የአሰልጣኞች አስተያየት | መቻል 1-1 ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ

“አስለቃሽ ጭስ የተተኮሰ ይመስል እንዲህ ሲሆን ደግሞ እግር ኳሱ ለዛውን ያጣል” አሰልጣኝ ገብረክርስቶስ ቢራራ

“በእንቅስቃሴ ደረጃ ቡድናችን አዲስ እንደመሆኑ መጥፎ አይደለም” አሰልጣኝ በፀሎት ልዑልሰገድ

ሁለቱን የመዲናይቱን ክለቦች መቻል እና ንግድ ባንክን አገናኝቶ 1ለ1 ከተጠናቀቀው የዕለቱ ቀዳሚ ጨዋታ መጠናቀቅ በኋላ አሰልጣኞች ከሶከር አትዮጵያ ጋር ቆይታ አድርገዋል።

አሰልጣኝ በፀሎት ልዑልሰገድ – ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ

ስለ ጨዋታው …

“ጨዋታው በእንቅስቃሴ ደረጃ ጥሩ ነበር ማለት እችላለሁ ፣ መጀመሪያ የጀመርን አካባቢ ቶሎ ሪትም ውስጥ አልገባንም ነበር። ግን ቀስ በቀስ ወደ ጨዋታ በመግባት የምንፈልገውን ቅርፅ በማግኘት እና ጎል ማስቆጠር ችለን የመጀመሪያውን አርባ አምስት አንድ ለባዶ እየመራን ወጥተን ነበር። ሁለተኛው አርባ አምስት ላይ ደግሞ የተሻለ ለመንቀሳቀስ ፣ ተጨማሪ ጎል ለማግባት በኳስ ቁጥጥሩም ያለብንን ክፍተቶች አርመን ለመግባት ሞከርን ፣ ዕድሎችንም ለመፍጠር ሞከርን ፣ በእንቅስቃሴም ደረጃ መጥፎ አልነበርንም ብዬ አስባለሁ። ትንሽ ያበሳጨኝ ነገር መጨረሻ ላይ የፍፁም ቅጣት ምት ስለተገኘብን እና ነጥብ ስለተጋራን ብቻ እንጂ በእንቅስቃሴ ደረጃ ቡድናችን አዲስ እንደመሆኑ መጥፎ አይደለም።”

ውጤቱ ያለ መሳካቱ ምክንያት…

“ለምሳሌ የሳትናቸውን ጎሎችን ስታያቸው ምንም ይሁን ምንም ይቅርታ የማያስፈልገው ነገር ምንድነው ተጨማሪ ጎል ማግባት ነው ፣ አንድ እርሱ ነው ፣ ሁለተኛው ያለህን ጎል አስጠብቀህ መውጣት ነው ፣ ይሄንን ባለ ማድረጋችን ፣ ባለቀ ሰዓት በማትነሳበትም ወቅት ላይ የፍጹም ቅጣት ምት ገብቶብን ነጥብ ልናጋራ ችለናል ማለት ነው።”

በቀጣይ ስለሚጠበቅባቸው ጠንካራ ጎን…

“እንደ ቡድን ነው መንቀሳቀስ የምንፈልገው ይሄ ሦስተኛ ጨዋታችን ነው። ይሄንን እንቅስቃሴ ይሄንን የጨዋታ መንገድ እንደ ቡድን ማሳደግ በማጥቃትም ፣ በመከላከልም ያለውን አጠቃላይ የቡድኑን ቅርፅ ማሳደግ ያስፈልጋል እና ገና ነው ቡድናችን ይሄ ነው ማለት አልችልም ግን እየተሻሻለ ነው ብዬ አስባለሁ።”


አሰልጣኝ ገብረክርስቶስ ቢራራ – መቻል

ስለ ሁለቱ የጨዋታ አጋማሾች…

“ለእኛ ሁለቱም ተመሳሳይ ነው። ከዕረፍት በፊትም የተሻለ ተንቀሳቅሰናል ፣ ሁለት ጊዜ ነው የሞከሩት አንዱ ግብ ሆነ ግን እኛ ከዛ በላይ ሞክረናል። አንዳንዴ እንደዚህ ነው የሚሆነው እግር ኳስ ፣ እንጂ ጥሩ ነው የተጫወትነው ቡድኔም ጥሩ ነው።”

ከጨዋታ ጨዋታ ግብ የማስቆጠር መጠናቸው እያነሰ ስለ መምጣቱ…

“ቡድኖች እኮ ያላቸው የመከላከል ጥልቀት ነው ነፃ ጨዋታ ሲሆን እኛ እና ሀድያ ስንጫወት ለምሳሌ ሁለቱም ክፍት ነበር ፣ ኳስ ወደ ጎል ብቻ ነው የሚሄደው አሁን ግን አይተሀል ፣ አንድ ጎል ካገቡ በኋላ አንድ ቡድን አስር ልጅ ይወድቃል ፣ አስለቃሽ ጭስ የተተኮሰ ይመስል እንዲህ ሲሆን ደግሞ እግር ኳሱ ለዛውን ያጣል ፣ ተጫዋቾች በመቆራረጡ ምክንያት ወደ ታች ዝቅ በሚሉበት ሰዓት ያላቸውን ነገር ያጣሉ ማለት ነው።”

እንደ ከነዓን ፣ አስቻለው ፣ ግሩም እና መሰል ተጫዋቾች ስለ ገጠማቸው ጉዳት…

“ጉዳት ሁሌም በቡድንህ ላይ ተፅዕኖ ይኖረዋል ፣ ይሄ የታወቀ ነው ፣ ነገር ግን ያሉን ተጫዋቾች ደግሞ የነዛን ቦታ መሸፈን የሚችሉ ናቸው እና ብዙ አያሳስበኝም ብዬ አስባለሁ።”