የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ | የ3ኛ ሳምንት ምርጥ 11

የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የሦስተኛ ሳምንት ጨዋታዎችን መሠረት በማድረግ ይህንን ምርጥ ቡድን ሠርተናል።

አሰላለፍ ፡ 4-1-3-2

ግብ ጠባቂ

ፍሬው ጌታሁን – ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ

በጨዋታ ሳምንቱ ተመሳሳይ ብቃት ያሳዩ የግብ ዘቦችን መመልከት ብንችልም በአንፃራዊነት ፍሬው በግሉ ጥሩ ቀን አሳልፏል። ቡድኑ በመጨረሻ ደቂቃ በተቆጠረበት ፍፁም ቅጣት ምት አንድ አቻ ቢወጣም ሌሎች እጅግ ለግብ የቀረቡ ሦስት አጋጣሚዎችን ያመከነበት እና በጥሩ የጊዜ አጠባበቅ ተሻጋሪ ኳሶች ሲመክት የነበረበት መንገድ እንዲሁም በተከታታይ ጨዋታዎች ላይ እያሳየ ያለው ዕድገት ምርጫ ውስጥ እንዲገባ አስችሎታል።

ተከላካዮች

ጀሚል ያዕቆብ– አዳማ ከተማ

በሳምንቱ ምርጥ ብቃት ካሳዩ ተጫዋቾች መካከል አንዱ የሆነው ጀሚል ቡድኑ ከሀንበርቾ ጋር ነጥብ ተጋርቶ ሲወጣ የነበረው ብቃት መልካም የሚባል ነበር። ዋና ኃላፊነቱ መከላከል ቢሆንም ለማጥቃት ወደ ተጋጣሚ ሜዳ ለመሄድ የማይደክመው ተጫዋቹ አዳማ ላስቆጠራቸው ሁለቱም ጎሎች አመቻችቶ በማቀበል መነሻ የነበረ መሆኑ ትልቅ አድናቆት እንዲቸረው አድርጎታል።

ተስፋዬ መላኩ – ወልቂጤ ከተማ

በሠራተኞቹ ቤት ሁለተኛ ዓመት ቆይታውን እያደረገ የሚገኘው ተስፋዬ ከዚህ ከቀደም ከነበረው አላስፈላጊ ጥፋቶች በመሥራት ቡድንን ዋጋ ከሚያስከፍሉ እንቅስቃሴዎች ፍፁማዊ ለውጥ በማድረግ ቡድኑን በብስለት እያገዘ ይገኛል። የሀዲያን የዓየር እና የመሬት ጥቃቶችን በንቃት እየተከታተለ አደጋ እንዳይፈጠር ያደርግ የነበረው የመከላከል ሥራ ድንቅ ሲሆን በተለይ ግዙፉን የሀዲያ አጥቂ ሪችሞንግ ኦዶንጎን ጨምሮ የመስመር አጥቂዎቹን ከጨዋታ ውጭ ያደረገበት መንገድ አስመርጦታል።

ፈቱዲን ጀማል – ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ

ዘንድሮ አዲስ አዳጊውን ክለብ ተቀላቅሎ በአንበልነት ቡድኑን የሚመራው ፈቱዲን እስካሁን በተደረጉ ሦስት ጨዋታዎች ለቡድኑ ያለውን አቅም ሁሉ እየሰጠ ጥሩ የውድድር ዓመት እያሳለፈ ይገኛል። በቁመቱ አጠር ቢልም በአዕምሮ ፈጥኖ የአንድ ለአንድ ግኑኝነትም ሆነ የዓየር ላይ ኳሶችን እንዲመክኑ ያደርግ የነበረበት መንገድ ልዩ ነበር። ምንም እንኳን በመጨረሻ ደቂቃ ቡድኑ በፍፁም ቅጣት ምት ጎል ነጥብ ተጋርቶ ቢወጣም ፈቱዲን ቡድኑ አሸንፎ እንዲወጣ የተሻለውን ሁሉ በማድረጉ እንዲመረጥ ሆኗል።

ፍፁም ግርማ – ወላይታ ድቻ

ከወላይታ ድቻ ነባር ተጫዋቾች ጋር በፍጥነት ለመላመድ ብዙም ያልተቸገረው ፍፁም በግራ መስመር ከነበሩ ሌሎች ተጫዋቾች በአንፃራዊነት የተሻለ ጊዜን አሳልፏል። ለመከላከል ቅድሚያ ሰጥቶ ሲጫወት የተመለከትነው ፍፁም በሽግግሮች ወቅትም ባልተገደበ የማጥቃት እንቅስቃሴ በቦታው ጥሩ አበርክቶ ለመስጠት ሲታትር የዋለ ሲሆን በተለይም ወደ ተጋጣሚ ሳጥን የሚደርስበት ብቃቱ እና የመጨረሻ ተሻጋሪ ኳሶቹ ወደ በዚህ ምርጫ ውስጥ እንዲካተት አስችለውታል።

አማካዮች

አብነት ደምሴ – ወላይታ ድቻ

በክረምቱ የዝውውር መስኮት የጦና ንቦቹን የተቀላቀለው አብነት በአሰልጣኝ ያሬድ ገመቹ ሥር ለወላይታ ድቻ አዲሱ የአጨዋወት መንገድ ዋነኛ መሣሪያ ሆኖ እያገለገለ ይገኛል። አማካዩ ቡድኑ ለሚፈልገው የኳስ ቁጥጥር ብልጫ እና ፈጣን የማጥቃት ሽግግር የቡድኑን ሚዛን በመጠበቅ ስኬታማ ጊዜ እያሳለፈ የሚገኝ ሲሆን ኢትዮጵያ መድንን 1-0 በረቱበት ጨዋታም ብቸኛዋን ግብ ከረጅም ርቀት በአስደናቂ ሁኔታ ማስቆጠር ችሏል።

ብዙዓየሁ ሰይፈ – ወላይታ ድቻ

እንደ ቡድን አጋሩ አብነት የተሳካ የጨዋታ ቀን ማሳለፍ የቻለው ብዙዓየሁ ዕረፍት የለሽ በሆነ እንቅስቃሴው ከሳጥን ሳጥን ብዙ ቦታዎችን ለማካለል የሚያደርጋቸው ማራኪ ሩጫዎቹ ለሌሎቹ ተጫዋቾች እፎይታን የፈጠሩ ሆነዋል። ሆኖም በዚህ የጨዋታ ሳምንትም የነበረው ታታሪነት እና ለማጥቃት እንቅስቃሴያቸው መነሻ የሆኑ ቁልፍ ኳሶችን ሲያመቻች የነበረበት መንገድ በቦታው ተመራጭ አድርጎታል።

ቸርነት ጉግሣ – ባህር ዳር ከተማ

በያዝነው የውድድር ዓመት የጣና ሞገዶቹን በመቀላቀል በቦታው ተቀዳሚ ምርጫ መሆን የቻለው ቸርነት ቡድኑ ከኢትዮጵያ ቡና ጋር ባደረገው ጨዋታ 2ለ2 ተለያይቶ ነጥብ ሲጋራ በጥሩ ክህሎት ለተከላካዮች ፈተና ከመሆኑ ባሻገር የቡድኑን የመጀመሪያ ግብ በስሙ ማስመዝገብ ሲችል ፍጹም ጥላሁን ላስቆጠረው ግብም አመቻችቶ ማቀበል ችሏል።

ፍጹም ጥላሁን – ባህር ዳር ከተማ

እንደ ቡድን አጋሩ ቸርነት ሁሉ ድንቅ ጊዜን ያሳለፈው ፍጹም በተደጋጋሚ የሚያደርጋቸው ዕረፍት የለሽ የማጥቃት እንቅስቃሴዎች ለቡና ተከላካዮች አስቸጋሪ ነበሩ። ተጫዋቹ ከእንቅስቃሴው ባሻገር ቸርነት ጉግሣ ላስቆጠረው ግብ አመቻችቶ ማቀበል ሲችል የቡድኑን ሁለተኛው ግብም በግንባሩ በመግጨት ማስቆጠር መቻሉ ከውጤታማነቱም አንጻር ያለ ተቀናቃኝ በቦታው ተመራጭ ያደርገዋል።

አጥቂዎች

ብሩክ በየነ – ኢትዮጵያ ቡና

ከአዲሱ አሰልጣኝ ኒኮላ ካቫዞቪች መምጣት በኋላ እጅግ ተሻሽለው ወደ ብቃታቸው ጫፍ እየተጓዙ ካሉት ተጫዋቾች ውስጥ ብሩክ አንዱ ነው። ተጫዋቹ ቡድኑ ከባህር ዳር ከተማ ጋር ሁለት አቻ በተለያየበት ጨዋታ ለጫላ ተሺታ አመቻችቶ በማቀበል ለመጀመሪያው ግባቸው መነሻ ሲሆን ሁለተኛውን ግብም ራሱ ማስቆጠር ችሏል።

አቤል ያለው – ቅዱስ ጊዮርጊስ

በሦስት ጨዋታዎች አራት ግቦችን በማስቆጠር የወቅቱ የሊጉ ኮከብ ግብ አስቆጣሪ የሆነው አቤል ያለው ለፈረሠኞቹ ወሳኝ ተጫዋች መሆኑን በተደጋጋሚ እያስመሰከረ የሚገኝ ሲሆን ቡድኑ በሻሸመኔ ከተማ ሁለት ጊዜ ከመመራት ተነስቶ የ3ለ2 ድል ሲጎናጸፍ ካደረገው መልካም እንቅስቃሴ ባሻገር የመጀመሪያ እና የመጨረሻ ግቦችን ከቅጣት ምት እና ከፍጹም ቅጣት ምት በማስቆጠር ቡድኑን አሸናፊ በማድረጉ በቦታው ያለ ተቀናቃኝ ተመራጭ መሆን ችሏል።


አሰልጣኝ – ዘሪሁን ሸንገታ

በ 100% የማሸነፍ ንፃሬ የሊጉ መሪ የሆነው ቅዱስ ጊዮርጊስ ባሳለፍነው የጨዋታ ሳምንት ከሁለት ጊዜ መመራት ተነስቶ ሻሸመኔን 3ለ2 ሲረታ የቡድኑ አሰልጣኝ ዘሪሁን በመጨረሻዎቹ 25 ደቂቃዎች ያደረጓቸው ቅያሪዎች ለውጤቱ መሳካት እጅግ ከፍተኛ ሚና ነበራቸው። ተቀይሮ የገባው በረከት ወልዴ ሁለተኛውን ግብ ሲያስቆጥር በተመሳሳይ ተቀይሮ የገባው ሞሰስ አዶ ላገኙት የፍጹም ቅጣት ምት ቁልፍ መነሻ ነበር። በዚህም አሰልጣኙ ከያሬድ ገመቹ ጋር ተፎካክረው ጨዋታውን አንብበው ባደረጉት ስኬታማ ቅያሪ እና ከመመራት ተነስተው ባሳኩት ድል ምክንያት ተመራጭ ሆነዋል።

ተጠባባቂዎች

ዳንኤል ተሾመ – ድሬዳዋ ከተማ
ወንድሜነህ ደረጄ – ኢትዮጵያ ቡና
ያሬድ ዳዊት – ሻሸመኔ ከተማ
አበባየሁ ሀጂሶ – ወላይታ ድቻ
ዊልያም ሰለሞን – አዳማ ከተማ
አሜ መሐመድ – ወልቂጤ ከተማ
ኪቲካ ጀማ – ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ
ዳግም በቀለ – ሀምበርቾ