ሀድያ ሆሳዕና አንድ ተጫዋች ሲያስፈርም ሁለት ተጫዋቾችን ለመቀላቀል ተስማማ

በአሰልጣኝ ዮሐንስ ሳህሌ መሪነት የቅድመ ውድድር ዝግጅቱን እየከወነ የሚገኘው ሀድያ ሆሳዕና የአንድ ተጫዋች ዝውውር ሲቋጭ ሁለቱን ለማስፈረም ከጫፍ ደርሷል።

ለ2016 የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የቅድመ ውድድር ዝግጅቱን በክለቡ መቀመጫ ከተማ በሆነችው ሆሳዕና በአሰልጣኝ ዮሐንስ ሳህሌ እና ረዳቶቹ መሪነት እያከናወኑ የሚገኙት ሀድያ ሆሳዕናዎች የተጨማሪ ተጫዋችን ዝውውር ሲፈፅሙ በሙከራ እየተመለከቷቸው የነበሩ ሁለት ተጫዋቾችን ለማስፈረም ስለመቃረባቸው ሶከር ኢትዮጵያ መረጃ ደርሷታል።

ወጣቱ የተከላካይ ስፍራ ተጫዋች ፍቅረአብ ፀጋዬ ለክለቡ ፊርማውን በይፋ አኑሯል። ከዚህ ቀደም በሀድያ ሆሳዕና እና በቅዱስ ጊዮርጊስ ወጣት ቡድን በመቀጠል በአንደኛ ሊግ ክለቦቹ ሀድያ ሌሞ እና ዱከም ከተማ የተጫወተው ተከላካዩ በክረምቱ በሆሳዕና ከተማ ሲደረግ በነበረው ያሆዴ ዋንጫ ላይ ጥሩ ብቃትን ማሳየቱን ተከትሎ ክለቡን ሊቀላቀል ችሏል።

ቡድኑ የሙከራ ዕድል ሰጥቷቸው የነበሩ ሁለት ተጫዋቾችንም ለማስፈረም በእጅጉ ተቃርቧል። የቀድሞው የድሬዳዋ ከተማ ፣ ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ እና ፋሲል ከነማ የግራ መስመር ተከላካይ የሆነው ሳሙኤል ዮሐንስ የተጠናቀቀውን ዓመት በመድን ያሳለፈ ሲሆን በወልዋሎ ካሰለጠኑት አሰልጣኝ ጋር ዳግም የመገናኘቱ ነገር ዕርግጥ ሆኗል።

ሌላኛው ከጫፍ የደረሰው አማካዩ በየነ ባንጃው ነው። በአፍሮ ፂሆን ኮንስትራክሽን እና ኢትዮጵያ ቡና ወጣት ቡድን ውስጥ ከተጫወተ በኋላ በቀድሞው ኢኮስኮ እንዲሁም ያለፉትን ሁለት ዓመታት ከገላን ከተማ ጋር ጥሩ የውድድር ቆይታ ያደረገው ተጫዋቹ ሀድያን ለመቀላቀል ተቃርቧል።

ክለቡ በቢጫ ቴሴራም የመስመር አጥቂዎቹ ታምራት ወልደዮሐንስ እና ብፁዐን እንዳልካቸው የተባሉ ወጣቶችንም ማሳደጉ ተጠቁሟል።