በሞሮኮ ሲሰጥ የነበረው የካፍ ኤሊት ኢንስትራክተሮች ሥልጠና በትናንትናው ዕለት ተጠናቀቀ

ኢትዮጵያዊው የካፍ ኤሊት ኢንስትራክተር አብረሀም መብራቱ በሰልጣኝነት እና በአሰልጣኝነት ሲሳተፉበት የነበረው የካፍ ኤሊት ኢንስትራክተሮች እና የጀማሪ ሴት ኢንስትራክተር ሥልጠና ፍፃሜውን አግኝቷል።

የአፍሪካ እግርኳስ ማህበር (ካፍ) ከፊፋ ጋር በመተባበር በሞሮኮ ራባት ከተማ ለአስራ ስድስት የአፍሪካ ወንድ ኤሊት ኢንስትራክተሮች ሥልጠና ለአንድ ሳምንት ያህል ሲሰጥ ቆይቶ በዛሬው ዕለት ተጠናቋል። ካፍ ለቀጣዮቹ ሦስት ዓመታት በኤሊት ደረጃ የሚገኙ አስራ ስድስት ከፍተኛ የአህጉሪቱ ኢንስትራክተሮች ራሳቸውን እንዲያበቁ እና የሚሰጧቸውም ሥልጠናዎች እንዲያድጉ በሚል ያዘጋጀው የሪፍሬሽመንት ሥልጠና ነው በትናንትናው ዕለት ሊጠናቀቅ የቻለው። ካፍ ከዓለም አቀፍ የእግርኳስ ተቋም ፊፋ ጋር በትብብር ባዘጋጀው በዚህ ሥልጠና ላይ የካፍ ኤሊት ኢንስትራክተር አብረሀም መብራቱ ተሳታፊ ሆነዋል።

ሥልጠናውን በመስጠት ፊፋን በመወከል የፊፋ ኮች ኢንዲኬተር ዳይሬክተር ሚስተር ብራንኮ ቨርኒች የተገኙ ሲሆን ካፍን በመወከል የሴቶች እግር ኳስ ልማት ዳይሬክተሯ ኢትዮጵያዊቷ መስከረም ጎሽሜ በአስተባባሪነት ተሳትፋበታለች። በሥልጠናው ላይ ተሳታፊ በመሆን በተሳካ ሁኔታ ማጠናቀቅ የቻሉት እነዚህ ሰልጣኞች ለቀጣዮቹ ሦስት ዓመታት በአህጉሩቱ የሚሰጡ ኮርሶችን መስጠት እና መታዘብም እንደሚችሉ ተጠቁሟል።

ከኤሊት ኢንትስትራክተሮች ሥልጠና ጎን ለጎን በተመሳሳይ ኢትዮጵያዊው የካፍ ኢንስትራክተር አብረሀም መብራቱ ከናሚቢያዊቷ ጃኪ ቺፓንዳ እና ከአይቮሪኮስት ዜግነት ካላት ክሌመንቲ ቱሬ ጋር በጋራ በመሆን በአሰልጣኝነት የተሳተፉበት የካፍ አዲስ ሴት ኢንስትራክተሮች ሥልጠናም በዛው ሞሮኮ ሲሰጥ ቆይቶ ትናንት መጠናቀቁን ሶከር ኢትዮጵያ ለማወቅ ችላለች።