የአሰልጣኞች አሰተያየት | ሀዋሳ ከተማ 0-0 ኢትዮጵያ መድን

ያለ ጎል ከተጠናቀቀው የዕለቱ ቀዳሚ ጨዋታ በኋላ ሁለቱም አሰልጣኞች ስለ ጨዋታው ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ቆይታ አድርገዋል።

አሰልጣኝ ገብረመድኅን ኃይሌ – ኢትዮጵያ መድን

ስለ ጨዋታው …

“መጥፎ አይደለም። ሀሳባችን ኳሱን ተቆጣጥረን ፣ የእነርሱን  የዓየር ኳስ የበላይነት ስላላቸው ብዙ ባለመጠቀም ኳሱን ተቆጣጥረን ማጥቃት ላይ አንድ ነገር ለማድረግ ነበር ሀሳባችን ግን ማጥቃት ላይ ብዙም አልነበርንም ዛሬ በአጠቃላይ ሲታይ ጥሩ ነው ፣ ማሸነፍ ይገባን ነበር ፣ ብዙ አጋጣሚዎችን የመፍጠር ችግር ታይቶብናል። አቻው አይገባንም ፤ እንቀበለዋለን።”

ከነበራቸው የሽግግር አጨዋወት ተቀዛቅዘው ዛሬ ስለ ቀረቡበት መንገድ…

“ያለፈው ሽንፈት የፈጠረው ችግር እርሱ አንድ ነገር ነው። በስነ ልቦና የሚፈጥረው ጉዳት አለ። ከዛ ውጪ የተወሰኑ ኳሶችን በቁጥጥር ስር አድርገን የበላይነት ወስደን ለማጥቃት ነው ሀሳባችን ፣ ስለዚህ የታክቲክ ለውጥ በመኖሩ ቶሎ ቶሎ የሽግግር አጨዋወት አልነበረም። ይሄን ለማድረግ ፈጣን ኳሶችን መጠቀም አለብህ ያ አቀዛቅዞታል። ከዕረፍት በኋላ ግን ፈጠን ፈጠን እያልን እንድንሄድ ለማድረግ ለውጥ አድርገናል ፣ የአጨዋወት ስታይልም ለውጥ አድርገናል እና ዝናቡም ትንሽ ማካፋቱ ተቆጣጥረህው የነበረውን ነገር እንደ አዲስ መላመድ ያስፈልጋል እርሱ የፈጠረብን ችግር ካልሆነ በስተቀር ደህና ነው።”

ሐቢብ ከማል እና ተካልኝ ደጀኔ ከጉዳት የሚመለሱበት ቀን…

“አናውቀውም ፣ ለሚቀጥለው ጨዋታ ላይ የመድረሳቸው ነገር አጠራጣሪ ነው ነገር ግን ከአምስተኛ ሳምንት ጨዋታ በኋላ ከዕረፍት መልስ በዕርግጠኝነት መድረስ ይችላሉ።”

አሰልጣኝ ዘርዓይ ሙሉ – ሀዋሳ ከተማ

ስለ ሁለቱ አርባ አምስት ደቂቃዎች…

“እጅግ የታክቲካል ጨዋታ ነው ማለት ይቻላል ፣ ምክንያቱም እነርሱ ኳስ ሲያገኙ የሚጫወቱበት ቦታ ላይ እኛም ስናገኝ የምንጫወትበት ቦታ ተመሳሳይ ነው። በይበልጥ ጎላችንን ጠብቀን ነበር ሁለታችንም ስንጫወት የነበረው ፣ በተለይ ከዕረፍት በፊት ብዙ አማራጮችን አግኝተን ነበር ያለ መጠቀማችን ሁለተኛው አጋማሽ ላይ ግን ጥንቃቄን መርጠን ነው ስንጫወት የነበረው። በምናገኘው ኳስ የተጫዋች ለውጥ ብናደርግም እንቅስቃሴው በዛው ልክ የእነርሱም ለውጥ በተለይ ወርደው መከላከል የሚችሉ ተጫዋቾች ሲገቡ ስለነበር ጨዋታው ተመጣጣኝ ነው ማለት ይቻላል። ከዕረፍት በፊት ግን ወደ 35 ደቂቃ ኳሱን በደንብ ተቆጣጣረነው ነበር ፣ ከዕረፍት በኋላም ሲጀመር አንድ ሃያ ደቂቃ ተመሳሳይ ነበር። መጨረሻ ሰዓቱ ሲያልቅ ግን ተከላካዩን ጠብቀን በመልሶ ማጥቃት ለመሄድ ነበር ያሰብነው ዞሮ ዞሮ መጥፎ አይደለም።”

ከዕረፍት በኋላ ያለፉትን ሦስት ጨዋታዎች ጠንካራ ስለ መሆኑ ዛሬ ግን ስለ መቀዛቀዙ…

“አዎ ከዕረፍት በፊት የምናገኛቸው አጋጣሚዎች ብዙ ኃይል ነው ያወጣንባቸው ፣ ተነጋግረን የገባነው ከዕረፍት በፊት ጫናውን ፈጥረን ጎል ለማግባት ነበር ያ ስላልተሳካ ግን እስከ መጨረሻው ደቂቃ ድረስ የነበሩ ተጫዋቾች ናቸው የቀጠሉት ፣ ስለዚህ የአቅም ችግር የለብንም ግን ጎሉን ጠብቀን መጫወቱ አስፈላጊ ስለነበር ብዙ ሳንሄድ የቆየነው እንጂ ተመሳሳይ ነው። አንዳንዴ ከምትገጥመው ቡድን ጋር ያንን ታሳቢ ስለምናደርግ በእርሱ ከዕረፍት በኋላ ያለው ነገር የወረደ ይምሰል እንጂ የወረደ አይደለም ፣ ግን በጣም አሁንም እያገኘን ነበር መረጋጋቶቹ ይቀራሉ ፊት ላይ እርሱን ለማስተካከል እንሞክራለን።”

የአማካይ ተጫዋቾች የማጥቃት ሚና የተገደበ ስለ መሆኑ…

“መሃሉ ላይ ብልጫውን ለመውሰድ አስበን ነበር ብልጫውንም ወስደናል። በተለይ ከዕረፍት በፊት ፣ ከዕረፍት በኋላ ግን በይበልጥ አጥቂ የሆነውን ታፈሰንም ለማስገባት ሞክረናል። እነርሱ ታክቲካሊ ዲሲፕሊን ሆነው ቆመው ስለነበሩ ክፍተቶችን ብዙ አላገኘንም። የመሃል ተከላካዮቻቸው ወደ ኋላ ሸሽተው ስለሚጫወቱ የመሮጫ ቦታ አላገኘንም። አንዳንዴ ሁለቱንም ባላንስ ያደረገ ነበር የመጀመሪያ ፎርሜሽናችን በእርሱ ነው ዘጠናውንም ያስቀጠልነው ማለት ይቻላል።”