የ2016 የአንደኛ ሊግ ውድድር የሚጀመርበት ቀን ታውቋል

የ2016 የኢትዮጵያ አንደኛ ሊግ ውድድር የሚጀመርበት ቀን ይፋ ሲሆን በኢትዮጵያ ዋንጫ ላይ የሚሳተፉ ክለቦችም ታውቀዋል።


የ2016 የኢትዮጵያ አንደኛ ሊግ ውድድር ከ60 በላይ ክለቦችን በማሳተፍ እንደሚደረግ ይጠበቃል። ውድድሩ ከመጀመሩ በፊት በዛሬው ዕለት የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌድሬሽን ከከፍተኛ ሊጉ የዕጣ ማውጣት ስነ ስርዓት መጠናቀቅ በኋላ ከአንደኛ ሊግ ክለቦች ጋር የቅድመ ስብሰባ ውይይትን በጁፒተር ሆቴል ያካሄደ ሲሆን የውድድሩ የዕጣ ማውጣት ስነ ስርዓት ፣ ውድድሩ የሚጀመርበት ቀን እና በኢትዮጵያ ዋንጫ የሚካፈሉ አራት ክለቦችም ተለይተው ታውቀውበታል።


በዚህም መሠረት የዘንድሮው የአንደኛ ሊግ ውድድር የዕጣ ማውጣት መርሐ-ግብሩ ህዳር 1 ከተደረገ በኋላ ውድድሩ ህዳር 15 በይፋ ይጀመራል። በተጨማሪም በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ እንደ ከፍተኛ ሊግ ክለቦች ሁሉ የአንደኛ ሊግ 4 ቡድኖች በኢትዮጵያ ዋንጫ የመጀመሪያ ዙር ጨዋታዎች ላይ ይሳተፋሉ። ቡራዩ ፣ ጉለሌ ፣ አቃቂ እና አሶሳ በውድድሩ የሚካፈሉ ክለቦች ናቸው።