ከድሉ በኋላ የፈረሰኞቹ አሠልጣኝ ምን አሉ?

የቅዱስ ጊዮርጊሱ ዋና አሠልጣኝ ዘሪሁን ሸንገታ ቡድናቸው ኬኤምኬኤም’ን በድምር ውጤት 5ለ2 አሸንፎ ወደ ቀጣዩ ዙር ካለፈ በኋላ ተከታዩን አስተያየት ሰጥተዋል።

ስለተለያዩት የሁለቱ አጋማሽ እንቅስቃሴ…

የመጀመርያው አጋማሽ እና ሁለተኛ አጋማሽ ብዙ ልዩነት አለው። መጀመርያው አጋማሽ ትኩረታችን አጥተን ነበር፤ እቅዳችንን በትክክል አልተገበርንም ነበር። ጎልም ተቆጥሮብናል፤ ማስተካከል የነበረብን ነገሮች አስተካክለን ጥሩ ውጤት ይዘን ወጥተናል።

ስለቀጣይ ተጋጣሚያቸው…

የሚቀጥለው ተጋጣምያችን ከባድ ነው። የአካል ብቃታችንም ገና ነው። ወደ ጥሩ ብቃት ለመምጣት ጊዜ ያስፈልገናል። ማድረግ ያሉብን ስራዎች አሉ፤ ጨዋታዎች ያስፈልጉናል። አሁን ትልቁ ችግር ብሄራዊ ቡድኑ ኢንተርናሽናል ጨዋታ አለበት፤ ስብስባችን እየጠበበ ነው የሚሄደው። ወጣቶች ላይ ነው ልንሰራ የምንችለው፤ ብሄራዊ ቡድን ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ይገባሉ ስንት ተጫዋቾች እንደሚሄዱብን አናውቅም። ግን ጠንክረን ሰርተን ለቀጣይ ጨዋታ ከዚህ በተሻለ ለመቅረብ እንሰራለን።

ስላደረጉት እንቅስቃሴ…

ጨዋታው ቅዱስ ጊዮርጊስ የሚገልፅ ብዙ ፍጥነት የነበረው አልነበረም። ግን ያንን ለማድረግ ምን ያስፈልጋል ነው፤ ቅድም ገልጬዋለው የአካል ብቃታችን ገና ነው በተጨማሪም ከመጀመርያው ጨዋታ በኋላ ለሦስት ቀን ነው ልምምድ የሰራነው። ከዚህ በላይ መጠበቅ አልነበረብንም፤ እንደውም በሁለተኛው አጋማሽ የተሻለ ነገር አድርገን ብዙ ዕድሎች ስተናል። የጊዮርጊስ መገለጫ የሆነውን ፈጣን ጨዋታ አድርጎ ጫና መፍጠር አላደረግንም። የተጫዋቾቼ የአካል ብቃት ሁኔታ ገና ነው፤ በአስራ አምስት ቀን ነው ሁለት ጨዋታ ያደረግነው በሜዳችም እና ከሜዳችም ውጭ ብዙ ነገር ይጠብቀናል። ከዛ ውጭ በብሄራዊ ቡድን ምክንያት መቆራረጦች ይኖራሉ፤ ከዛ በተጨማሪ ስብስባችን ጠባብ ነው። እነዚን ነገሮች አቻችለን የተሻለ ነገር እናደርጋለን። ግን በሁለቱም አጋማሾች አንድ አልነበርን፤ በመጀመርያው አጋማሽ ትኩረታችንም አናሳ ነበር በሁለተኛው አጋማሽ ግን ማድረግ ያለብንን ነገር አድርገን ከመመራት ተነስተን አሸንፈን ወጥተናል።

ስለተጋጣሚ ቡድን አጨዋወት…

ቡድኑ ተመሳሳይ ነው የሚጫወተው። እዛም እንደዚ ነው የተጫወትነው፤ እንደውም በሜዳቸው በመጀመርያው አጋማሽ ላይ ጫና ለመፍጠር አልሞከሩም። አሁን ግን ከመጀመርያው አጋማሽ ጫና ለመፍጠር ሞክረዋል ኳስም አግኝተዋል። እኛ ግን በመጀመርያው ትኩረታችን አናሳ ነበር፤ ከዛ ግን ታክቲካሊ ነገሮች እና ትኩረታችን አስተካክለን ውጤት ይዘን ወጥተናል። ተጋጣምያችን አጨዋወት ግን ይሄ ነው የተለወጠ ነገር የለውም።

ስለአዳዲስ ተጫዋቾች እንቅስቃሴ…

ስብስቡ እንዳያችሁት በጣም ጠባብ ነው። ወጣቶችን አሁን ካላስገባም ነገ ማግኘት አልቻልንም። ትልቁ ኢትዮጵያዊያን ግብ ጠባቂዎች እንዲጫወቱ ፈልገን ነው ወደፊት ኃይል ለመጨመር ከፊት ዜጎች ያመጣነው። አጥቂው ብዙ ነገር አላረገም ግን አሁን ላይ ይሄ ነው ብዬ መናገር የምችለው ነገር አይደለም። ጊዜ አግኝቶ ከቡድኑ ጋር ተዋህዶ የተሻለ ነገር ማድረግ ከቻለ አለ። ግን ጥሩ አቅም ስላለው ነው ቡድናችንን የተቀላቀለው። ይሄንን የምናየው ጨዋታዎችን በደንብ ሲያደርግ ነው። ዛሬ ጥሩ አይደለም ማለት ነገም ጥሩ አይሆንም ማለት አይደለም። ተጫዋቾቼ ላይ መስራት የምችለውን ሁሉ ሰርቼ የራስ መተማመናቸውን ከፍ አድርጌ እንዲጫወቱ ነው የምፈልገው። እንዳልኩት ስብስባችን በጣም ጠባብ ነው። አሁንም በሀገራችን ገበያ የተሻሉ ተጫዋቾችን ካገኘሁ አስፈርማለው። በየትኛው ቦታ እና ለቅዱስ ጊዮርጊስ የሚመጥነውን ተጫዋች ማሰብ ያስፈልጋል።

ጨዋታው ሲጠናቀቅ ጉዳት ስላስተናገደው አማኑኤል ተረፉ…

አማኑኤል የተጎዳው ጠንከር ያለ ጉዳት አይደለም። አዙሮት ነው የወደቀው። ከባድ ነገር ነው ብዬ አላስብም። ቅድም እንዳልኩት ማች ፊትነሳችን ብዙ ይቀረዋል። በተጨማሪም የመጫወቻ ሜዳው በጣም ከባድ ነው። እነዚህ ነገሮች ተደራርበው ይሆናል ያዞረው ብዬ አስባለው።