የሉሲዎቹን እና የጭልፊቶቹን ጨዋታ የሚመሩት ዳኞች ታውቀዋል

በ2024 በፓሪስ ለሚደረገው የሴቶች ኦሊምፒክ እግርኳስ ውድድር ለማለፍ በነገው ዕለት በአበበ ቢቂላ ስታዲየም የሚደረገውን የመጀመሪያ ጨዋታ የቶጎ ዜግነት ያላቸው ዳኞች ይመሩታል።

የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ሴቶች ብሔራዊ ቡድን በኦሊምፒክ የሴቶች እግርኳስ ማጣርያ ሁለተኛ ዙር የመጀመርያ ጨዋታ ናይጄርያን በነገው ዕለት በአበበ ቢቂላ ስታዲየም የሚያስተናግድ ሲሆን ጨዋታውን የሚመሩት የቶጎ ዜግነት ያላቸው ዳኞች እንደሆኑም ታውቀዋል።

በዚህም ንዴድጂ ኤዶህ በዋና ዳኝነት ፣ አግበዳኑ አብራ ሲቶፌ እና አውቴይ ኮሲዋ ኬይጋን በረዳትነት እንዲሁም አሜዶሜ ቪንሴንሺያ ኢንዮናም በአራተኛ ዳኝነት ሲመደቡ ጊኒያዊቷ ኦላሬ ዳሎባ የዳኞች አሴሰር ፣ ጋናዊቷ ዚጋ ክርስቲን ኢንዮናም ደግሞ የጨዋታው ኮሚሽነር ሆነው ተሰይመዋል።

የሁለቱም ብሔራዊ ቡድኖች የመጀመሪያ ጨዋታ ነገ ረቡዕ ጥቅምት 14 ከቀኑ 9፡30 የሚደረግ ሲሆን የመልሱ ጨዋታ ደግሞ ማክሰኞ ጥቅምት 20 ቀን ከምሽቱ 12 ሰዓት ላይ አቡጃ በሚገኘው አቢዮላ ስታዲየም ይደረጋል።