“ጉዟችንን ለማደናቀፍ እየሰሩ ነው።” አቶ ልዑል ፍቃዴ

በካፍ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ላይ እየተሳተፈ የሚገኘው ባህር ዳር ከተማ ወደ ቱኒዚያ የሚያደርገው ጉዞ መስተጓጎል ገጥሞታል።

በታሪኩ ለመጀመሪያው ጊዜ በአህጉራዊ ውድድር እየተካፈለ የሚገኘው ባህር ዳር ከተማ የመጀመርያውን ዙር ማጣሪያ የታንዛኒያውን አዛም በደርሶ መልስ ውጤት በማሸነፍ ወደ ሁለተኛው አልፎ በሁለተኛው ዙር ከቱኒዚያው ክለብ አፍሪካ ጋር በአዲስ አበባ ያደረገውን ጨዋታ ሁለት ለምንም በመርታት ወደ ቀጣይ ዙር ለማለፍ ዕድሉን አስፍቶ መውጣቱ ይታወሳል። የፊታችን እሁድ መስከረም 20 ቀን ቱኒዚያ ላይ የመልሱ ጨዋታ የሚያደርገው ቡድኑ ዝግጅቱን እያደረገ ሲገኝ ወደ ቱኒዚያ የሚያደርገው ጉዞ የተለያዩ መስተጓጉሎች እየገጠመው መሆኑን አስመልክቶ የክለቡ ሥራ አስኪያጅ አቶ ልዑል ፍቃዴ ለሶከር ኢትዮጵያ ተከታዩን ሀሳብ ሰጥተዋል።

“ አስቀድመን የቪዛውን ጉዳይ ለመጨረስ ባሳለፍነው ሳምንት ነበር የሚሄደውን የልዑካን ቡድን ዝርዝር ለቱኒዚያ ኤንባሲ ፓስፖርት አዘጋጅተን ክፍያ ከፍለን ያስገባነው። ዛሬ በቀጠሯችን መሰረት ቪዛውን ለመቀበል ብንሄድም አንድ ሰው ብቻ ነው ያለን ቪዛው አልደረሰንም አሉን። እኛ ደግሞ የመጀመርያው ልዑክ ረቡዕ ነው የሚሄደው የቀረው ደግሞ ሐሙስ ነው ተጠቃሎ የሚገባው። ለምድነው በቀጠሯችን መሰረት የማትሰጡን ስንላቸው ምክንያታቸው አሳማኝ አይደለም። አሁን ቪዛውን መቼ እንደሚሰጡን እርግጠኛ መሆን አልቻልንም። ባንክ ደግሞ ቪዛውን አይቶ ነው ዶላር የሚሰጠን ነገ ቀጠሮ ሰጥቶናል። ነገ ዶላሩን መቀበል ካልቻልን ረቡዕ እና ሐሙስ በበዓል ምክንያት ሥራ ዝግ ነው። ዶላር ካላገኘን ደግሞ እንጓዝም ይህ ደግሞ ጉዟችን ይቀራል ማለት ነው። ለምንድነው የምታጉላሉን ሆን ብላቹሁ ጉዟችንን ለማደናቀፍ እየሰራቹ ነው። ብለን ከኤንባሲ ወጥተናል። ይህ ያጋጠመንን ችግር የሚመለከተው አካል አፋጣኝ መፍትሄ ይስጠን እንላለን።”

– በጉዳዩ ላይ ምላሽ ለሚሰጥ አካል ሶከር ኢትዮጵያ በሯ ክፍት መሆኑን ለመግለፅ እንወዳለን።