ዮሴፍ ታረቀኝ ማክሰኞ ወደ ሰሜን አፍሪካዊቷ ሀገር ያቀናል

የአዳማ ከተማው የመስመር አጥቂ ማክሰኞ ወደ ሰሜን አፍሪካዊቷ ሀገር ግብፅ ለሙከራ እንደሚጓዝ ታውቋል።

የ2015 የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ተስፋ የተጣለበት ተጫዋቾች ዘርፍ አሸናፊ በመሆን ያጠናቀቀው ዮሴፍ ታረቀኝ የሙከራ ዕድል በማግኘቱ የፊታችን ማክሰኞ ዕኩለ ለሊት ላይ ወደ ግብፅ ለማቅናት ለጉዞው አስፈላጊ የሆነውን ቅድመ ሁኔታ ያጠናቀቀ መሆኑ ታውቋል።

ለዮሴፍ የአንድ ሳምንት የሙከራ ዕድል ያመቻቸለት የግብፁ አረብ ኮንትራክተር ክለብ ሲሆን የሚኖረው ቆይታ ስኬታማ ከሆነ ዝውውሩን ለማጠናቀቅ የተጫዋቹ ህጋዊ ባለቤት ከሆነው አዳማ ከተማ ጋር ክለቡ ንግግር የሚያደርግ መሆኑ ሲታወቅ። በጉዞው ዙርያ ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር አጭር ቆይታ ያደረገው ዮሴፍ ይህን ዕድል በማግኘቱ ደስተኛ መሆኑን ገልፆ “በሚኖረኝ የሙከራ ቆይታ የተሰጠኝን ዕድል ተጠቅሜ ሀገሬን በግብፅ ምድር ከፍ ለማድረግ ከፈጣሪ ጋር የምችለውን ሁሉ አደርጋለው” ብሏል።

በ2012 አዳማ ተስፋ ቡድን የተቀላቀለው ዮሴፍ በተጠናቀቀው የውድድር ዓመት ወደ ዋናው ቡድን በማደግ ከአስራ አምስተኛ ሳምንት አንስቶ በመጀመርያ አስተላለፍ በመካተት ቡድኑን በማገልገል ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴ ያደረገ ሲሆን ስምንት ጎሎችን በማስቆጠር የቡድኑ ከፍተኛ ጎል አስቆጣሪ በመሆን ማጠናቀቁ ይታወቃል።

ሶከር ኢትዮጵያም ዮሴፍ በግብፅ የሚኖረውን የሙከራ ቆይታ አስመልክቶ ጉዳዩን እየተከታተለች የምታቀርብ መሆኑን ከወዲሁ ትገልፃለች።