በሴካፋ የሚሳተፈው የብሔራዊ ቡድኑ ስብስብ ታውቋል

ከህዳር 24 ጀምሮ በኬንያ አስተናጋጅነት በ9 የክልሉ ሃገራት መካከል በሚደረገው የምስራቅ እና መካከለኛው አፍሪካ ዋንጫ (ሴካፋ) የሚካፈለው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን 27 ተጫዋቾችን በመያዝ ላለፉት 7 ቀናት ዝግጅቱን ሲያደርግ ቆይቷል። የብሔራዊ ቡድኑ አሠልጣኝ አሸናፊ በቀለም ከስብስቡ ላይ 4 ተጫዋቾችን በመቀነስ ወደ ውድድሩ የሚያቀናውን የመጨረሻ ቡድናቸውን ይፋ አድርገዋል።

የድሬዳዋ ከተማው ተከላካይ አናጋው ባደግ፣ የጅማ አባ ጅፋሩ ዮናስ ገረመው እና የኢትዮ ኤሌክትሪኩ ኃይሌ እሸቱ ከቡድኑ ጋር ወደ ኬንያ የማይጓዙ ተጫዋቾች ሲሆኑ የኢትዮጵያ ቡናው አማካይ መስዑድ መሀመድ ሐሙስ ክለቡ በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ከሲዳማ ቡና ጋር ባደረገው ጨዋታ ካጋጠመው ጉዳት ማገገም ባለመቻሉ ከቡድኑ ውጪ ሆኗል።

ዝርዝር

ግብ ጠባቂዎች (3)

ታሪክ ጌትነት (ደደቢት)፣ በረከት አማረ (ወልዋሎ)፣ ተክለማርያም ሻንቆ (ሀዋሳ ከተማ)

ተከላካዮች (7)

ቴዎድሮስ በቀለ (መከላከያ)፣ አበበ ጥላሁን (ሲዳማ ቡና)፣ አበባው ቡታቆ (ቅዱስ ጊዮርጊስ)፣ ግርማ በቀለ (ኤሌክትሪክ)፣ አምሳሉ ጥላሁን (ፋሲል)፣ ተመስገን ካስትሮ (አርባምንጭ ከተማ)፣ ኄኖክ አዱኛ (ጅማ አባ ጅፋር)

አማካዮች (6)

ሳምሶን ጥላሁን (ኢትዮጵያ ቡና)፣ ተስፋዬ አለባቸው (ወልዲያ)፣ ከነአን ማርክነህ (አዳማ)፣ እንዳለ ከበደ (አርባምንጭ)፣ ብሩክ ቃልቦሬ (ወልዲያ)፣ ፍሬው ሰለሞን (ሀዋሳ ከተማ)

አጥቂዎች (7)

አቡበከር ሳኒ (ቅዱስ ጊዮርጊስ)፣ አብዱራህማን ሙባረክ (ፋሲል ከተማ)፣ አዲስ ግደይ (ሲዳማ ቡና)፣ ዳዋ ሁቴሳ (አዳማ ከተማ)፣ አማኑኤል ገብረሚካኤል (መቐለ ከተማ)፣ አቤል ያለው (ደደቢት)፣ ፀጋዬ ብርሀኑ (ወላይታ ድቻ)

ዋልያዎቹ ነገ ጠዋት 2 ሰዓት ላይ ወደ ናይሮቢ የሚያቀኑ ሲሆን በምዕራብ ኬንያ ከዋና ከተማዋ 360 ኪ.ሜ. ርቀት ላይ ወደምትገኘው ካካሜጋ የሚጓዙ ይሆናል። ውድድሩ እሁድ ተጋባዧ ሊብያ ከታንዛኒያ ጋር በሚታደርገው ጨዋታ ሲጀመር ሰኞ በ8 ሰዓት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከብሩንዲ አቻው ጋር በካካሜጋው ቡክሁንጉ ስታዲየም የሚጫወት ይሆናል።

በተያያዘ ዜና በ2017ቱ የምስራቅ እና መካከለኛው ዋንጫ ተሳታፊ እንዲሆኑ ከተጋበዙ 2 ቡድኖች አንዱ የሆነው እና ኢትዮጵያ በምትገኝበት ምድብ ለ ተደልድሎ የነበረው የዚምባቡዌ ብሔራዊ ቡድን ራሱን ከውድድሩ እንዳገለለ አስታውቋል። የዚምባቡዌ እግርኳስ ፌዴሬሽን ዛሬ ይፋ እንዳደረገው ከሆነ በኬንያ ያለው ፖለቲካዊ አለመረጋጋት የተነሳ ለተጫዋቾቹ ደህንነት አስተማማኝ ዋስትና ማጣቱን በውድድሩ ላለመሳተፉ በምክኒያትነት አስቀምጧል። ይህንን ተከትሎም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በምድብ ጨዋታዎች ከብሩንዲ፣ ዩጋንዳ እና ደቡብ ሱዳን ጋር ብቻ የሚገናኝ ይሆናል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *