የፕሪምየር ሊግ ዝግጅት የሚጀምረው የመጨረሻው ክለብ ሀምበሪቾ ሆኗል

በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ፕሪምየር ሊጉ ያደገው ሀምበሪቾ ዱራሜ ወደ ዝግጅት ሊገባ ነው።

በተጠናቀቀው የከፍተኛ ሊግ ውድድር ላይ ሲሳተፍ ቆይቶ በአሰልጣኝ ደጉ ዱባሞ መሪነት ወደ ሊጉ ማደግ የቻለው ሀምበትቾ በክረምቱ የዝውውር መስኮት አስቀድሞ የአሰልጣኙን ውል ካራዘመ በኋላ በመቀጠል ከከፍተኛ ሊግ ክለቦች ማናዬ ፋንቱ ፣ ንጋቱ ጎዴቦ ፣ አፍቅሮት ሰለሞን ፣ አብዱሰላም የሱፍ እና የኋላሸት ሰለሞንን ሲያስፈርም የጥቂት ነባሮች ውልም ሲያራዝም እንደነበር በተከታታይ ዘገባችን መግለፃችን ይታወሳል።

ከፋይናንስ እና ተያያዥ ጉዳዮች ጋር ወደ ቅድመ ውድድር ዝግጅት መግባት ሳይችል እንደቀረ ሲሰማ የነበረው ክለቡ በቀጣዮቹ ቀናት የፕሪምየር ሊግ ልምድ ያላቸውን ተጫዋቾች ጨምሮ ውላቸው የተጠናቀቁትንም ከማስፈረሙ አስቀድሞ ከዛሬ ጷጉሜ 2 ጀምሮ በሀዋሳ ከተማ ሐብል ሆቴል መቀመጫውን በማድረግ ከነገ ጀምሮ በይፋ ዝግጅት እንደሚጀምር ለማወቅ ተችሏል።