ ዳውዝ ጎል ማሸነፍ የቻለው ፋሲል ከተማ አራት ነጥቦችን ከሰበሰቡ ሰባት የሊጉ ክለቦች መሀል አንዱ መሆን ችሏል። አዳማ ከተማ ላይ በተቀዳጀው ድል ሊጉን የጀመረው ወልድያ ደግሞ በሳምንቱ በሀዋሳ ከተማ በሰፊ ጎል ተሸንፎ ድሬደዋ ከተማን በሜዳው ያስተናገደበትን ጨዋታ ማሸነፍ ሳይችል በአቻ ውጤት ተለያይቷል። ሀለቱ ቡድኖች አምና በሊጉ ጎንደር ላይ ሲገናኙ ፋሲል ከተማ በይስሀቅ መኩሪያ ብቸኛ ጎል ማሸነፉ የሚታወስ ነው።

እንደ አምናው አይነት የመከላከል ጥንካሬ የሌለው ወልድያ ከሜዳው ውጪ በሚያደርገው በዚህ ጨዋታ ላይ በጥንቃቄ ላይ አመዝኖ ወደሜዳ ይገባል ለማለት ያስቸግራል። ቡድኑ ሊጉን ወደ ጀመረበት መንፈስ ለመመለስም ይህን ጨዋታ ማሸነፍ አማራጭ የሌለው ሀሳብ ነው የሚሆነው። አምና ብዙዎችን ያስደመመው ፋሲል ከተማ በሜዳው ላይ በሚያደርጋቸው ጨዋታዎች ላይ ሲቸገር ይስተዋል ነበር። ቡድኑ ነገ ወልድያን ሲገጥም የአመቱ የመጀመሪያ ጨዋታውን ሜዳው ላይ ያደርጋል። ስለዚህ ፋሲልም ይህን ጨዋታ አሸንፎ መውጣቱ በራሱ ሜዳ ላይ ለሚያደርጋቸው ጨዋታዎች ሊኖረው ለሚገባው የተጨዋቼች የዐዕምሮ ዝግጅት ከፍተኛ ሚና ይኖረዋል። በመሆኑም ጨዋታው የተሻለ ፉክክር የሚታይበት እንደሚህምን ይገመታል። ከዚህ ውጪ ትኩረት የሚስበው ጉዳይ አሰልጣኝ ዘማርያም ወ/ጊዮርጊስ የቀድሞው ክለባቸውን የሚገጥሙ መሆናቸው ነው። የባለሜዳው ቡድን ደጋፊዎች የቀድሞው አሰልጣኛቸውን በምን መንገድ እንደሚቀበሉት የሚጠበቅ ይሆናል።

የመሀል ተከላካዩ አዳሙ መሀመድ ከወልድያ እንዲሁም ራምኬል ሎክ ከፋሲል ከተማ በኩል በጉዳት ጨዋታው የሚያመልጣቸው ይሆናል።

ፌ/ዳ ሸዋንግዛው ተባበል እና ፌ/ዳ ሶርሳ ዱጉማ በረዳትነት እንዲሁም ፌ/ዳ ዳዊት አሳምነው በዋና ዳኝነት ጨዋታውን ይመሩታል።

መቐለ ከተማ ከ ጅማ አባጅፋር 

ሁለቱ አዲስ አዳጊ ክለቦች እርስ በእርስ በሚገናኙበት በዚህ ጨዋታ ሶስት ተከታታይ ጨዋታዎችን በአቻ ውጤት ያጠናቀቀው መቋለ ከተማ ሊጉን በማሸነፍ ከጀመረ በኃላ ሁለት ተከታታይ ሽንፈቶች የገጠሙትን ጅማ አባጅፋርን ያስተናግዳል።

በአዲስ አበባ ዋንጫ ተሳትፎው ላይ ጠንካራ የቡድን መዋቅር ታይቶበት የነበረው ጅማ አባ ጅፋር ውጤት እየቀናው አይደለም። በርግጥ ቡድኑ በርካታ አዳዲስ ተጨዋቼችን እንደማስፈረሙ ለውህደት ጊዜ ቢወስድበት አያስገርምም። አባጅፋር አሁንም ቢሆን ከወገብ በታች ያለው የቡድኑ ጥንካሬ ለክፉ የሚሰጥ ባይሆንም ግቦችን እንደልብ ማስቆጠሩ ላይ ግን ችግር ይስተዋልበታል። ወደ መቐለ ተጉዞ በሚያደርገው ጨዋታም የተከላካይ ክፍሉ እና ጥሩ የመከላከል ተሳትፎ የሚያደርገው የአማካይ መስመር ቡድኑ ከጨዋታው ነጥብ ይዞ እንዲመለስ ሊረዱት እንደሚችሉ መናገር ይቻላል። በተመሳሳይ መልኩ መቐለ ከተማም በመገንባት ላይ ያለ ቡድን ነው። ለአብነት ያህል በሁለተኛ ሳምንት ከወልዋሎ ዓ.ዩ ጋር ባደረገው ጨዋታ ላይ በቀኝ መስመር ተከላካይነት የተጠቀመውን አቼምፖንግ አሞስን በቅዱስ ጊዮጊሱ ጨዋታ ላይ በፊት አጥቂነት ማሰለፉ ይህን ነጥብ የሚያስረዳ ነው። መቐለም እንደተጋጣሚው ሁሉ ግብ በማስቆጠሩ በኩል ደካማ ሆኗል። በሶስቱ ጨዋታዎች የተገኘቺው የአማኑኤል ጎልም ከፍፁም ቅጣት ምት የተገኘች ነበረች። ጠንካራ የተከላካይ ክፍል ካለው ቡድን ጋር የሚያደርገው ይህ ጨዋታም የቡድኑን የማጥቃት አማራጮች የሚፈትን እንደሚሆን ይጠበቃል።

