መከላከያ በጥሩ አቋሙ በመቀጠል ተከታታይ ሁለተኛ ድሉን አስመዝግቧል

ዛሬ አዲስ አበባ ባስተናገደው ብቸኛ ጨዋታ ከድሬደዋ ከተማ ጋር የተገናኘው መከላከያ በምንይሉ ወንድሙ ድንቅ የቅጣት ምት ጎል አማካይነት ሁለተኛ ተከታታይ ድል ማጣጣም ችሏል።
 
11፡30 ላይ እንዲደረግ ቅድሚያ መርሀ ግብር ተይዞለት የነበረው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ ወደ 10 ሰዐት እንዲመጣ ቢደረግም ኢ/ን ዳኛ አማኑኤል ኃ/ስላሴ የጨዋታውን ማስጀመሪያ ፊሽካ ያሰሙት 10፡20 ላይ ነበር። ድሬደዋ ከተማ ከሚታማበት ተከላክሎ የመጫወት ዘይቤ ወጥቶ ፈጠን ያለ የማጥቃት እንቅስቃሴ ለማድረግ በመሞከር ጨዋታውን ሲጀምር የባለሜዳው መከላከያም ምላሽ ተመሳሳይ ነበር።
ባልተለመደ መልኩ አሰልጣኝ ዘላለም ሽፈራው ከመቀመጫቸው ሳይነሱ በምክትል አሰልጣኝ ስምዖን አባይ መሪነት ድሬደዋዎች ኳስ ይዘው በመጫወት ዕድሎችን ለመፍጠር ቢሞክሩም የፊት አጥቂዎቹ ኩዋሜ አትራም እና ዳኛቸው በቀለ በመከላከያ ሳጥን ውስጥ ተገኝተው ሙከራዎችን ለማድረግ የታደሉበት አጋጣሚ አልታየም። 6ኛው ደቂቃ ላይ ሰንደይ ሙቱኩ እንዲሁም 43ኛው ደቂቃ ኩዋሜ አትራም ያደረጓቸው ሙከራዎችም ከረጅም ርቀት የተደረጉ ነበር። ቡድኑ ኳስ መስርቶ ከሜዳው በሚወጣባቸው አጋጣሚዎች ተጋጣሚ ክፍተት የሚተውበትን የሜዳ ክፍል የመጠቀም ችግሩ ንፁህ እድሎችን ለመፍጠር እንዲቸገር ምክንያት ሆኖበታል። በዚህም የድሬዎች የማጥቃት እንቅስቃሴ በብዛት ወደ ግራ ያደለ እንደነበር መናገር ይቻላል። መከላከያዎችም ተመሳሳይ የሜዳ አጠቃቀም ችግር የነበረባቸው ቢሆንም ከተጋጣሚያቸው የተሻለ በፍፁም ቅጣት ምት ክልል ውስጥ በመገኘትም ሆነ ሙከራዎችን በማድረግ የተሻሉ ነበሩ። 5ኛው ደቂቃ ላይ ምንይሉ ወንድሙ ከጥቂት ሜትሮች ርቀት ላይ ከሙሉቀን ደሳለኝ እንዲሁም 9ኛው ደቂቃ ላይ ሌላኛው አጥቂ አቅሌስያስ ግርማ ከግማሽ ጨረቃው ላይ ከቴውድሮስ ታፈሰ ተቀብለው የሞከርሯቸው ኳሶች በጀማል ጣሰው ተመለሱ እንጂ በጦሩ በኩል የታዩ ጥሩ ሙከራዎች ነበሩ።
ሆኖም ጀማል 13ኛው ደቂቃ ላይ በግምት ከሠላሳ ሜትሮች ርቀት ላይ ምንይሉ ወንድሙ በአስገራሚ መልኩ በቀጥታ የመታውን ቅጣት ምት ለማዳን አልቻለም። የግቧ ባለቤት ምንይሉ 31ኛው ደቂቃ ላይ በቀኝ መስመር ከአቤል ከበደ የተላከለትን ኳስ አንድ የተከላካይ መስመር ተጨዋች ካለፈ በኃላ ሞክሮ ጀማል ያዳንበት አጋጣሚ መከላከያዎች በእጅጉ ወደ ጎል የቀረቡበት ሌላ ቅፅበት ነበር ማለት ይቻላል።
ምንይሉ በ3 ተከታታይ ጨዋታዎች ጎል በማስቆጠር በግሩም አቋም ላይ ይገኛል
በሁለተኛው አጋማሽ መከላከያዎች ጨዋታዉ በገፋ ቁጥር ወደኃላ በማፈግፈግ ውጤት ለማስጠበቅ ሲጥሩ ታይተዋል። አራቱ የአማካይ መስመር ተሰላፊዎች ወደ ተከላካይ መስመሩ በእጅጉ ተጠግተው እንዲሁም ሁለቱ የፊት አጥቂዎችንም እገዛ እያገኙ ለተጋጣሚያቸው ክፍተት ባለመስጠት ተጫውተዋል። ቡድኑ በመልሶ ማጥቃት ሙከራዎችን ለማድረግ ያሰበ ቢመስልም 83ኛው ደቂቃ ላይ ምንይሉ በግራ መስመር ሰብሮ ገብቶ በቀጥታ አክርሮ ሲመታ ጀማል ቢተፋውም ከረጅም ጊዜ በኃላ ወደ ሜዳ የተመለሰው ማራኪ ወርቁ ሳይደርስበት ቀርቶ ጀማል በድጋሜ ያዳነበት ሙከራ ብቻ በመልሶ ማጥቃት የተገኘ ዕድል ነበር። ከዚህ ውጪ 57ኛው ደቂቃ ላይ በመስፍን ኪዳኔ የተሻማውን የማዕዘን ምት ምንተስኖት ከበደ በግንባሩ ሞክሮ የግቡ አግዳሚ ያወጣበት አጋጣሚ ሌላው አረንጓዴ እና ቀይ ለባሼቹ ሙከራ ነበር። ይበልጥ ተጭነው የተጫወቱት ብርቱካናማዎቹ የመጀመሪያው አጋማሽ ችግራቸው እምብዛም ባይቀረፍም በተሻለ መልኩ ወደ ግብ ሲደርሱ ማየት ተችሏል። በተለይም አንጋፋው ወሰኑ መዐዜ ተቀይሮ ከገባ በኃላ የቡድኑ የግራ መስመር ጥቃት አስፈሪነት ቢጨምርም የተደረጉት ሙከራዎች በብዛት ከሳጥን ውጪ የተደረጉ ነበሩ። በዚህም ረገድ የ73ኛ ደቂቃ የወሰኑ ቅጣት ምት እንዲሁም ዘሪሁን አንሼቦ በቀኝ መስመር ሞክሮ የጎን መረብ ላይ ያረፈበትን እና በ84 እና 89ኛው ደቂቃዎች ላይ ኢማኑኤል ላርያ እንዲሁም አህመድ ረሺድ ያደረጓቸውን ሙከራዎችን ማንሳት ይቻላል። ከነዚህ ሙከራዎች መሀል ኢላማዋን ጠብቃ ጎል ላለመሆን የአቤል ማሞን ጥረት የጠየቀችው የወሰኑ ቅጣት ምት ብቻ ነበረች። በጭማሪ ደቂቃ ወሰኑ ከግራ መስመር ወደ ሳጥኑ ውስጥ የጣላት ኳስ አህመድ ሳይደርስባት ቀረች እንጂ ለድሬደዋ ከሜትሮች ርቀት ላይ የግብ ዕድል ለመፍጠር የተቃረበች አጋጣሚ ነበረች። በዚህ መልኩ የአቻነት ግብ ለማግኘት የሞከሩት ድሬዎች ሳይሳካላቸው ጨዋታው በመከላከያ አሸናፊነት ሲጠናቀቅ ጦሩ በሶስት ጨዋታዎች ሰባት ነጥቦችን ለመሰብሰብ ሲበቃ ድሬደዋ ከተማ ከሜዳው ውጪ በድጋሜ በመሸነፍ በደረጃ ሰንጠረዡ መንሸራተቱን ቀጥሏል።
የአሰልጣኞች አስተያየት
አሰልጣኝ ምንያምር ፀጋዬ – መከላከያ
” በራሳችን ጥቃቅን ስህተቶች እና ግብ ማስቆጠር ባለመቻላችን ስንሸነፍ ቆይተናል። ሆኖም ጥሩ እየተጫወትን የመሸነፋችንን ምክንያት እንደሰራዊት በመገምገም ችግራችንን ፈተናል። አሁን ላይ ግብ ማስቆጠር መጀመራችን ውጤታማ እያደረገን ይገኛል። ድሬደዋ ጥሩ ቡድን ነው። አክብደናቸው ነው የገባነው። በሁለተኛው አጋማሽም ተጭነውን ነበረ። መጀመሪያ ግብ በማስቆጠራችን አሸንፈን ልንወጣ ችለናል። “
ረዳት አሰልጣኝ ስምኦን አባይ – ድሬደዋ ከተማ
” የመጀመሪያው አጋማሽ ላይ የነበረው የቡድናችን ቅርፅ እና ሁኔታ አጥጋቢ አልነበረም። እነሱ ከኛ የተሻሉ ነበሩ። ሁለተኛው አጋማሽ ላይ ግን የተሻለ ተጫውተናል ሆኖም ግብ አስቆጥረን የምንፈልገውን ውጤት እስካላገኘን ድረስ ሙሉ ሉሙሉ ጥሩ ነበርን ማለት አይቻልም። ውጤቱም እንቅስቃሴያችንን የሚገልፅ ነው። መሸነፋችንም ከጫወታው አንፃር ትክክል ነው ብዬ አስባለው።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *