ከ20 ዓመት በታች የማጣሪያ ሁለት ጨዋታዎች ላይ ኢትዮጵያዊያን ዳኞች ተመድበዋል

አምስት ኢትዮጵያውያን ዕንስት ዳኞች በአፍሪካ ዞን የዓለም ከ20 ዓመት በታች የሴቶች ዋንጫ የማጣሪያ ጨዋታን ይመራሉ።

የዓለም ከ20 ዓመት በታች ሴቶች ዋንጫ በኮሎምቢያ አስተናጋጅነት ይከናወናል። በዚህ የውድድር መድረክ ላይ ለመሳተፍ ሀገራት የማጣሪያ ጨዋታዎችን የሚያከናውኑ ሲሆን በአህጉረ አፍሪካ  የሚገኙ ሀገራትም በዚህ ውድድር ላይ ለመካፈል የማጣሪያ መርሐ-ግብራቸውን ዛሬ ይጀምራሉ። ሀገራችን ኢትዮጵያ ኢኳቶሪያል ጊኒን ከሜዳዋ ውጪ ዛሬ የምትገጥም ሲሆን አምስት የሀገራችን ዳኞች ደግሞ በሁለት ጨዋታዎች ላይ በዳኝነት እንዲያገለግሉ ስለ መመረጣቸው ሶከር ኢትዮጵያ ያገኘችው መረጃ አመላክቷል።

ሞዛምቢክ ማፑቶ ላይ ዛሬ 10፡00  ሞዛምቢክ በሜዳዋ ዩጋንዳን ስትገጥም የብሩንዲ ዜግነት ያላቸው ዳኞች በዋና እና በረዳት ዳኝነት ጨዋታውን ሲመሩ ሊዲያ ታፈሰ አሁንም እስከ ታህሳስ ወር የፊፋ ባጅ ስላላት በሚል አሁንም በድጋሚ በአራተኛ ዳኝነት እንድትመራ ስትመረጥ በነገው ዕለት ዕሁድ ደግሞ ናይሮቢ ላይ ከቀትር መልስ 09፡00 ኬኒያ በሜዳዋ አንጎላን ስትገጥም ፀሐይነሽ አበበ በዋና ዳኝነት ይልፋሸዋ አየለ እና ወጋየሁ ዘውዴ በረዳትነት ሲሳይ ራያ በበኩሏ በአራተኛ ዳኝነት በጋራ እንዲመሩት ተመድበዋል።