የቀድሞ የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌደሬሽን ምክትል ፕሬዝዳንት ወደ ፌደሬሽኑ ይመለሱ ይሆን ?

ከዚህ ቀደም በኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ሥራ አስፈፃሚነት ያገለግሉት ግለስብ ዳግም ለዕጩነት ቀርበዋል።

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ጥቅምት 18 ከሚያካሄደው ጠቅላላ ጉባዔ ጎን ለጎን የፌዴሬሽኑ የማሟያ ምርጫ እንደሚያካሄድ መግለፁ ይታወሳል።

በተለያየ ምክንያት መሳተፍ ያልቻሉት ሦስቱ ክልሎች ማለትም አፋር ፣ ትግራይ እና ነሀሴ 22 2014 የፌደሬሽኑ አባል የሆነው የደቡብ ምዕራብ ክልል በምርጫው የሚሳተፉ ዕጩዎች በማቅረብ ላይ ይገኛሉ። ከነዚህ ውስጥም የቀድሞ የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌደሬሽን ምክትል ፕሬዝዳንት እና የደደቢት እግርኳስ ክለብ መስራች የሆኑት ኮሎኔል ዐወል አብዱራሂም ትግራይ ክልልን ወክለው እንደሚሳተፉ ተረጋግጧል።

ይህንን ተከትሎም ላለፉት ዓመታት ከእግርኳስ ርቀው ከቆዩ በኋላ ዳግም ወደ እግርኳሱ የሚመለሱበት ዕድል ተፈጥሯል። በዚህኛው ምርጫ የሚመረጡ ከሆነም ዳግም ወደ ፌደሬሽኑ ይመለሳሉ። በ2011 በሰመራ በተካሄደው ምርጫ ተሳትፈው የፌደሬሽኑ ምክትል ፕሬዝዳንት ሆነው ሲያገለግሉ የቆዩ ሲሆን ከ2012 በኋላ ደግሞ በሥራ ገበታቸው ላይ አልነበሩም። በታህሳስ 23 2014 በአርባምንጭ ከተማ በተካሄደው 13ኛ ጠቅላላ ጉባዔ ላይም በአቶ አበበ ገላጋይ መተካታቸው ይታወሳል። የትግራይ ክልል ከኮሎኔል አወል አብዱራሂም በተጨማሪ ኢንስትራክተር ህይወት አረፋይኔ እና አቶ አስፋው ፀጋይን በዕጩነት አቅርቧል።

በተያያዘ ዜናም ፌደሬሽኑ ያስቀመጠው የዕጩዎች ማቅረቢያ ቀነ ገደብ በዛሬው ዕለት መስከረም 22 ከቀኑ 10:00 የሚጠናቀቅ ሲሆን ተቋሙ ከቀናት በፊት ባሳወቀው መሰረት ክልሎች እስከ ዛሬ ድረስ በድጋሚ የተሟሉ የዕጩዎች ሰነድ እንዲያቀርቡ አስገንዝቧል።