ሪፖርት | ሲዳማ ቡና የዓመቱ የመጀመሪያ ሶስት ነጥቡን አሳክቷል

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 8ኛ ሳምንት ጨዋታ በደቡብ ደርቢ ይርጋለም ላይ ሲዳማ ቡና ወላይታ ድቻን አስተናግዶ 3-1 በሆነ ውጤት በማሸነፍ የውድድር ዘመኑ የመጀመሪያ ሶስት ነጥቡን አሳክቷል፡፡
በደቡብ ደርቢ ሁለቱ ክለቦች ሲገናኙ የደጋፊዎች ውጥረት እና ያልተገቡ የስፖርታዊ ጨዋነት ጉድለቶች ከዚህ ቀደም ይስተዋሉ የነበረ ሲሆን ይህንን ለማስቀረትም በስፖርታዊ ጨዋነት ላይ ትኩረት በማድረግ የተለያዩ ስራዎች ሲሰሩ ቆይተዋል። የዛሬው ጨዋታ ከመጀመሩ በፊትም የሁለቱ ክለቦች ተጫዋቾች ቡድኖቻቸውን የሚወክሉ የባህል አልባሳትን ስጦታ ተለዋውጠዋል። ወላይታ ድቻዎች የሲዳማ ቡናው ተጫዋች ትርታዬ ደመቀ ቅጣቱን ሳይጨርስ ነው የተሰለፈው በሚል ክስ ካስያዙ በኋላም ጨዋታው ጀምሯል፡፡
በጨዋታው የመጀመሪያ ደቂቃዎች ጥሩ የእንቅስቃሴ ቢታይበትም በሂደት ግን የተጠበቀውን ያህል ሳቢ እና ማራኪ እንቅስቃሴን ሳይሆን በተቃራኒው ፍሰት የሌለው እግርኳስ ተመልክተናል። አብዱላጢፍ መሐመድ በ9ኛው ደቂቃ ትርታዬ ደመቀ ከማዕዘን ምት ያሻገረውን ኳስ በግንባሩ ገጭቶ በማስቆጠር ሲዳማ ቡናን ቀዳሚ አድርጎል። ሲዳማ ቡናዎች መሪነቱን ከወሰዱ በኋላ ልዩነቱን ለማስፋት አጥቅተው መጫወት የቀጠሉ ሲሆን የግብ ሙከራ የበላይነቱንም መውሰድ ችለዋል። በ16ኛ ደቂቃ ላይ አብዱለጢፍ መሀመድ ከመስመር ያሻማትን ኳስ ሀብታሙ ገዛኸኝ በግንባሩ ገጭቶ ግብ ጠባቂው ወንደሰን ገረመው ሲያወጣበት በ21ኛው ደቂቃ ላይ በጨዋታው መልካም እንቅስቃሴን ሲያደርግ የነበረው ጋናዊው አብዱለጢፍ መሀመድ ሁለት የዲቻ ተከላካዮችን አልፎ የሰጠውን ኳስ ሀብታሙ ገዛኸኝ አስቆጥሮ የሲዳማን መሪነት ወደ ሁለት ከፍ አድርጓል።
ሐብታሙ የመጀመርያ የፕሪምየር ሊግ ግቡን ካስቆጠረ በኋላ ከወንድሙ ባዬ ጋር ደስታውን ሲገልፅ
ከሁለተኛው ግብ መቆጠር በኋላ በመጀመሪያው አጋማሽ ቀሪ ደቂቃዎች ከሁለቱም ቡድኖች ይህ ነው የሚባል የግብ ሙከራ ያልተደረገ ሲሆን በ38ኛው ደቂቃ ላይ ተመስገን ዱባ ከርቀት የመታው እና ዒላማውን ሳይጠብቅ የወጣው ኳስ በወላይታ ድቻ በኩል የተደረገው ብቸኛ ሙከራ ነበር። የመጀመሪያው 45 ደቂቃም በሲዳማ ቡና 2-0 መሪነት ተጠናቅቆ ቡድኖቹ ወደ እረፍት አምርተዋል።
