​የእንቦጭ አረምን ከጣና ሀይቅ የማጥፋት ዘመቻ አካል የሆኑ ጨዋታዎች በባህርዳር ተካሄዱ

በጣና ሐይቅ ላይ የተከሰተው እንቦጭ መጤ አረም በሐይቁ ላይ እያደረሰ ያለውን ጉዳት ለመቅረፍ እና ግንዛቤ ለመፍጠር  ታስቦ የተዘጋጀው የገቢ ማሰባሰቢያ የወዳጅነት ጨዋታ በቅዱስ ጊዮርጊስ ፣ ፋሲል ከተማ ፣ ባህርዳር ከተማ እና አውስኮድ መካከል ተደርጓል፡፡

በተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ላይ የሚሰራው ሶሳይቲ ፎር ኢኮ ቱሪዝም ኤንድ ባይ ዳይቨርሲቲ ኮንሰርቬሽን የበጎ አድራጎት ማህበር አዘጋጅነት በተካሄደው በዚህ ውድድር በጎ አላማውን ለመደገፍ የባህርዳር ዩኒቨርስቲ ስታድየም ተመልካች ከመያዝ አቅሙ በላይ እጅግ በርካታ የስፖርት ቤተሰብ ታድሟል፡፡ በዛሬው ጨዋታ ከጨዋታው አስቀድሞ የተለያየ የግንዛቤ ማስጨበጫ መልዕክቶች የተከናወኑ ሲሆን በተለይ ከዛሬ ስድስት አመት በፊት በጣና ሐይቅ ላይ የእንቦጭ አረም መከሰቱን በሳይንሳዊ ምርምር ያገኙት እና የችግሩን አሳሳቢነት ከግምት በማስገባት አረሙን ለማጥፋት ከፍተኛ ስራ የሰሩት ዶ/ረ አያሌው ወንዴ የግንዛቤ ማስጨበጫ ንግግር አድርገዋል።

አስቀድሞ 08:00 ላይ በሁለቱ የከፍተኛ ሊግ ተሳታፊ ቡድኖች በሆኑት ባህርዳር ከተማ እና አውስኮድ መካከል በተደረገው ጨዋታ አውስኮድ ከመመራት ተነስቶ 2 – 1 ሲያሸንፍ የአውስኮድን የድል ጎሎች ከእረፍት መልስ አብዱልከሪም ሳዲቅ እና ሰለሞን ጌዲዮን አስቆጥረዋል፡፡ ባህርዳር ከተማን ከሸንፈት ያላዳነውን ብቸኛ ጎል ደግሞ በፍጹም ቅጣት ምት ፍቃዱ ወርቁ አስቆጥሯል ።

ፋሲሎች ጎል ካስቆጠሩ በኋላ አረም የመንቀል እንቅስቃሴ በማሳየት ደስታቸውን ገልጸዋል

በመቀጠል 10:00 ላይ በአስገራሚ የደጋፊ ድበብ ታጅቦ ሞቅ ብሎ በጀመረውና በሁለቱ የኢትዮዽያ ፕሪምየር ሊግ ተሳታፊ በሆኑት ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ፋሲል ከተማ መካከል በተካሄደው ጨዋታ ቅዱስ ጊዮርጊስ 3-1 አሸንፏል፡፡ በኤርሚያስ ኃይሉ አማካኝነት አፄዎቹ ቀዳሚ የነበሩ ቢሆንም ፈረሰኞቹ አበባው ቡጣቆ ፣ ደጉ ደበበ እና አዳነ ግርማ አከታትለው ባስቆጠሯቸው ጎሎች አሸናፊ ሆነዋል፡፡
እጅ የተሳካ በነበረው የዛሬ የበጎ አድራጎት የወዳጅነት ጨዋታ ለታሰበለት አላማ የሚውል ከፍተኛ ገቢ መገኘቱ የተነገረ ሲሆን በተጨማሪ ተመሳሳይ እንዲህ ያሉ ፕሮግራሞች በቀጣይ እንደሚኖር አዘጋጅ ኮሚቴው ገልጿል፡፡  ነገ ከማለዳ አንስቶ የባህርዳር ከተማ እና የአካባቢው ነዋሪ ፣ የክለብ ደጋፊዎች በተገኙበት ችግሩ ወደተከሰተበት ጣና ሐይቅ በማምራት እንቦጭ አረምን የማስወገድ ዘመቻ እንደሚካሄድም ሰምተናል ።

ይህንን በጎ አላማ ለመደገፍ የቅዱስ ጊዮርጊስ ፣ የባህርዳር ከተማ ፣ የፋሲል ከተማ እንዲሁም የአውስኮድ ደጋፊዎች ለአላማው መሳካት ያሳዩት ተነሳሽነት አድናቆት የሚቸረው ተግባር ነው፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *