በሁለቱ ተጫዋቾች ዙርያ ፌዴሬሽኑ ውሳኔ አሳልፏል

በአርባምንጭ ከተማ እና በሁለቱ ተጫዋቾች ዙርያ የተፈጠረውን ውዝግብ አስመልክቶ ፌዴሬሽኑ ውሳኔውን አሳውቋል።

ከዚህ ቀደም ባቀረብነው ዘገባችን እንዳልካቸው መስፍን እና አሸናፊ ፊዳ ‘ነሐሴ 30 2015 ከአርባምንጭ ከተማ ጋር ያለው ውላችን የተጠናቀቀ በመሆኑ ለቅዱስ ጊዮርጊስ ለመጫወት ከስምምነት በመድረሳችን ፌዴሬሽኑ ውላችንን ያፅድቅልን’ በማለት ጥያቄያቸውን አቅርበዋል። አርባምንጭ ከተማ በበኩሉ ‘እስከ ነሐሴ 30 2016 ድረስ በክለቡ የሚያቆያቸውን አዲስ ስምምነት አድርገዋል ፤ ስለሆነም የተጫዋቾቹ ህጋዊ ባለቤት እኔ ነኝ’ በማለት ቅሬታውን ለፌዴሬሽኑ አቅርቧል።

የሁለቱን አካለት አቤቱታ ሲመረምር የቆየው የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን በዛሬው ዕለት በደብዳቤ ውሳኔ አሳልፏል። በዚህም መሠረት ክለቡ የእንዳልካቸው መስፍን እና አሸናፊ ፊዳን ውል በክልል ደረጃ ማፀደቁን የደቡብ እግርኳስ ፌዴሬሽን በቀን 23 12 2015 በፃፈው ደብዳቤ ማሳውቁን ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ጠቁሟል። ይኸውም የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን በክልል ደረጃ ተጫዋቾች እና አሰልጣኞች ውል እንዳያፀድቁ በሰርኩላር ከማሳወቁ በፊት የሆነ መሆኑ በፌዴሬሽኑ ተረጋግጧል። እንዲሁም ፌዴሬሽኑ ባደረገው ማጣራት አዲስ በተዋዋሉት ውል ደመወዝ እና ተጨማሪ ጥቅማጥቅም ሲከፈላቸው መቆየቱን በማስታወቅ የተጫዋቾቹን ህጋዊነት ፌዴሬሽን አምጥተው እንድያፀድቁ አሳስቦ ሁለቱ ተጫዋቾች የአርባምንጭ ከተማ መሆናቸውን በመግለፅ ወደ ክለቡ እንዲመለሱ ወስኗል።

የተጫዋቾቹ ህጋዊ ጠበቃ እንዳደረሱን መረጃ ከሆነ በውሳኔው ዙርያ ይግባኝ እንደሚጠይቁበት ለሶከር ኢትዮጵያ ገልፀዋል።