ሪፖርት | መቐለ ከተማ 1-1 አዳማ ከተማ

በ8ኛው ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ መቐለ ከተማ በሜዳው ትግራይ ስታድየም ኣዳማ ከተማን ያስተናገደበት ጨዋታ 1-1 በሆነ አቻ ውጤት ተጠናቋል።
ተቀዛቅዞ እና ለአጥቂዎች በቀጥታ በሚሻገሩ ያልተሳኩ ረጃጅም ኳሶች በጀመረው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ በመጀመርያዎቹ 5 ደቂቃዎች አዳማ ከተማዎች የተሻለ ሲንቀሳቀሱ ተስተውሏል። በተለይም በ4ኛው ደቂቃ ላይ የመቐለ ተከላካይ እና አማካይ መስመር መሀል በኳስ አመሰራረት ችግር የተገኘውን ኳስ ከነኣን ማርክነህ ሞክሮ ለጥቂት ወደ ውጭ ወጥታበታለች። ከ10 ኛው ደቂቃ በኃላ በነበረው የጨዋታ እንቅስቃሴ መቐለ ከተማዎች የተወሰደባቸውን የኳስ ቁጥጥር ብልጫ በማርገብ በሁለቱም የመስመር አጥቂዎች ኣማካኝነት ጥሩ ሲንቀሳቀሱ ታይቷል። በተለይም ያሬድ ከበደ በግሉ በሚያደርጋቸውን እንቅስቃሴዎች የአዳማን ተከላካይ መስመር መረበሽ ችሎ ነበር። በ13ኛው ደቂቃ ላይ የመጀመርያው ኢላማውን የጠበቀ የጎል ማግባት ሙከራ ማድረግ የቻለው በመቐለው አማካይ ሚኪኤል ደስታ ነበር፡፡ በዚህም ከአንተነህ ገ/ክርስቶስ ከቀኝ መስመር የተሻማውን ኳስ ሚኪኤለ ደስታ ኣግኝቶ ሞክሮ በግቡ ቋሚ ተመልሶበታል።
አዳማ ከተማዎች በአመዛኙ በመጀመሪያው የጨዋታ አጋማሽ ክፍል ጊዜ ጠንካራ የሚባል የግብ ሙከራ ሳያርጉ ወደ መልበሻ ክፍል ሲያመሩ በተቃራኒው መቐለ ከተማዎች በአመዛኙ በአዳማ የሜዳ ክፍል ላይ አጋድለው ባደረጉት እንቅስቃሴ 38ኛው ደቂቃ ላይ ቢስማርክ ያሻማውን ኳስ አማኑኤል ገ/ሚካኤል በግንባሩ በመግጨት ቢሞክርም የግቡ ቋሚ መልሶበታል። የመጀመርያው ኣጋማሽ ሊጠናቀቅ ጥቂት ደቂቃዎች ሲቀሩት ጥሩ ሲንቀሳቀስ የነበረው አፖንግ ከ ፍ.ቅ.ም ክልል ውጪ መሬት ለመሬት የመታውን ኳስም እንዲሁ የግቡ ቋሚ መልሶበታል፡፡
መቐለዎች ጨዋታው ከመጀመሩ በፊት ለአዳማ የማስታወሻ ስጦታ አበርክተዋል
ከመጀመርያው በተሻለ የጨዋታ እንቅስቃሴ በታየበት ሁለተኛው ኣጋማሽ ኣዳማ ከተማዎች ተመሳሳይ የጨዋታ አቀራረብ ይዘው ሲቀርቡ መቐለ ከተማዎች በአንፃሩ የማጥቃት ባህሪ ያለው ሚካኤል ደስታን ወደ መከላከል በሚያመዝነው ዳንኤል አድሃኖም በመቀየራቸው የተነሳ ቡድኑ ግቦችን ለማግኘት ሊኖረው የሚገባውን የፈጠራ አቅም እንዲያጣ አድርጎታል። 50ኛው ደቂቃ ላይ አፖንግ ከመሃል ሜዳ አጋማሽ መሃል ለመሃል ባሾለከው ኳስ አማኑኤል ከፔንዜ ጋር 1 ለ 1 ተገናኝቶ ቢሞክርም ኳሷ በፔንዜ ልዩ ብቃት ድናለች። ሆኖም 56ኛው ደቂቃ ላይ ፔንዜ በያሬድ ከበደ ላይ በስራው ጥፋት የተገኘውን ፍ.ቅ.ም አማኑኤል ገ /ሚካኤል አስቆጥሮ መቐለን መሪ ማድረግ ችሎ ነበር።
ከግቧ መቆጠር በኃላ ጫና ፈጥረው የተጫወቱት ኣዳማዎች 64ኛው ደቂቃ ላይ በግራ መስመር የተገኝውን ቅጣት ምት ኤፍሬም ዘካርያስ ሲያሻማለት ዳዋ ሆቴሳ በግምባር በመግጨት የአቻነቷን ግብ ማስቆጠር ችሏል። ከግቡ መቆጠር በኃላ የአዳማዎች ውጤት ለማስጠበቅ ወደ ኃላ ማፈግፈግ ተከትሎ መቐለዎች የማሸነፍያ ጎል ማግኘት ቢጥሩም አልተሳካላቸውም። በተለይም 87ኛው ደቂቃ ላይ አሞስ የመታው ቅጣት ምት አንተነህ ቢያገኝም ተንሸራቶ ሲሞክር ኳሷ ኢላማዋን ስታ ወደ ውጭ ወጥታለች::
የአቻ ውጤቱን ተከትሎ መቐለ ከተማ በ10 ነጥብ በነበረበት 8ኛ ደረጃ ላይ ሲረጋ አዳማ ከተማ በ11 ነጥብ በተመሳሳይ የደረጃ ለውጥ ሳያስመዘግብ 7ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *