ሪፖርት | አርባምንጭ ከተማ 1-3 ኦኪኪ አፎላቢ

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 8ኛ ሳምንት የመጨረሻ ጨዋታ በሞቃታማዋ አርባምንጭ ጅማ አባ ጅፋር ከመመራት ተነስቶ በኦኪኪ አፎላቢ ጎሎች አርባምንጭ ከተማን 3-1 በሆነ ውጤት አሸነፏል።

ጨዋታው የአርባምንጭ ከተማ የተጨዋች ቅያሪ ቡድኑን ዋጋ ያስከፈለበት በተቃራኒው የጅማ አባጅፋር የተጨዋች ለውጥ ቡድኑን ውጤታማ ያደረገበት ፣ ኦኪኪ አፎላቢ ልዩ ሆኖ በዋለበት እና በአሰልጣኝ ፀጋዬ ኪ/ማርያም ላይ ከፍተኛ ተቃውሞ የተስተናገደበት በመሆን ተጠናቋል።

በውጤት ቀውስ የሚገኙት አርባምንጭ ከተማዎች በ7ኛው ሳምንት አዲስ አበባ ስታድየም ላይ በፈረሰኞቹ የ 3-0 ሽንፈት ካስተናገዱ በኃላ ለዛሬው ጨዋታ ሲቀርቡ አሰልጣኝ ፀጋዬ ኪ/ማርያም 3 – 5 – 2 አሰላለፍን ተጠቅመዋል። ከባለፈው ሳምንት ጨዋታ አንተነህ መሳ ፣ አሌክስ አሙዙ ፣ አለልኝ አዘነ ፣ ላኪ ሳኒን በመቀየር በምትካቸው ሲሳይ ባንጫ ፣ በረከት ቦጋለ ፣ ብርሃኑ አዳሙ ፣ ዮናታን ከበደን ቋሚ 11 ውስጥ በማስገባት ነበር ባለሜዳዎቹ ጨዋታውን የጀመሩት። አባጅፋሮች በበኩላቸው በሜዳቸው ሁለተኛ የአመቱን ድላቸውን ኢትዮዽያ ቡናን 2-0 በሆነ ውጤት ሲያሸንፉ ከነበረው የጨዋታ አቀራረብ የተጨዋችም ሆነ የአጨዋወት ለውጥ ሳያደርጉ በ4-4-2 አሰላለፍ ቀርበዋል።

ከባለፉት አመታት ጀምሮ አርባምንጭ ከተማ በሜዳውም ሆነ ከሜዳ ውጭ በሚያስመዘግበው ውጤት እና በሚያሳየው የሜዳ ላይ እንቅስቃሴ ደስተኛ ያልሆኑት የአዞዎቹ ደጋፊዎች ከስታድየም መራቅ ከጀመሩ ሰነባብተዋል። ዛሬ የተመለከትነው የስታድየም ድባብም ይህን አባባላችንን የሚያጠናክር ሆኖ ነው ያገኘነው። የተመልካች ቁጥሩ አነስተኛ የነበረ ሲሆን ምክንያቱም የጨዋታው ቀን በስራ ዕለት መሆኑ ቢሆንም ዋነኛው ምክንያት ሆኖ የቀረበው ግን የቡድኑ የውጤት ማሽቆልቆል ነው።

በፌደራል ዳኞ ተካልኝ ለማ የጨዋታ መሪነት በጀመረው ጨዋታ ባለሜዳዎቹ አርባምንጮች ከጨዋታው ሙሉ ሦስት ነጥብ እንደፈለጉ በሚያመላክት ሁኔታ ፈጣን እንቅስቃሴ እና ጫና ፈጥሮ የመጫወት ሂደትን ያሳዩት ከጨዋታው መጀመር አንስቶ ነበር። በ7ኛው ደቂቃ ላይ አሚኑ ነስሩ በጅማ አባጅፋር የግብ ክልል ከጀርባው ያለውን ተጨዋች ሳይመለከት ኳስ አዙሬ እጀምራለው ሲል ምንተስኖት አበራ ነጥቆ ለብርሃኑ አዳሙ ፣ ብርሃኑ አዳሙ መልሶ ለምተስኖት አበራ በጥሩ ሁኔታ የሰጠውን ምንተስኖት አገባው ሲባል ወደ ሰማይ የሰደደው ኳስ የጨዋታው የመጀመርያ የጎል ሙከራ ብቻ ሳይሆን ባለሜዳዎቹን ቀዳሚ ሊያደርግ የተቃረበ የጎል አጋጣም ነበር። አርባምንጮች በግራው የሜዳ ክፍል በእንደለ ከበደ እና በተካልኝ ደጀኔ አማካኝነት የማጥቃት እንቅስቃሴዎችን አጠናክረው ሲቀጥሉ እንግዶቹ አብዛኛው ተጨዋቾቻቸውን ከኳስ ጀርባ እንዲሆኑ በማድረግ ሲከላከሉ ቢቆዩም 11ኛው ደቂቃ ላይ የበረከት ቦጋለን ስህተት ተጠቅሞ ኦኪኪ አፎላቢ ከሳጥን ውጭ የመታው ኳስ ለጥቂት የወጣችበትን ሙከራ ማድረግ ችለዋል ። አዞዎቹ ጫና እንደመፍጠራቸው የግብ እድል ለማግኘት ቢቸገሩም 22ኛው ደቂቃ ላይ እንዳለ ከበደ ከማዕዘን ምት ያሻገረው ኳስ ተጨራርፎ እግሩ ላይ ሲመጣለት ብርሃኑ አዳሙ አስቆጥሮ አርባምንጭን ቀዳሚ ማድረግ ችሏል ። በዛውም ብርሃኑ ጎሉን አስቆጥሮ ደስታውን ማልያውን አውልቆ በመግለፁ ምክንያት የቢጫ የማስጠንቀቂያ ካርድ ሊመለከት ችሏል ። በመቀጠልም ከግቡ መቆጠር በፊት አርባምንጮች በፍጥነት ሚያጠቁበትን እንቅስቃሴያቸውን ትተው ወደ መከላከሉ በማመዘን አፈግፍገው መጫወታቸው እና ቴክኒካል በሆነ መንገድ ሰአት የማባከን አማራጭንም መጠቀማቸው ታይቷል። ይህ ሁኔታ በአንፃሩ ለጅማ አባጅፋሮች የማጥቃት ዕድል ሰጥቶ ገፍተው እንዲጫወቱ አስችሏቸዋል ። የኳስ ፍሰቱ ከአንድ ሁለት ንክኪ በቀር በተደጋጋሚ ይቆራረጥ በነበረበት በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ውስጥ 45ኛው ደቂቃ ላይ ተመስገን ገ/ኪዳን በጥሩ መንገድ አምልጦ በመግባት ጎል ቢያስቆጥርም ኢ/ን ረዳት ዳኛ ሸዋንግዛው ተባበል ከጨዋታ ውጪ ነው በማለት በመሻራቸው የጅማ አባ ጅፋር ተጨዋቾች እና የቡድኑ አባላት በከፍተኛ ሁኔታ ውሳኔውን ተቃውመውታል ። ጨዋታውም በዚህ መልክ በባለ ሜዳዎቹ 1 – 0 መሪነት ወደ እረፍት አምርቷል

ከእረፍት መልስ ጅማ አባጅፋሮች በኦኪኪ አፎላቢ ፊት አውራሪነት የሞከሯቸውን ኳሶች የአርባምንጭ መረብ ውስጥ አግኝተዋቸዋል። በዚህ አጋማሽ የጨዋታውን መልክ ከቀየሩ አጋጣሚዎች መካከል አንዱ የሆነው አሰልጣኝ ፀጋዬ ኪዳነ ማርያም ወንድሜነህ ዘሪሁን በወንድወሰን ሚልኪያስን እንዲሁም በአማካይ ክፍሉም ሆነ በማጥቃት እንቅስቃሴው ጥሩ ሲንቀሳቀስ የነበረው ዮናታን ከበደን በአለልኝ አዘነ መቀየራቸው የቡድኑን የማጥቃት እንቅስቃሴ በመግታት ዋጋ ማስከፈሉ ብቻ ሳይሆን በሜዳ የተገኙት ደጋፊዎች በቅያሪው ተቃውሟቸውን እንዲያሰሙ በር ከፍቷል። አሰልጣኝ ገብረመድህን በተቃራኒው ንጋቱ ገብረስላሴን በይሁን እንደሻው እንዲሁም ተከላካዩ ቢንያም ሲራጅን አስወጥተው አጥቂው ሳምሶን ቆልቻን በማስገባት በማጥቃት ወረዳው የተጫዋች ቁጥር መጨመር ችለዋል።

ብቻውን ማለት በሚያስደፍር ሁኔታ ፍጥነቱን ፣ ጉልበቱን እና ክህሎቱን ተጠቅሞ ለአርባምንጭ ተከላካዮች ፈተና ሆኖ የዋለው ኦኪኪ አፎላቢ 71ኛው ደቂቃ ላይ የግል ብቃቱን በመጠቀም ከሳጥን ውጭ በግራ እግሩ ግሩም ጎል አስቆጥሮ አባጅፋሮቹን አቻ ማድረግ ቻለ። ከ5 ደቂቃ በኋላ 76ኛው ደቂቃ ላይ ተመስገን ካስትሮ ኳሱን በግንባሩ ለማራቅ ሲሞክር በስህተት ኦኪኪ አፎላቢ እግር ውስጥ ገብቶ ናይጄርያዊው አጥቂ ተከላካዮችን አታሎ በማለፍ ሁለተኛ ጎል አስቆጥሮ አባጅፋሮችን ቀዳሚ ማድረግ ችሏል።

ከዚህ በኋላ በነበረው ቀሪ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ አርባምንጮች መረጋጋት ተስኗቸው የታዩ ሲሆን በስታድየሙ የሚሰማው ተቃውሞም እየበረታ መጥቶ አብዛኛዎቹ ሜዳውን ለቀው ወጥተዋል ።

ጨዋታው በዚህ ውጤት ተጠናቀቀ ሲባል 89ኛው ደቂቃ ላይ በመልሶ ማጥቃት ሳምሶን ቆሊቻ አመቻችቶ ያሳለፈለትን ኳስ ኦኪኪ ወደ ግብነት ለውጦ ሐት-ትሪክ በመስራት ጨዋታው በጅማ አባጅፋር 3-1 አሸናፊነት ተጠናቋል።

ውጤቱን ተከትሎ ጅማ አባጅፋር በውድድር አመቱ ሦስተኛ ድሉን ሲያስመዘግብ ደረጃውንም በማሻሻል ሦስተኛ ላይ መቀመጥ መሆን ችሏል። በዘንድሮው የውድረር አመት ሐት-ትሪክ የሰራ ሶስተኛው ተጫዋች መሆን የቻለው ኦኪኪ አፎላቢ ደግሞ በ6 ጎሎች የግብ አስቆጣሪዎች ደረጃን መምራት ጀምሯል። በሜዳው ሁለተኛ ፣ በውድድር አመቱ ደግሞ አራተኛ ሽንፈቱን ያስመዘገበው አርባምንጭ በበኩሉ 14ኛ ደረጃ ላይ በመቀመጥ በውጤት አልባ ጎዳና መጓዙን ቀጥሎበታል።

ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ የአርባምንጭ ደጋፊዎች የዕለቱ ዳኞች እና የጅማ አባጅፋር ተጨዋቾችን አጨብጭበው በክብር ሲሸኙ የአርባምንጭ ከተማ የቡድን አባላት በተለይ አሰልጣኝ ፀጋዬ ላይ ጨዋታው ከተጠናቀቀ በኋላ ለ1:30 ያህል የዘለቀ ተቃውሞ አሰምተዋል።

የአሰልጣኞች አስተያየት

አሰልጣኝ ገብረህመድን ኃይሌ

” ጨዋታው በጣም ጥሩ ነበር። ሁለታችንም ለማሸነፍ እንደፈለግን በእንቅስቃሴያችን መመልከት ይቻላል። የተቀራረበ ደረጃ ላይ መገኘታችን አንዱን ጥሎ ለማምለጥ የሚደረግ ጨዋታ ነበር። በተለይ ቅያሪ ላይ የፈጠርነው ለውጥ ተሳክቶልን በማሸፋችን ደስ ብሎኛል። ውጤቱም ለቀጣይ ጨዋታ ተነሳሽነትም ከፍተኛ አስተዋፆ አለው።

” ኦኪኪ አፎላቢ በጣም አቅም ያለው ተጨዋች ነው። ከዚህ በላይም መጫወት የሚያስችል አቅም አለው። በግሉ የሚያደርጋቸው ጥረቶች ጥሩ ናቸው። እዚህ ደረጃም ለማድረስ ብዙ የቅንጅት ስራ ተሰርቶ ነው። እንደዚህ ያለ ተጨዋች በቡድንህ ውስጥ ሲኖር በግሉ ጥረት አሸንፈህ ትወጣለህ። እርሱ ዛሬ ልዩ ነበር።”

*አሰልጣኝ ፀጋዬ ኪዳነማርያም አስተያየት ለመስጠት የሚያችል ሁኔታ ውስጥ ባለመሆናቸው ምክንያት ድህረ ጨዋታ አስተያየት አልሰጡም።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *