መረጃዎች | 14ኛ የጨዋታ ቀን

ዛሬ በተደረጉ ሁለት ጨዋታዎች የጀመረው
የአራተኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ነገም ይቀጥላል። ነገ የሚደረጉ ሁለቱን ጨዋታዎች የተመለከቱ መረጃዎችንም እንደሚከተለው አቅርበንላችኋል።

ሀዋሳ ከተማ ከ ኢትዮጵያ መድን

በሦስተኛው ሳምንት ድል ማስመዝገብ ያልቻሉትን ቡድኖች የሚያገኘው ጨዋታ የተመለከቱ መረጃዎች!

በሦስቱም ሳምንታት አምስት ነጥቦች የሰበሰቡት ሀዋሳዎች በአንድ ጨዋታ ድል አድርገው ሁለት ጨዋታዎች አቻ ተለያይተዋል። ቡድኑ በመጀመሪያው ሳምንት በፋሲል ከነማ ሦስት ግብ ካስተናገደ በኋላ በመጨረሻዎቹ ሁለት ጨዋታዎች ግብ ያላስተናገደ ጠንካራ የተከላካይ ክፍል አለው። የመከላከል አደረጃጀታቸው እና ከኳስ ውጭ ያላቸው እንቅስቃሴም የቡድኑ ጠንካራ ጎን ነው። እንደ ተጋጣሚያቸው አቀራረብ የሚቀያየር አጨዋወት መርጠው ጨዋታዎቻቸውን በማካሄድ ላይ የሚገኙት ኃይቆቹ ከድሬዳዋ ከተማ ጋር ባካሄዱት የመጨረሻ ሳምንት ጨዋታ ላይ ግን በአንፃራዊነት ደከም ያለ እንቅስቃሴ አድርገው ነጥብ ተጋርተዋል። ጨዋታው ላይ የፈጠሯቸው የግብ ዕድሎች ጥቂት መሆንም ቡድኑ ግብ እንዳያስቆጥር አድርጎታል። በሁለት ጨዋታዎች ያስቆጠሩት የግብ መጠንም አንድ ነው።

ባደረጓቸው ሦስት ጨዋታዎች ሦስቱም የጨዋታ ውጤቶች ማለትም ድል፣ የአቻና ሽንፈት ውጤቶች አስመዝግበው በአራት ነጥቦች 10ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ኢትዮጵያ መድኖች ከሦስተኛው ሳምንት ሽንፈት መልስ ሀዋሳን ይገጥማሉ።
መድኖች ወላይታ ዲቻን በገጠሙበት ጨዋታ ከቀደመው ብቃታቸው ወርደው ነው የታዩት። በጨዋታው የሦስት ወሳኝ ተጫዋቾቻቸው በጉዳት መውጣትም ተፅዕኖ አሳድሮባቸዋል። በተለይም የቡድኑ ዋነኛ የማጥቂያ መሳሪያ የሆነው ሀቢብ ከማል ከሜዳ ከወጣ በኋላም የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር ተቸግረው ታይተዋል። በነገው ጨዋታም ሀቢብ ከማልን ጨምሮ በርካታ ወሳኝ ተጫዋቾቻቸውን በጉዳት ምክንያት ማጣታቸውን ተከትሎ የቀደመው በፈጣን የማጥቃት ሽግግር ያተኮረው አጨዋወታቸውን ለመተግበር መቸገራቸው አይቀሬ ነው። በአዲስ የማጥቃት ጥምረት ጨዋታውን ይጀምራሉ ተብለው የሚጠበቁት አሰልጣኝ ገብረመድኅን ኃይሌ ተጋጣሚያቸው ጠንካራ የተከላካይ ክፍል ያለው ቡድን እንደመሆኑ የአጥቂዎቻቸውን ስልነት ከፍ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል።

ሀዋሳ ከተማዎች በቅጣትም ሆነ በጉዳት የሚያጡት ተጫዋች የለም። ኢትዮጵያ መድኖች በነገው ጨዋታ የወሳኙን አጥቂያቸው ሀቢብ ከማልን ጨምሮ የብሩክ ሙሉጌታ ፣ የበርናንድ ኦቼንግ ፣ የተካልኝ ደጀኔ እና የጆርጅ ደስታን አገልግሎት የማያገኙ ሲሆን የአዲስ ተስፋዬም መሰለፍም አጠራጣሪ ስለመሆኑ ታውቋል።

ሊጉ በአዲስ ፎርማት ሲጀመር የነበሩት ሁለቱ ክለቦች በአጠቃላይ 27 ጊዜ ተገናኝተዋል። ሀዋሳ 13 በማሸነፍ ከፍተኛ የበላይነት ሲያስመዘግብ የመጨረሻ አራት ተከታታይ ጨዋታዎችን ጨምሮ በ10 አጋጣሚዎች አቻ ተለያይተው መድን 4 ጨዋታ አሸንፏል። (ሁለቱም አንድ አንድ ጨዋታ በፎርፌ አሸናፊ ሆነዋል) ሀዋሳ 36 ፣ መድን 26 አስቆጥረዋል።

ኢንተርናሽናል ዳኛ አሸብር ሰቦቃ የጨዋታው ዋና ዳኛ ሆኖ ተመድቧል። አብዱ ይጥና እና አማን ሞላ ደግሞ ረዳት ዳኞች ናቸው ፤ ባህሩ ተካ በበኩሉ የጨዋታው አራተኛ ዳኛ ሆኖ ተመድቧል።

ወልቂጤ ከተማ ከ ባህርዳር ከተማ

በመጨረሻው ሳምንት በተመሳሳይ ነጥብ ተጋርተው ወደ ድል መንገድ ለመመለስ አልመው ወደ ሜዳ የሚገቡ ቡድኖችን የሚያገናኘው ጨዋታ የተመለከቱ መረጃዎች!

ወልቂጤዎች በመጀመሪያው ሳምንት ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ባደረጉት ጨዋታ ካሳዩት ደካማ እንቅስቃሴ በኋላ የሚታይ መሻሻል አሳይተዋል። ከአስከፊው የአራት ለአንድ ሽንፈት በኋላ በመጨረሻዎቹ ሁለት ጨዋታዎች ሽንፈት አለማስተናገዳቸውም አንዱ ማሳያ ነው። በተጠቀሱት ሁለት ጨዋታዎችም ነጥብ ተጋርተው ወጥተዋል። ከውጤቱ በዘለለ ግን ቡድኑ በሜዳ ላይ ያሳየው ጥሩ እንቅስቃሴ ለቡድኑ መሻሻል ትልቁ ምስክር ነው። በጊዜ ሂደት ኳስን ተቆጣጥሮ የሚጫወት ቡድን የገነባው አሰልጣኝ ሙሉጌታ ምሕረት በነገው ጨዋታ ዕድሎችን ወደ ግብነት የመለወጥ ችግር ያለበት ቡድን ላይ ማሻሻያ ማድረግ ግድ ይለዋል፤ ተጋጣሚያቸው ጠንካራ ተከላካይ ክፍል ያለው ባህርዳር ከተማ መሆኑ ደግሞ ለውጡን አንገብጋቢ ያደርገዋል። ከዚህ በተጨማሪ ከአስከፊው ሽንፈት አገግሞ ባለፉት ሁለት ጨዋታዎች አንድ ግብ ብቻ የተቆጠረበት የቡድኑ ተከላካይ ክፍል ጥንካሬውን ማስቀጠል ይጠበቅበታል።

ከሦስት ጨዋታዎች አራት ነጥቦች የሰበሰቡት የጣና ሞገዶቹ በሊጉ በእኩሌታ የድል፣ አቻና ሽንፈት ውጤቶች አስመዝግበዋል። ባህርዳሮች በፈጣን ሽግግር ለማጥቃት የሚሞክር ጠንካራ የማጥቃት አጨዋወት አላቸው። በየጨዋታው በአማካይ ሁለት ግቦችን ማስቆጠራቸውም የማጥቃት አጨዋወታቸውን አስፈሪነት ቁልጭ አድርጎ ያሳያል።
ሆኖም የቡድኑ ሚዛን በርካታ ጥያቄ ይነሳበታል፤ ቡድኑ ምንም እንኳ ጠንካራ የተከላካይ ክፍል ቢኖረውም በአማካይ ክፍሉ በቂ ሽፋን ይሰጠዋል ብሎ ደፍሮ መናገር አይቻልም። በጨዋታ በአማካይ ሁለት ግቦች ማስተናገዳቸውም እምብዛም በማጥቃት ላይ ያተኮረው የአማካይ ጥምረታቸው ለተከላካይ ክፍሉ በቂ ሽፋን አለመስጠቱ እንደማሳያ መጥቀስ ይቻላል።

የባህር ዳር ከተማን የቡድን ዜና ለማግኘት ያደረግነው ጥረት ያልተሳካ ሲሆን ወልቂጤዎች መሳይ ፓውሎስ እና አቡበከር ሳኒን በጉዳት ምክንያት አያሰልፉም።

ወልቂጤ እና ባህር ዳር ከዚህ ቀደም ስድስት ጊዜ ተገናኝተዋል። በግንኙነታቸውም ባህር ዳር ሁለት ጊዜ ሲረታ ወልቂጤ በበኩሉ ሁለቱን አሸንፏል ፤ ሁለት ጊዜ ደግሞ አቻ ተለያይተዋል። በአምስቱ ጨዋታዎች ባህር ዳር ከተማ አምና በሁለተኛው ዙር 4-0 የረታበትን ጨምሮ ዘጠኝ ግቦች ሲያስቆጥር ወልቂጤ ከተማዎች ደግሞ አምስት ጊዜ ኳስ እና መረብ አገናኝተዋል።

ተከተል ተሾመ ጨዋታውን በመሀል ዳኝነት ይመራል። ኢንተርናሽናል ረዳት ዳኛ ፋሲካ የኋላሸት እና ኤፍሬም ኃይለማርያም ደግሞ የጨዋታው ረዳቶች ናቸው፤ ሔኖክ አክሊሉ በበኩሉ በአራተኛ ዳኝነት ተሰይሟል።