ቤቲካ ኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያ ቡና ውላቸውን አድሰዋል

ያለፉትን ሁለት ዓመታት በማስታወቂያ አጋርነት አብረው ሲሰሩ የነበሩት ቤቲካ ኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያ ቡና ቀሪ የሦስት ዓመት ውላቸውን እንደ አዲስ አድሰዋል።

የበርካታ ደጋፊዎች ባለቤት የሆነው ኢትዮጵያ ቡና ከ2014 ጀምሮ ከቤቲካ የስፖርት ውርርድ ተቋም ጋር የአምስት ዓመታት የማስታወቂያ አጋርነት ውል መፈራረሙ አይዘነጋም። ሁለቱ ተቋማት እስከ 2018 ድረስ የሚቆይ ውል ቢኖራቸውም የአከፋፈል እና የአፈፃፀም ሂደቱን እንደ አዲስ በመከለስ በዛሬው ዕለት በኢንተርሌግዠሪ ሆቴል ውላቸውን አድሰዋል።

በፊርማ ሥነ-ስርዓቱ ላይ ኢትዮጵያ ቡና ስፖርት ክለብን ወክለው ሥራ-አስኪያጁ አቶ ገዛኸኝ ወልዴ እንዲሁም ቤቲካ ኢትዮጵያን ወክለው ሥራ-አስኪያጁ አቶ አብርሃም ተክለማርያም ተገኝተዋል። በቅድሚያ ንግግራቸውን የጀመሩት አቶ አብርሃም በሚሊዮን የሚቆጠሩ ደጋፊዎች ካሉት ክለብ ጋር አብሮ በመስራታቸው ደስተኛ እንደሆኑ በመግለፅ ትጥቆች ላይ የተቋሙ ዓርማ እንደሚቀመጥ እንዲሁም በስታዲየም ውስጥ በሜዳ ዳር ማስታወቂያ የዕይታ ዕድል እንደሚያገኙ አመላክተዋል።

አቶ ገዛኸኝ በበኩላቸው ባለፉት ሁለት ዓመታት ሊጉ በነበረው የስያሜ መብት ምክንያት ቤቲካ ኢትዮጵያ ማግኘት የነበረበትን መብት እንዳላገኘ ጠቅሰው ከዚህ በኋላ ግን ይህንን አይነት ችግር እንደማይፈጠር ተናግረው መሰል ነገሮች ከመፈጠራቸው በፊት ከሊጉ የበላይ አካል ጋር እንደሚነጋገሩ እና የክለቡንም የአጋሮቻቸውንም መብት እና ጥቅም የሚነኩ ውሳኔዎችን እንደማይቀበሉ አፅዕኖት ሰጥተው ተናግረዋል።

በውሉ መሰረት በየዓመቱ ቤቲካ ለክለቡ የሚፈፅመው ክፍያ በንግግር የሚወሰን ቢሆንም ዘንድሮ ግን እንደ ዓምናው 6 ሚሊዮን ብር እንደሚከፈል ተገልጿል። አከፋፈሉ በፊት በሁለት ዙር የነበረ ሲሆን አሁን ግን በየወሩ እንደሚፈፀም ተያይዞ ተነግሯል።

በተለያዩ ማኅበራዊ ጉዳዮች ላይ ድጋፍ በማድረግ የሚታወቀው ቤቲካ ኢትዮጵያ በአፍሪካ በስምንት ሀገራት የስፖርት ውርርድ ስራዎችን በመስራት ላይ የሚገኝ ዓለም አቀፍ ድርጅት ሲሆን በየሀገራቱ ያሉ ትልልቅ ክለቦችን ስፖንሰር እያደረገ ራሱን እያስተዋወቀ ይገኛል።