ኃይቆቹ ጋናዊ አማካይ አስፈርመዋል

ሀዋሳ ከተማዎች ጋናዊ የተከላካይ አማካይ ወደ ስብስባቸው ቀላቅለዋል።

በአሰልጣኝ ዘርዓይ ሙሉ መሪነት የቅድመ ውድድር ዝግጅታቸውን እየሰሩ የሚገኙት ሀዋሳ ከተማዎች እስከ አሁን በስብሰባቸው ውስጥ የሀገር ውስጥ አዳዲስ ተጫዋቾች በማስፈረም እና ነባሮችን በመያዝ ልምምዳቸውን ቀጥለዋል። አሁን ደግሞ የመጀመሪያ የውጪ ዜጋ ፈራሚያቸው በማድረግ ጋናዊውን የተከላካይ አማካይ ስፍራ ተጫዋቹን ሚካኤል ኦቶውን በይፋ ስለ ማስፈረማቸው ሶከር ኢትዮጵያ ያገኘችው መረጃ አመላክቷል።

አብዛኛዎቹ የእግር ኳስ ህይወቱን በሀገሩ ክለቦች ዩኒ ስታር ፣ ኢንተር አላይንስ እና ግሬት ኦሎምፒክስ ከተጫወተ በኋላ በመቀጠል ወደ ፓርቹጋል አምርቶ ለፖርትሞኔንሴ ተጫውቷል። ያለፉትን ሁለት ዓመታት ወደ ሀገሩ ጋና በመመለስ ለሊጎን ሲቲስ ግልጋሎት ሲሰጥ የነበረ ሲሆን ለቀጣዩ የውድድር ዘመን ደግሞ ወደ ሀገራችን በመምጣት ሀዋሳን ተቀላቅሏል።