ሪፖርት | ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ወደ ድል ተመልሷል

አምስት ግቦች በተቆጠሩበት እና ለተመልካች ሳቢ የሆነ ፉክክር በተደረገበት የምሽቱ ጨዋታ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ድሬዳዋ ከተማን 3-2 ረቷል።

ምሽት ላይ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከድሬዳዋ ከተማ ሲገናኙ ንግድ ባንኮች ከመቻሉ ጨዋታቸው የሦስት ተጫዋቾችን ለውጥ አድርገዋል። ካሌብ አማንክዋን በእንዳለ ዮሐንስ ፣ ፉዓድ ፈረጃን በሀብታሙ ሸዋለም እና ቢኒያም ጌታቸውን በሳይመን ፒተር ሲቀይሩ ድሬዳዋ በአንፃሩ ከሀዋሳ ያለ ጎል ያጠናቀቀውን ስብስብ ዛሬም ደግመው ገብተዋል።

ምሽት 12 ሰዓት ላይ በተጀመረው ጨዋታ በመጀመሪያ ሃያ ደቂቃዎች በሁለቱም በኩል ተጠቃሽ የሆነ የማጥቃት ሂደት ያልተመለከትንበት ሲሆን በመጠኑ ግን ድሬዳዋ ከተማዎቸ በቁጥር በዝተው ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል መድረስ ችለው ነበር። ሆኖም ግን 18ኛው ደቂቃ ላይ አቤል አሰበ ከሳጥኑ የግራ ክፍል ላይ አግኝቶት ካልተጠቀመበት አጋጣሚ ውጪ የጠራ የግብ ዕድል ለመፍጠር ተቸግረዋል።

ብርቱ ፉክክር በታየባቸው የአጋማሹ የመጨረሻ 25 ደቂቃዎች ንግድ ባንኮች ከነበራቸው የጨዋታ ግለት ይበልጥ በመሻሻል በጠንካራ የማጥቃት እንቅስቃሴ 20ኛው ደቂቃ ላይ ጨዋታውን መምራት ጀምረዋል። ግቡንም አዲስ ግደይ ከመሃል በተሰነጠቀለት ኳስ ከግራ መስመር የግብ ጠባቂው ዳንኤል ተሾመን የጊዜ አጠባበቅ ስህተት ተጠቅሞ ማስቆጠር ችሏል።

ጨዋታውን መምራት በጀመሩበት ቅጽበት ለተከታታይ አስር ደቂቃዎች በተሻለ የራስ መተማመን ጨዋታውን ማስኬድ የቀጠሉት ባንኮች 28ኛው ደቂቃ ላይም መሪነታቸውን አጠናክረዋል። ሳይመን ፒተር ወደ ግብ ያደረገውን ሙከራ ግብ ጠባቂው ዳንኤል ተሾመ ሲመልስበት ያንኑ ኳስ ለማስቆጠር ምቹ ቦታ ላይ የነበረው ኪቲካ ጅማ በቀላሉ ማስቆጠር ችሏል።

በመጀመሪያ ደቂቃዎች ከነበራቸው እንቅስቃሴ እየተቀዛቀዙ የሄዱት ድሬዎች በሁለት ግብ ልዩነት ከተመሩ በኋላ በድጋሚ በማንሠራራት የንግድ ባንክን የተከላካይ መስመር መፈተን ጀምረዋል። በዚህ እንቅስቃሴያቸውም 33ኛው ደቂቃ ላይ ተሳክቶላቸው ግብ አስቆጥረዋል።

 

አሰጋኸኝ ጴጥሮስ ከቀኝ መስመር ያሻገረለትን ኳስ አቤል አሰበ በግንባሩ በመግጨት መረቡ ላይ አሳርፎታል። ብርቱካናማዎቹ 41ኛው ደቂቃ ላይም በኤፍሬም አሻሞ አማካኝነት ከሳጥን ውጪ ጥሩ ሙከራ አድርገው በኳሱ አቅጣጫ የነበረው ግብ ጠባቂው ፍሬው ጌታሁን ይዞታል።

ከዕረፍት መልስ ጨዋታው በተመሳሳይ ሂደት ሲቀጥል አጋማሹ በተጀመረ በአንድ ደቂቃ ውስጥ ድሬዳዋ ከተማዎች ግብ ለማስቆጠር እጅግ ተቃርበው ነበር። በሳጥኑ የግራ ክፍል ኳስ ይዞ የገባው አቤል አሰበ ያደረገው ግሩም ሙከራ በግቡ የቀኝ ቋሚ በኩል ለጥቂት ወጥቶበታል። በሁለት ደቂቃ ልዩነትም ንግድ ባንኮች ከራሳቸው የግብ ክልል በትክክል ያላራቁትን ኳስ ኤልያስ አህመድ አግኝቶት ለቻርለስ ሙሴጌ ቢያቀብለውም ዝግጁ ያልነበረው ቻርለስ የግብ ዕድሉን ሳይጠቀምበት ቀርቷል።

እንደ መጀመሪያው አጋማሽ ሁሉ በሁለተኛው አጋማሽም ዝግ ብለው ወደ ጨዋታው ግለት የገቡት ባንኮች 53ኛው ደቂቃ ላይ ጥሩ የግብ ዕድል ፈጥረው ሱሌይማን ሐሚድ ከሳጥን አጠገብ ያደረገውን ሙከራ የመሃል ተከላካዩ መሐመድ አብዱልጋኒዩ ተደርቦ አምክኖበታል። ሆኖም በሁለቱም በኩል በሚደረጉ የማያቋርጡ የሽግግር እንቅስቃሴዎች ተመጣጣኝ ፉክክር እያስመለከተን በቀጠለው ጨዋታ 65ኛው ደቂቃ ላይ ባንኮቹ መሪነታቸውን በሁለት ግብ ልዩነት በማድረግ አጠናክረዋል። አዲስ ግደይ በተረከዙ በመምታት በቄንጥ ያቀበለውን ኳስ በሳጥኑ የግራ ክፍል ላይ የነበረው ተቀይሮ የገባው በረከት ግዛው ኳሱን ወደ ግብ ሲመታው ባሲሩ ዑመር የመጨረሻ ኳሱን በመንካት ግብ እንዲሆን አድርጎታል።

እንደ መጀመሪያው አጋማሽ በሁለት ግብ ልዩነት መመራት ከጀመሩ በኋላ የተጫዋቾች ቅያሪ በማድረግ ተጭነው የተጫወቱት ድሬዎች በተደጋጋሚ ወደ ተጋጣሚ የግብ ሳጥን ቢደርሱም 76ኛው ደቂቃ ላይ ቻርለስ ሙሴጌ ከሳጥን ውጪ በግራ እግሩ መትቶት በግቡ አግዳሚ በኩል ለጥቂት ከወጣበት ግሩም ሙከራ ውጪ ለግብ የቀረበ ሙከራ ለማድረግ ተቸግረዋል። ሆኖም ግን በቀሪዎቹ ደቂቃዎችም ድሬዎች በኳስ ቁጥጥሩ መጠነኛ ብልጫ በመውሰድ ተጨማሪ ግብ ፍለጋ መታተራቸውን ሲቀጥሉ 93ኛው ደቂቃ ላይ ተቀይሮ የገባው ካርሎስ ዳምጠው ከግብ ጠባቂ በተመለሰ ኳስ ግብ አስቆጥሮት ጨዋታው በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 3-2 አሸናፊነት ተጠናቋል።