ሲዳማ ቡናዎች ከመጀመሪያው አጋማሽ አንፃር ወርደው በታዩበት በሁለተኛው የጨዋታ ክፍለጊዜ ወላይታ ድቻዎች የእንቅስቃሴ የበላይነት የነበራቸው ሲሆን በ64ኛው ደቂቃም በጉዳት ምክንያት ተጠባባቂ ወንበር ላይ አስቀምጠውት የነበረውን ቶጎዋዊ አጥቂ ጃኮ አራፋትን በያሬድ ዳዊት ቀይረው ካስገቡ በኃላ የተሻለ መንቀሳቀስ ችለዋል። ተጨማሪ ግብ ማስቆጠር የቻለው ግን ባለሜዳው ሲዳማ ቡና ነበር። በ62ኛው ደቂቃ አብዱለጢፍ በረጅሙ ወደ ድቻ የግብ ክልል የላካት ኳስ አዲስ ግደይ እና ግብ ጠባቂው ወንደሰን ገረመውን ፊት ለፊት ስታገናኝ ወንደሰን ገረመው በሳጥን ውስጥ አዲስ ግደይ ላይ በሰራው ጥፋት ምክኒያት ፌደራል ዳኛ ሚካኤሌ አርአያ የፍፁም ቅጣት ምት ለሲዳማ ቡና ሰጥተዋል፤ የፍ/ቅጣት ምቱንም ራሱ አዲስ ግደይ ወደግብ በመቀየር የሲዳማ ቡናን መሪነት አጠናክሯል።
ከዚህ በኋላ ወላይታ ድቻዎች የግብ ልዩነቱን ለማጥበብ የተንቀሳቀሱ ሲሆን በ75ኛው ደቂቃም ከቀኝ መስመር አምረላ ደልታታ ያሻገረውን ኳስ ዳግም በቀለ በግንባሩ ገጭቶ በማስቆጠር ቡድኑ እንዲነቃቃ አድርጓል። ድቻዎች በቀሪ ደቂቃዎች ጫና ፈጥረው በመጫወት ግብ ለማስቆጠር ጥረት ቢያደርጉም ያገኙዋቸውን የግብ ዕድሎች በአግባቡ መጠቀም አልቻሉም። ባለሜዳዎቹ ሲዳማ ቡናዎችም ግባቸውን በድጋሚ ሳያስደፍሩ ውጤታቸውን አስጠብቀው ጨዋታውን 3-1 አሸናፊነት ተወጥተዋል።
የዓመቱ የመጀመሪያ ሶስት ነጥቡን ያሳካው ሲዳማ ቡና ከወራጅ ቀጠናው በመውጣት በ8 ነጥቦች 11ኛ ደረጃን ሲይዝ በውጤት ቀውስ ውስጥ የሚገኘው ወላይታ ድቻ በአንፃሩ በ5 ነጥብ እና በ6 የግብ ዕዳ የደረጃ ሰንጠረዡ ግርጌ ላይ ተቀምጧል።
የአሰልጣኞች አስተያየት
አለማየሁ አባይነህ – ሲዳማ ቡና
“ባለፈው ጨዋታ በሰፊ ጎል ተሸንፈን መጥተን አሁን ማሸነፍ በመቻላችን ደስ ብሎኛል። በጥቃቅን ስህተቶች ነበር የምንሸነፈው እና ነጥብ የምናጣው እንጂ ቡድኑ አቅም አለው። ዛሬ ግን ወስነን ገብተን አሸንፈናል፤ ይህም የልጆቼን ቁርጠኝነት ያሳያል። ከዚህ በፊትም ቡድናችን በእንቅስቃሴ የተሻለ ነው። በአዲስ መንፈስ በአዲስ አስተሳሰብ ገብተን የተነጋገርነውን ተግባራዊ አድርገውልኛል።”
መሳይ ተፈሪ – ወላይታ ድቻ
” በመጀመሪያው አጋማሽ እነሱ ጥሩ ነበሩ። በሁለተኛው አጋማሽ ግን እኛ የተሻልን የነበርን ቢሆንም ተሸንፈን ወጥተናል። ያሰብነውን ማግኝት አልቻልንም። ሁልጊዜ ግን ማሰብ ያለብን ጉድለታችን ምንድነው ብለን ሰርተን መለወጡን ነው። ነገ ደግም አሸንፈን እንደምንመለስ አልማለው። ጉዳቶች አሉብን፤ ነገር ግን መደናገጥ የለብንም። ነገ አሸንፈን ወደ ላይ ከፍ እንላለን። በቀጣይ የተሻለውን ዲቻ ጠብቁ። ጃኮ አራፋት ጉዳት ስላለበት አስቀድመን ማስገባትም አልቻልንም፤ እሱ ሲገባ ጥሩ ነበርን። በሱ ላይ ብቻ ጥገኛ መሆን ግን የለብንም።
“አንደኛም ሆንኩ መጨረሻ ጫና አይኖርብኝም፤ የስራው ባህሪ ነው ብዬ አስባለሁ፡፡ ይህ ሽንፈት ለነገ ኃይል ይሆነኛል።”

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *