ከፍተኛ ሊግ | ሀላባ ከተማ አዳዲስ ተጫዋቾችን አስፈርሟል

የከፍተኛ ሊጉ ክለብ ሀላባ የዘጠኝ አዳዲስ ተጫዋቾችን ዝውውር ሲያጠናቅቅ የነባሮችን ውልም አድሷል።

በኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ላይ ዘለግ ያለ ተሳትፎ ያለው ሀላባ ከተማ ለዘንድሮው የውድድር ዘመን እስማኤል አቡበከርን የክለቡ አሰልጣኝ በማድረግ የቀጠረ ሲሆን አሁን ደግሞ ቡድኑ ራሱን ለማጠናከር ዘጠኝ አዳዲስ ተጫዋቾችን ሲያስፈርም የአራት ነባሮቹን ውል ደግሞ አራዝሟል።

ክለቡ ያስፈረማቸውን ስንመለከት የቀድሞው የስሑል ሽረ ፣ መቻል ፣ለገጣፎ ፣ ሀድያ ሆሳዕ እና ኤሌክትሪክ አጥቂ ልደቱ ለማ ፣ የቀድሞው የደቡብ ፖሊስ ሀዋሳ ከተማ እና ኮልፌ ግብ ጠባቂ ሀብቴ ከድር ፣ ከማል አቶም አማካይ ከገላን ከተማ ፣ ኦካይ ጁል አማካይ ከለገጣፎ ፣ ሙባረክ ጅላሎ ተከላካይ ከኮልፌ ፣ አሸናፊ በቀለ አማካይ ከአዲስ ከተማ ክ/ከተማ ፣ አሳልፈው መኮንን ተከላካይ ከደብረብርሃን ፣ ኤፌሶን በቀለ ተከላካይ ከየካ እና ሰለሞን የተባለን አማካይ ከአቃቂ ስለማስፈረሙ የደረሰን መረጃ አመላክቷል።

ከአዳዲስ ፈራሚዎች በተጨማሪ ክለቡ የኪሩቤል ማርቆስ ፣ ፎሳ ሰዴቦ ፣ ተስፋሁን ሰቦቅሳ እና አብዱልከሪም ራህመቶን ውል ለተጨማሪ ዓመትም አራዝሟል።