የአሰልጣኞች አስተያየት | ድሬዳዋ ከተማ 2-3 ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ

“ቡድኑ ከዕለት ወደ ዕለት እየተሻሻለ ነው ብዬ አስባለሁ” አሰልጣኝ በፀሎት ልዑልሰገድ

“ጎል ላይ የምንስታቸው ኳሶች ዋጋ እያስከፈሉን ነው” አሰልጣኝ አስራት አባተ

ምሽቱን በተደረገው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና ድሬዳዋ ከተማ ጨዋታ በወይንጠጅ ለባሾቹ 3-2 አሸናፊነት መጠናቀቅ በኋላ ሶከር ኢትዮጵያ ከአሰልጣኞቹ ጋር ቆይታን አድርጋለች።

አሰልጣኝ በፀሎት ልዑልሰገድ – ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ

ስለ ጨዋታው ..

“አጀማመራችን ባለፈው የመጀመሪያ ጨዋታን ከመቻል ጋር እንዳደረግነው የመጀመሪያ አስር አስራ አምስት ደቂቃዎች ቶሎ ሪትም ውስጥ ያለመግባት ነገር ነበር ፤ አንዱ እንደ ዕርምት የወሰድነው። ዛሬ ደግሞ እሱን አስተካክለን ቶሎ ሪትም ውስጥ የመግባት ፣ ኳሱን የመቆጣጠር ፣ ጫና መፍጠር የሚለውን በደንብ ተሳክቶልናል ብዬ አስባለሁ። ይኸውም ከመጀመሪያው ጀምሮ በይበልጥ በኳስ ቁጥጥሩም ጫና በመፍጠርም የተሻልን ነበርን። ጎሎችንም ከዕረፍት በፊት ሁለት ጎሎችን አግብተናል። በዕረፍት ሰዓት የእርማት እና በይበልጥ እነርሱ እያጠቁ ያሉት በየቱጋ ነው የሚለውን ለማረም ሞከርን። ከዕረፍትም በኋላ ያንን የማስቀጥል ሥራን ነበር ስንሰራ የነበርነው። ጨዋታውም ክፍት ጨዋታ ነበር ፤ ተጨማሪ አንድ ጎል አገባን። ነገር ግን ከጥንቃቄ ማነስ የገቡብን ጎሎች ናቸው። እነኚህን የምናርማቸው ናቸው እንጂ እንደ አጠቃላይ በሁሉም ረገድ ደስተኛ ነኝ። ጥሩ ነበር ማለት ነው። ቡድኑን ከዕለት ወደ ዕለት እየተሻሻለ ነው ብዬ አስባለሁ።”

ፉዓድ ፈረጃ እና ቢኒያም ጌታቸው ወደ ተጠባባቂ ወንበር ስለመውረዳቸው…

“አንደኛው የታክቲካል ለውጥ ነው። ሁለተኛው ደግሞ ትንሽ ከጤንነትም ጋር ያሉ ነገሮች ስላሉ ነው ፣ ሁለቱ ናቸው ዋነኛ ምክንያቶች።”

ከሦስቱ ጎሎች መካከል የአሰልጣኙን የጨዋታ መንገድ ስለምትገልፀዋ ጎል…

“በተለይ ሁለቱ ጎሎች በትክክል ይዘን ወይንም ደግሞ በጨዋታ ሂደት ውስጥ የተገኙ ጎሎች ናቸው እና ሁለቱ ጎሎች የበለጠ ፤ ግን ሦስተኛው አይገልጽም እያልኩ አይደለም። በይበልጥ ደግሞ ሁለቱ የመጀመሪያዎቹ ጥሩ ናቸው ብዬ አስባለሁ።”

በሁለቱም አጋማሾች በመጀመሪያ አስራ አምስት ደቂቃዎች ስለሚታዩ መቀዛቀዞች…

“የበለጠ በየጊዜው ስለ መሻሻል ነው የምናስበው ፤ አሁን ፒካችን ላይ ደርሰናል። የተሻለ ቡድን ነው ፤ ፐርፎርማንሳችን እንደ ቡድንም እያልኩህ አይደለም። ራሳችንን ከራሳችን ጋር ስናነፃፅር ከዕለተ ወደ ዕለት የተሻለ ነገር እያየየን ነው ፤ ያንን ለማሻሻል ነው የምንሄደው።”

አሰልጣኝ አስራት አባተ – ድሬዳዋ ከተማ

ስለ ጨዋታው…

“ጨዋታው ጥሩ የሚባል ነው ፤ በሁለታችንም መሐል የተደረገው። አንድ ነጥብ ልዩነት ነው የነበረን ሁለታችንም ጥሩ እንቅስቃሴ ያደረግንበት ነው። እንዳለፈው ጨዋታ በሀዋሳም ፣ በቡናም እንደነበረው ጎል ላይ የምንስታቸው ኳሶች ዋጋ እያስከፈሉን ነው። ምን አልባት ሁለት ጎል ማግኘታችን ነው እንጂ ከዛ በላይ ንፁህ ዕድሎችን መጠቀም አልቻልንም ፤ በዛ ላይ ሰርተን እንመጣለን ።”

ወጥ የሆነ እንቅሰቃሴ በቡድኑ ላይ አለመኖሩ…

“እንደውም ከተጋጣሚ ቡድን የተሻለ ነው እንዴት እንዳየኸው አልገባኝም። ይሄ በየትኛውም ቡድን ላይ ያለ ነው ፤ አሸናፊ ቡድን ላይ እንኳን በእኛ ደረጃ አይደለም ያለው። እንቅስቃሴው የሚያሳየው ምክንያቱም የኢንዲቪዡዋል ልዩነቶች እና የእኛ ግብ ጠባቂ የነበረው የታይሚንግ አጠባበቅ ከጓደኛው ጋር የመናበብ ስህተቶች ጎሎች እንዲገቡ ሆኗል እንጂ በእንቅስቃሴ ደረጃ ከተጋጣሚ ቡድን የተሻልን ነን። ይሄ እንቅስቃሴ እንግዲህ ከባድ ጨዋታ ስለሆነ ጨዋታው ራሱ የሚያመጣው ሙድ ነው። ምክንያቱም ተጋጣሚህ ቡድን ቀላል የምትለው አይደለም ፤ አቅም ያላቸው ቡድኖች ናቸው። የእኛ አብዛኞቹ ልጆች ወጣት ተጫዋቾች ናቸው ያ ላይ የበለጠ እየሰራን ስንመጣ የበለጠ ጠንካራ እንሆናለን።”

ቡድኑ ላይ በቀጣይ ልንጠብቀው ስለምንችለው ጠንካራ ጎን…

“ቡድኑ ታክቲካሊ በጣም ዲሲፕሊን ነው ፣ ከዛ ውጪ ደግሞ በህብረት ነው የሚነጥቁት። በህብረት ነው ለማጥቃት ጥረት የሚያደርጉት መቀጠል አለበት ብዬ አስባለሁ። የእያንዳንዱ ቡድን አጨዋወት አግሬሲቭ የሆነ አጨዋወትን ነው የሚመርጡት ያንን ጫና መቋቋማቸውም አንድ ጠንካራ ብዬ አስባለሁ። ጎሎች ከዚህ በፊት በተከታታይ ጨዋታ አላገባንም ፣ ዛሬ ሁለት ጎል ማግባት ችለናል ፣ ይሄን እያደበርን ከሄድን አንድ ነገር ማሳካት እንችላለን።”