መረጃዎች | 11ኛ የጨዋታ ቀን

ሦስተኛ ሳምንት ላይ የደረሰው የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ነገ በሚደረጉ ሁለት ጨዋታዎች ሲቀጥል ጨዋታዎቹን የተመለከቱ መረጃዎችን እንደሚከተለው አቅርበንላችኋል።

መቻል ከ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ

ተቀራራቢ የጨዋታ መንገድ ያላቸውን ሁለት ክለቦች የሚያገናኘው ተጠባቂው የዘጠኝ ሰዓቱ ጨዋታ የተመለከቱ መረጃዎች እነሆ!

ሀዲያን አሸንፈው በባህርዳር ከተማ ሽንፈት በማስተናገድ በሦስት ነጥቦች 9ኛ  ደረጃ ላይ የተቀመጡት መቻሎች በተከታታይ ጨዋታዎች ነጥብ ላለመጣል ከንግድ ባንክ ጋር ብርቱ ፉክክር ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል። መቻል ኳስን ተቆጣጥሮ ለመጫወት ጥረት የሚያደርግ እና በዋናነት በፈጣን ሽግግሮች ለማጥቃት የሚሞክር ቡድን ነው። በተለይም የሽመልስ በቀለና የከነአን ማርክነህ የሰመረ ጥምረት ለቡድኑ የማጥቃት ክፍል አስፈሪነት አላብሶታል። በሁለቱም ጨዋታዎች ያስቆጠሯቸው አራት ግቦችም ለጥንካሪያቸው ማሳያ ነው። አሰልጣኝ ገብረክርስቶስ ቢራራ በነገው ጨዋታም የተለወጠ አቀራረብ ይኖራቸዋል ተብሎ ባይገመትም ባለፈው ሳምንት እንደገለፅነው የቡድኑ ሚዛን ላይ ማስተካከያ ማድረግ ግድ ይላቸዋል። በየጨዋታው በአማካይ ሁለት ግቦች አስቆጥሮ ሁለት ግቦች ያስተናገደው ቡድናቸው ከውስን ማስተካከያ ባለፈ አጠቃላይ የቡድኑ የመከላከል አደረጃጀት ላይ ማስተካከያ ይሻል።


እስካሁን ድረስ ግብ ካላስተናገዱ ክለቦች ውስጥ አንዱ የሆኑት የኢትዮጵያ ንግድ ባንኮች ከሁለት ጨዋታዎች አራት ነጥቦች ሰብስበው 6ኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ። በነገው ዕለት ከመቻል ጋር በሚያደርጉት ጨዋታም ጥሩ ጅማሯቸውን ለማስቀጠል አልመው እንደሚገቡ እሙን ነው።

ለኳስ ቁጥጥር ብልጫ ቅድሚያ ካልሰጡት ሀዲያ ሆሳዕናና ይበልጥ ጥንቃቄ መርጠው ከቀረቡት አዳማ ከተማ ጋር ባደረጓቸው ጨዋታዎች በኳስ ቁጥጥር ላይ የተመሰረተ አጨዋወት ለመከተል የሞከሩት አሰልጣኝ በፀሎት በነገው ዕለት ግን ጠንካራ አማካዮች ካሉትና በተመሳሳይ ኳሱን ለመቆጣጠር ብርቱ ፍላጎት ከሚያሳየው መቻል የሚገጥማቸው ፈተና ቀላል እንደማይሆን ለመገመት አያዳግትም። አሰልጣኙ ከወዲሁ በነገው ጨዋታ የአጨዋወት ለውጥ ያደርጋሉ ወይስ አያደርጉም ለሚለው ለመገመት አዳጋች ቢሆንም እስካሁን ድረስ አንድ ግብ ብቻ ማስቆጠር የቻለው የማጥቃት አጨዋወታቸው ላይ ግን ማስተካከያ ማድረጋቸው አይቀሬ ነው። ቡድኑ በመጨረሻው ጨዋታ ላይ ከድር ኩሊባሊ በራሱ መረብ ላይ ባሳረፋት እና ለቡድኑ የመጨረሻ ደቂቃ መና በሆነችው ግብ ማሸነፉም ይታወሳል።

ንግድ ባንኮች ከጉዳትና ቅጣት ነጻ የሆነው ስብስባቸውን ይዘው ወደ ጨዋታው ሲቀርቡ በመቻል በኩልም በቅርቡ ልምምድ ከጀመረው ፍፁም አለሙ ውጭ ሙሉ ቡድኑ ለጨዋታ ዝግጁ ነው።

ሁለቱ ለክቦች መቻል ወደ ፕሪምየር ሊግ ካደገበት 1997 ንግድ ባንክ እስከወረደበት 2009 ድረስ 25 ጊዜ የተገናኙ ሲሆን መቻል 8 ጨዋታ በማሸነፍ ቀዳሚ ነው። ባንክ 5 ጊዜ ሲያሸንፍ የመጨረሻ ግንኙነታቸውን ጨምሮ 12 ጊዜ አቻ ተለያይተዋል። መቻል 34 ሲያስቆጥር ባንክ 30 አስቆጥሯል።

