ከፍተኛ ሊግ | አዲስ አበባ ከተማ የአዳዲስ ተጫዋቾችን ዝውውር ፈፅሟል

በኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ተሳታፊው አዲስ አበባ ከተማ የአስራ ሁለት አዳዲስ ተጫዋቾችን ዝውውር ሲያጠናቅቅ የነባሮቹን ውልም አድሷል።

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ላይ ሁለት ጊዜያትን ያህል የመሳተፍ በለስ የቀናው አዲስ አበባ ከተማ በ2014 የውድድር ዘመን ከፕሪምየር ሊጉ ከወረደ በኋላ ከተጠናቀቀው ዓመት ጀምሮ በከፍተኛ ሊጉ እየተወዳደረ ዳግም ወደ ሀገሪቱ ትልቁ የሊግ ዕርከን ለመመለስ እየተሳተፈ እንደሚገኝ ይታወሳል። ክለቡ በዘንድሮው የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ምድብ ሀ ስር የተደለደለ ሲሆን በአሰልጣኝ ጳውሎስ ጌታቸው እየተመራ አስራ ሁለት አዳዲስ ተጫዋቾችን ሲያስፈርም የአስራ አንድ ነባር ተጫዋቾችን ውል አራዝሟል።

ክለቡን የተቀላቀሉ ተጫዋቾችን ስንመለከት የቀድሞው የድሬዳዋ ፣ ስልጤ ወራቤ እና ንብ አማካይ ረመዳን ናስርን ጨምሮ ፣ ኮክ ኩዌት ግብ ጠባቂ ከጉለሌ ፣ ምስጋና ፈይሳ ተከላካይ ከይርጋጨፌ ቡና ፣ ሔኖክ ካሳሁን ተከላካይ ከአቃቂ ፣ ዳግማዊ ሙሉጌታ አማካይ ከቡታጅራ ፣ ዝናቡ ዳመነ ተከላካይ ከቦዲቲ ፣ ቢኒያም ታከለ አጥቂ ከቦዲቲ ፣ ውብሸት ክፍሌ ተከላካይ ከቦዲቲ ፣ ማቲያስ ሸመታ አጥቂ ከየካ ፣ የአብስራ አብነት ተከላካይ ከአዳማ ተስፋ ቡድን ፣ አማኑኤል አሊሴ አጥቂ ከቦዲቲ እና ግርማዬ አስፋው አማካይ ከሀላባ ሸገር የክለቡ አዳዲሶቹ ፈራሚዎች ናቸው።

ክለቡ ከአዳዲስ ፈራሚዎቹ ባለፈ ቢኒያም ፀጋዬ ተከላካይ ፣ ኤፍሬም ጌታቸው ተከላካይ ፣ ዳዊት ደግአረገ አማካይ ፣ ኤርሚያስ ሐይሉ አጥቂ ፣ ከበደ አሰፋ ተከላካይ ፣ ይሁን ገላጋይ ተከላካይ ፣ ታሪኩ ጎጀሌ አጥቂ ፣ ሙሉቀን ተስፋዬ አማካይ ፣ ሙሴ ገብረኪዳን ግብ ጠባቂ ፣ ነብዩ ዳንኤል ግብ ጠባቂ እና አዲስአለም ዘውዱ አማካይ በክለቡ ለተጨማሪ አንድ ዓመት ውላቸው ተራዝሞላቸዋል።