ከፍተኛ ሊግ | ሀላባ ከተማ አዲስ አሰልጣኝ ሾሟል

በከፍተኛ ሊጉ ረዘም ባሉ ዓመታት ተሳትፎው የሚታወቀው ሀላባ ከተማ የአዲስ አሰልጣኝ ቅጥር ቋጭቷል።

ሀላባ ከተማ በኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ውድድር ላይ ረዘም ያሉ ዓመታቶችን በተሳታፊነት አሳልፏል። በውድድሩ ላይ ወደ ሀገሪቱ ትልቁ የሊግ ዕርከን ለማደግ በተደጋጋሚ ከጫፍ እየደረሰ ሲመለስ በተደጋጋሚ የምናየው ክለቡ የተጠናቀቀውን ዓመት በራህመቶ መሐመድ እየተመራ በምድብ አንድ 6ኛ ደረጃን በመያዝ ያጠናቀቀ ሲሆን በ2016 የውድድር ደግሞ በተሻለ ሆኖ ለመገኘት እና በፕሪምየር ሊጉ ላይ ለመታየት ዕቅድ በመያዝ አዲስ አሰልጣኝ ስለ መቅጠሩ ክለቡ ለዝግጅት ክፍላችን አሳውቋል። እስማኤል አቡበከር ደግሞ የክለቡ አዲሱ አሰልጣኝ ሆኗል።

ከዚህ ቀድሞ አዲስ አበባ ከተማን ወደ ፕሪምየር ሊጉ ማሳደግ የቻለው እና በተወሰኑ ጨዋታዎች ላይ ክለቡን በፕሪምየር ሊጉ የመራው እስማኤል የተጠናቀቀውን የውድድር ዘመን ኮልፌ ቀራኒዮን ሲመራ ቆይቶ ቀጣዩ ክለቡ ደግሞ ሀላባ ከተማ መሆኑ ታውቋል።