ኢንተርናሽናል ዳኛ ኃይለየሱስ ባዘዘው ይህንን ጨዋታ በዋና ዳኝነት ይመራል ፤ አማን ሞላ እና እሱባለው መብራቱ በረዳትነት ፤ ዮናስ ካሳሁንም በአራተኛ ዳኝነት ተመድበዋል።

ሀዋሳ ከተማ ከ ድሬዳዋ ከተማ

በሁለተኛው ሳምንት ጨዋታ ሻሸመኔ ከተማን አሸንፈው ሦስት ነጥብ ማሳካት የቻሉት ሀዋሳ ከተማዎች ከሁለት ጨዋታዎች አራት ነጥቦች ሰብስበውና በ 5ኛ ደረጃነት ተቀምጠው ወደ ነገው ጨዋታ ይቀርባሉ።

ባደረጓቸው ሁለት ጨዋታዎች ተገማች ያልሆነ ፣ ተቀያያሪ የጨዋታ መንገድ የተከተሉት ኃይቆቹ በጨዋታዎቹ የአጨዋወት ብቻ ሳይሆን የተጫዋቾች ሚናም ጭምር በመለወጥ ተገማች ያልሆነ አቀራረብ ተከትለዋል። አሰልጣኝ ዘርዓይ ሙሉም ይህንን አካሄድ እንደሚቀጥሉበት እና የተጫዋቾች ተለዋዋጭ ሚና  በልምምድ ሜዳም እንደሠሩበት መግለጻቸውም ይታወሳል።  ይህንን ተከትሎም የነገ አቀራረባቸውን ለመተንበይ እጅግ አዳጋች ቢሆንም በብዛት ሲተገብሩት የሚስተዋለው የፈጣን ሽግግር አጨዋወት ይከተላሉ ተብሎ ይገመታል። ከዚ በተጨማሪ ወሳኙ ተከላካያቸው በረከት ሳሙኤል ከቅጣት መልስ ማግኘታቸው ለቡድኑ ጥሩ ዜና ነው።


ካደረጓቸው ሁለት ጨዋታዎች ሦስት ነጥቦች ሰብስበው 11ኛ ደረጃ ላይ  የተቀመጡት ብርቱካናማዎቹ ከመጨረሻው ሳምንት ሽንፈት ለማገገም ኃይቆቹን ይገጥማሉ። ድሬዳዋ ከተማዎች ከኋላ ተነስተው ሀምበሪቾን ካሸነፉበት የመጀመርያው ሳምንት የሁለተኛ አጋማሽ ጨዋታ ጀምሮ ኤልያስ አሕመድ እና ኤፍሬም አሻሞን መሰረት ያደረገ የመስመር አጨዋወት ለመተግበር ቢሞክሩም ዘጠና ደቂቃ በወጥነት የመጫወት ችግር ይታይባቸዋል። ይህ ችግርም በሁለቱም ጨዋታዎች በጉልህ ተስተውሏል።

አሰልጣኝ አስራት አባተ የተጠቀሰውን ችግር ከመቅረፍ ባለፈ በመጨረሻው ጨዋታ ላይ በዛ ያሉ ንፁህ የግብ ዕድሎች መፍጠር ያልቻለው የአማካይ ክፍል ጥምረት ላይ ማስተካከያ በማድረግ ከተገማች አቀራረባቸው መላቀቅ ይጠቅባቸዋል።

ሀዋሳዎች በቅጣትም ሆነ በጉዳት የሚያጡት ተጫዋች የለም። ከፋሲል ከነማ ጋር አቻ በተለያዩበት የመጀመርያ ሳምንት ጨዋታ በቀይ ካርድ ከሜዳ የወጣው ተከላካዩ በረከት ሳሙኤል ቅጣቱን ጨርሶ ለጨዋታው ዝግጁ ሆኗል። በብርቱካናማዎቹ በኩል ያሲን ጀማል እና ተመስገን ደረስ ከጉዳታቸው ሙሉ ለሙሉ ባለማገገማቸው በነገው ጨዋታ ተሳትፎ አይኖራቸውም።

ሁለቱ ክለቦች ነገ በሊጉ  ለ23ኛ ጊዜ ይገናኛሉ። በእስካሁኖቹ ጨዋታዎች ስምንት ድሎች ያሏቸው ሀዋሳ ከተማዎች 25 ግቦችን ሲያስቆጥሩ ስድስት ድሎችን ያስመዘገቡት ድሬዳዋ ከተማዎች ደግሞ 22 ግቦችን ከመረ ብአገናኝተዋል። ቀሪዎቹ ስምንት ጨዋታዎች ነጥብ በመጋራት የተጠናቀቁ ነበሩ።

ባሪሶ ባላንጎ የዓመቱ የመጀመሪያ ጨዋታውን በዋና ዳኝነት ይመራል ፤ አዲሱ ኢንተርናሽናል ረዳት ዳኛ ሲራጅ ኑርበገን እና አብዱ ይጥናም በረዳት ዳኝነት ሲመደቡ ተከተል ተሾመ በበኩሉ አራተኛ ዳኛ ሆኖ ተመድቧል።