የመቐለ ከተማው ቢስማርክ ኦባሜንግ እንዲሁም የአባጅፋሮቹ ዝናቡ ባፋአ እና ጌቱ ረፌራ በጉዳት ሳቢያ ከየቡድኖቻቸው ውጪ ሆነዋል።

ጨዋታውን በመሀል ዳኝነት ሚመራው ፌ/ዳ ሀብታሙ መንግስቴ ሲሆን ኢ/ዳ ክንፈ ይልማ እና ፌ/ዳ ዳንኤል ዘለቀ በረዳት ዳኝነት ተመድበዋል።

ሀዋሳ ከተማ ከ ወላይታ ድቻ 

በሉጉ የሶስተኛ ሳምንት ጨዋታዎች ሀዋሳ ከተማ በደደቢት እንዲሁም ወላይታ ድቻ በአዳማ ከተማ ከደረሰባቸው ሽንፈት በኃላ እርስ በእርስ የገናኛሉ። ሀዋሳ ከሜዳው ውጪ ባደረጋቸው ሁለት ጨዋታዎች ድል ሳይቀናው ሲመለስ ወላይታ ድቻ ደግሞ በተቃራኒው እስካሁን የሰበሰባቸው አራት ነጥቦች የተገኙት ከሜዳ ውጪ በተደረጉ ጨዋታዎች ነው። በመሆኑም ጨዋታው ሜዳው ላይ ማሸነፍ የሚቀናውን ሀዋሳን ከሜዳው ውጪ ነጥቦችን ማሳካት ከቀለለው ወላይታ ድቻ ጋር የሚያገናኝ ይሆናል።

አምና 9ኛው ሳምንት ላይ 3-3 በሆነ ውጤት ተለያይተው የነበሩት ሁለቱ ቡድኖች ነገም በመጠኑ ክፍት የሆነ ጨዋታ እንደሚያደርጉ ይገመታል። ሁለቱም ቡድኖች ከሽንፈት እንደመመለሳቸው የትኛው ክለብ ይህን ጨዋታ አሸንፎ ወደ መልካም አጀማመሩ ይመለሳል የሚለውን ጥያቄ ለመመለስ የሚደረግ ፉክክርም ይሆናል። በተጋጣሚዎቹ ላይ ከፍተኛ የመሀል ሜዳ ብልጫ የሚወስደው ሀዋሳ ከተማ ቡድኑ ጫና ውስጥ በሚገባበት ወቅት የመስመር ተመላላሾቹ ወደኃላ ተስበው መሀል ሜዳው በሚጋለጠው ወላይታ ድቻ ላይም የአማካይ ክፍል ብልጫ ሊወስድ እንደሚችል ይጠበቃል። ይህን ብልጫ ወደ ግቦች በመቀየሩ በኩል ቡድኑ በተጋጣሚው የሜዳ ክፍል የሚያሳየው ብቃት ለሚመዘገበው ውጤት ወሳ ይሆናል። የወላይታ ድቻ የፊት አጥቂ ጃክም አራፋት አብረውት ከሚሰለፉት የመስመር አጥቂዎች ጋር በመሆን በሀዋሳ የተከላካይ ክፍል ላይ የሚፈጥሩት ጫና በቅርብ ሳምንታት ተደጋጋሚ ስህተቶች ሲሰራ ከሚታየው የሀዋሳ የኃላ መስመር ፊት ንፁህ የግብ ዕድሎችን ሊያስገኝ ይችላል። ቡድኑ መከላከያን ሲያሸንፍ በዚህ መልኩ ግብ ማግኘቱ በነገውም ጨዋታ ተመሳሳይ አቀራረብ እንዲኖረው የሚያደርግ ይመስላል።

የሀዋሳ ከተማዎቹ ዮሀንስ ሴጌቦ እና ዳንኤል ደርቤ በሀዋሳ በኩል በጉዳት ሳቢያ ከጨዋታ ውጪ ሲሆኑ በተመሳሳይ መልኩ የወላይታ ድቻዎቹ ተስፉ ኤልያስ ፣ አብዱልሰመድ አሊ ፣ በዛብህ መለዮ እና ዳግም በቀለም ለጨዋታው አይደርሱም።

ጨዋታው በኢ/ዳ ለሚ ንጉሴ እና ረዳቶቹ ፌ/ዳ ቦጋለ አበራ እና ፌ/ዳ ይበቃል ደሳለኝ የሚዳኝ ይሆናል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *