መረጃዎች| 12ኛ የጨዋታ ቀን

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ሦስተኛ ሳምንት ነገ በሚደረጉ ሁለት ጨዋታዎች ይገባደዳል። ጨዋታዎቹን የተመለከቱ መረጃዎችንም እንደሚከተለው አሰናድተንላችኋል።

አዳማ ከተማ ከ ሀምበሪቾ ዱራሜ

በሁለተኛው ሳምንት ድል ያደረጉትን አዳማ ከተማዎች እና እስካሁን ድረስ ነጥብ ማስመዝገብ ያልቻሉት ሀምበሪቾ ዱራሜዎች የሚያደርጉት ጨዋታ የተመለከቱ መረጃዎች

ከንግድ ባንክ አቻ በመለያየት ሊጉን ጀምረው በሁለተኛው ሳምንት ወላይታ ድቻን የረቱት አዳማ ከተማዎች በአራት ነጥቦች 7ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል። አዳማዎች በሁለቱም ጨዋታዎች የተለያየ የአጨዋወት መንገድ ተከትለዋል። ንግድ ባንክን በገጠሙበት ጨዋታ ጥንቃቄ የተሞላበት አጨዋወት ሲከተሉ ድል ባደረጉበት ሁለተኛው ጨዋታ ግን በተሻለ መንገድ ኳሱን ለመቆጣጠር ብርቱ ጥረት አድርገዋል። አሰልጣኝ ይታገሱ እንዳለ ሦስት ነጥብ ያስገኘላቸውን አጨዋወት ይቀይራሉ ተብሎ ባይገመትም ቋሚ አሰላለፉ ላይ ግን ለውጦች ማድረጋቸው የሚጠበቅ ነው። ባለፈው ጨዋታ ተቀይሮ ገብቶ የሚታይ ለውጥ ያመጣው ዊልያም ሰለሞንም ወደ ቋሚ አሰላለፉ ይመለሳል ተብሎ ይገመታል። አዳማዎች በ180 ደቂቃዎች አንድ ግብ ብቻ ያስቆጠረው የማጥቃት አጨዋወታቸው ላይ ውስን ለውጦች ያደርጋሉ ተብሎም ይጠበቃል። ቡድኑ ምንም ግብ ያላስተናገደ ጠንካራ የተከላካይ ክፍል ቢኖረውም ያስቆጠረው የግብ መጠን አንድ ብቻ መሆኑ ስናይ ግን በማጥቃት አጨዋወቱ ለውጥ የማድረግ አስፈላጊነት ግድ መሆኑን መታዘብ ይቻላል። ከዚ በተጨማሪ ተጋጣሚያቸው ከኳስ ውጭ ከፍ ባለ ጫና የሚጫወት ቡድን ስለሆነ በኳስ አመሰራረት ሂደት ላይ የሚስተዋሉ ስህተቶችን ማረም ይጠበቅባቸዋል።


በተመሳሳይ የሁለት ለአንድ ሽንፈቶች አስተናግደው በሰንጠረዡ ግርጌ ለመቀመጥ የተገደዱት ሀምበሪቾ ዱራሜዎች የውድድር ዓመቱን የመጀመሪያ ድል ፍለጋ አዳማን ይገጥማሉ። ቡድኑ በአጨዋወት ረገድ ብዙ ተስፋ ሰጪ ጎኖች ቢኖሩትም በሁለቱም ጨዋታዎች ላይ የነበራቸው
የግብ ዕድሎችን ያለመጠቀም ችግር ለውጤት ማጣቱ እንደ ዋነኛ ምክንያት ይነሳል። አሰልጣኝ ደጉ ዱባሞ በነገው ጨዋታም እንደ ባለፉት ጨዋታዎች ኳሱን በመቆጣጠር እና ከኳስ ውጭ ከፍ ባለ ጫና የሚጫወት ቡድን ያስመለከቱናል ተብሎ ይጠበቃል። ሆኖም ተጋጣሚያቸው በሊጉ ምንም ግብ ያላስተናገደ ቡድን እንደመሆኑ የማጥቃት ክፍላቸውን ውጤታማነት ከፍ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል።

በሀምበሪቾዎች በኩል ኤፍሬም ዘካርያስ በጉዳት ምክንያት ለጨዋታው አይደርስም ፤ በተቃራኒው ቃለአብ በጋሻው ቅጣቱን ጨርሶ ለጨዋታው ይደርሳል። በአዳማ በኩል መስዑድ መሐመድ በጉዳት ምክንያት ከጨዋታው ውጭ ሆኗል። ከዚ በተጨማሪ አዲስ ፈራሚዎቹ ሐቢብ መሐመድና ቻርለስ ሪባኑ የወረቀት ጉዳዮች ባለማጠናቀቃቸው ከነገው ጨዋታ ውጭ ሆነዋል። በሌላ ዜና ባለፈው ጨዋታ ያልተሳተፈው ዮሴፍ ታረቀኝም ወደ ሜዳ ተመልሶ ቡድኑን ያገለግላል ተብሎ ይጠበቃል።

ይህንን ጨዋታ ሀብታሙ መንግስቴ በዋና ዳኝነት ሲመራው ፣ ኢንተርናሽናል ረዳት ዳኛ ፋሲካ የኋላሸት እና ኤልያስ መኮንን በረዳት ዳኝነት አባይነህ ሙላት ደግሞ አራተኛ ዳኛ በመሆን ጨዋታውን ይመሩታል።

ሁለቱ ቡድኖች በታሪካቸው ለመጀመሪያ ጊዜ በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ውድድር ነገ ይገናኛሉ።

ባህርዳር ከተማ ከ ኢትዮጵያ ቡና

የሳምንቱ የመጨረሻ መርሐ-ግብር የሆነው እና ተጠባቂውን ጨዋታ የተመለከቱ መረጃዎች እንደሚከተለው አቅርበንላችኋል

ከሁለት ወሳኝ መርሐ-ግብሮች ሦስት ነጥቦች ሰብስበው በ 11ኛ ደረጃነት የተቀመጡት የጣና ሞገዶቹ  ነጥብ ካልጣሉት ኢትዮጵያ ቡናዎች ጋር የሚያደርጉት ጨዋታ ተጠባቂ ነው። ከባለፈው የውድድር ዓመት አጨዋወታቸው ብዙም ለውጥ ሳያደርጉ  ጨዋታዎቻቸው በማካሄድ ላይ የሚገኙት ባህርዳሮች በፈጣን ሽግግሮች ላይ የተመሰረተ ስኬታማ የማጥቃት አጨዋወታቸውን እንደሚያስቀጥሉ አጠያያቂ አይደለም። በየጨዋታው በአማካይ ሁለት ግቦች ማስቆጠራቸውም ምን ያህል ጠንካራ የማጥቃት ክፍል እንዳላቸው አንዱ ማሳያ ነው። አሰልጣኝ ደግአረግ በመጀመርያው ጨዋታ ሦስት ግቦች ያስተናገደውን የተከላካይ ክፍላቸው ላይ ያደረጉት ለውጥም በበጎ ጎኑ ይጠቀሳል። ጠንካራ የአጥቂ ክፍል ካላቸው ቡድኖች አንዱ የሆነውን መቻል በገጠሙበት ጨዋታም የተከላካይ ክፍሉ ጥንካሬ የታየበት ነበር። የመሀል ተከላካዮቹ ፍሬዘር ካሳና ያሬድ ባየህ አስተዋፅኦም የጎላ ነበር።


በመጀመርያዎቹ ሁለት ሳምንታት ካደረጓቸው ጨዋታዎች ስድስት ነጥቦች መሰብሰብ የቻሉት ኢትዮጵያ ቡናዎች የሰመረ አጀማመራቸውን ለማስቀጠል ከባህርዳር ከተማ ጋር ብርቱ ፉክክር ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል። በሁለቱም መርሐ-ግብሮች በሁለቱም መስመሮች እንዲሁም ቀጥተኛ አጨዋወት ለመከተል የመረጡት ቡናማዎቹ በነገው ጨዋታም ውጤታማ ያደረጋቸውም አጨዋወት ያስቀጥላሉ ተብሎ ይጠበቃል። ሆኖም ከተጋጣሚያቸው ጥንካሬ አንፃር በአንዳንድ ተጫዋቾች እንቅስቃሴ ላይ ውስን ለውጦች ማድረጋቸው አይቀሬ ይመስላል።

ቡናማዎቹ ባለፉት ሁለት ጨዋታዎች ያልተገደበ የማጥቃት እንቅስቃሴ ባላቸው የመስመር ተከላካዮች እና በጥሩ ወቅታዊ አቋም ላይ በሚገኙ ጫላ ተሺታና በፍቃዱ አለማየሁ ለማጥቃት ጥረት ማድረጋቸው ይታወቃል ፤ የነገው ተጋጣሚያቸው ባህርዳር በቁጥር በዝቶ በፈጣን ሽግግር የሚያጠቃ ቡድን እንደመሆኑ ግን ቢያንስ በመስመር ተከላካዮቹ እንቅስቃሴ ላይ ገደብ መጣላቸው አይቀርም። ኢትዮጵያ ቡናዎች ባለፈው ሳምንት ተቀይሮ በመግባት የመጀመርያ የሊግ ጨዋታውን ያደረገው አምበሉ አማኑኤል ዮሐንስን ወደ ቋሚ አሰላለፍ የሚመልሱበት ዕድልም አለ።

ኢትዮጵያ ቡና ከሮቤል ተክለሚካኤል ውጭ በጉዳትና በቅጣት የሚያጡት ተጫዋች የለም። ባህርዳር ከተማዎች በተመሳሳይ ከቅጣት እና ከጉዳት ነፃ የሆነው ስብስባቸውን ይዘው ለጨዋታው ይቀርባሉ።

ኢንተርናሽናል ዳኛ አሸብር ሰቦቃ በመሐል ዳኛ ሲያገለግል ፣ ኢንተርናሽናል ረዳት ዳኛ ትግል ግዛው እና ሠለሞን ተስፋዬ ረዳቶች ሆነው ተመድበዋል። የዕለቱ አራተኛ ዳኛ ደግሞ ኢንተርናሽናል በላይ ታደሰ ይሆናሉ።

ሁለቱ ቡድኖች ከዚህ ቀደም ለ 8 ጊዜያት ተገናኝተው ባህር ዳር ከተማ ሦስት ኢትዮጵያ ቡና ደግሞ አንድ ጊዜ ድል ሲያደርጉ አራቱ ጨዋታዎች አቻ የተጠናቀቁ ናቸው። በግንኙነታቸውም ቡድኖቹ እኩል 13 ግቦችን አስቆጥረዋል።