ሐበሻ ቢራ ከኢትዮጵያ ቡና ጋር የአጋርነት ስምምነቱን አድሷል

ያለፉትን 12 ዓመታት የኢትዮጵያ ቡና ስፖንሰር በመሆን ከክለቡ ጋር አብሮ የዘለቀው ሐበሻ ቢራ ለተጨማሪ ሦስት ዓመታት የሚያቆየውን ስምምነት ፈፅሟል።

ዛሬ ቤስት ዌስተርን ሆቴል በተካሄደው በስምምነት ፊርማ ሥነ ስርዓት ላይ የክለቡ ፕሬዝደንት መቶ አለቃ ፍቃደ ማሞ ፣ ሥራ አስኪጁ አቶ ገዛኸኝ ወልዴ እንሲሁም በሐበሻ ቢራ በኩል ማርኬቲንግ ዳሬክተሩ አቶ እዮብ ኃይሉ እና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተውበታል።

በስምምነቱ የተቀመጡ ዋና ዋና ነጥቦች

– ሐበሻ ቢራ በየዓመቱ ሃያ ሁለት ሚሊዮን ሁለት መቶ ሺ ብር የሚከፍል ይሆናል።

– ከዚህ በፊት ቃል ተገብቶ ያልተፈፀመው ለዋናው ቡድን ግልጋሎት የሚሆን ዘመናዊ አውቶብስ ግዢ በ20,300,000 ሚሊዮን ብር የሚገዛበት ሁኔታ ይመቻቻል።

– የክለቡን አቅም በዘላቂነት ለማሳደግ የገቢ ምንጭ ሚገኝባቸው የተለያዩ ፕሮጀክቶች ለመስራት አምስት ሚልዮን በላይ ብር በጋራ የተለያዩ ሥራዎችን የሚሰሩ ይሆናል።

– በተለየ ሁኔታ ደግሞ ኢትዮጵያ ቡና የ2016 የውድድር ዘመንን አሸናፊ ሆኖ የሚያጠናቅቅ ከሆነ አስር ሚሊዮን ብር በሽልማት መልክ ለመስጠት መታሰቡን በስምምነቱ ወቅት የተገለፀ ሲሆን በኢትዮጵያ ቡና በኩል ሐበሻ ቢራን ክለቡ በዋናው ቡድን እና የሴቶቹ ቡድን በማልያ ላይ ያስተዋውቃል ፣ ኢትዮጵያ ቡና በሚያደርጋቸው ጨዋታዎች ላይ የሀበሻን ሎጎ ማስተዋወቅ እና በተጨማሪም በሚያዘጋጃቸው የተለያዩ ፕሮግራሞች ሐበሻ ቢራን የማስተዋወቅ ሥራ የሚሰራ ይሆናል።