መረጃዎች| 16ኛ የጨዋታ ቀን

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አራተኛ ሳምንት መቋጫ የሆኑት ሁለት ተጠባቂ ጨዋታዎችን የተመለከቱ መረጃዎች እንደሚከተለው አዘጋጅተንላችኋል።

ፋሲል ከነማ ከ ኢትዮጵያ ቡና

ሁለት ሽንፈት ያላስተናገዱ ክለቦች የሚያገናኘው የሳምንቱ ትልቅ ጨዋታ የዕለቱ ቀዳሚ ፍልሚያ ይሆናል።

ከሦስት ጨዋታዎች ሁለት አቻና አንድ ድል ያስመዘገቡት ዐፄዎቹ በአምስት ነጥቦች አራተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል። የመጨረሻው ጨዋታ ላይ በተጨማሪ ደቂቃ ወሳኝ ግብ አስቆጥረው ወደ ትልቁ ጨዋታ መቅረባቸውም በውስን መልኩ ጫናዎች አርግቦላቸዋል።

ዐፄዎቹ ማግኘት ከሚገባቸው ዘጠኝ ነጥቦች አምስቱን አሳክተው በውጤት ረገድ መጥፎ የማይባል ክብረ-ወሰን ቢያስመዘግቡም እንደተጠበቀው ማራኪ የሜዳ ላይ እንቅስቃሴ አላሳዩም። አሰልጣኝ ውበቱ በድህረ ጨዋታ አስተያየት ቡድኑ ወደ ሚፈለገው ደረጃ እንዳልደረሰም አንስተዋል። ድል ባደረጉበት ጨዋታ በአመዛኙ  ቃልኪዳን እና ናትናኤል መሰረት አድርገው በመስመሮች የግብ ዕድል ለመፍጠር ጥረት ያደረጉት ፋሲሎች አጨዋወቱ በጥራትም በብዛትም እንደሚፈለገው  የግብ ዕድሎች አልፈጠረላቸውም።

በነገው ጨዋታም ብዙ ክፍተቶች የማይሰጥ እና ከፍ ባለ ጫና የሚጫወት ቡድን እንደመግጠማቸው ጨዋታውን ለመቆጣጠር ቀላል ፈተና አይጠብቃቸውም። ከዚህ በተጨማሪ በመጀመርያዎቹ ሁለት ጨዋታዎች አራት ግቦች አስተናግዶ በመጨረሻው ጨዋታ ግቡን ያላስደፈረውን የተከላካይ ክፍላቸው ጥንካሬውን ማስቀጠል ይኖርበታል።

በመጀመርያዎቹ ሁለት ጨዋታዎች ድል አስመዝግበው ባህርዳር ከተማን በገጠሙበት ጨዋታ አቻ የተለያዩት ኢትዮጵያ ቡናዎች መልካም አጀማመር አድርገው ሰባት ነጥቦችም ሰብስበዋል።

ቀጥተኛ አጨዋወት መርጠው ጨዋታዎቻቸው በማድረግ ላይ የሚገኙት ቡናማዎቹ ይበልጥ ውጤት ተኮር የመስመር አጨዋወት አላቸው። ቡድኑ በሁለቱም በማጥቃት እና በመከላከል ሂደቶች ሚዛናዊ ነው። በሁለት ጨዋታዎች ግብ ያላስተናገደውና እስካሁን ሁለት ግቦች ብቻ የተቆጠሩበት ጠንካራ የመከላከል አደረጃጀት ያላቸው ቡናማዎቹ ከሌላው የቡድኑ ክፍል አንፃር ዕድሎች ወደ ግብነት የመቀየር ችግር ያለበት የማጥቃት ክፍል አላቸው።
ከባህር ዳር ከተማ ጋር አቻ በተለያዩበት የእስካሁኑ የሊጉ ሂደት ምርጥ ጨዋታም ይህ ክፍተት በጉልህ ታይቷል። ሰርብያዊው አሰልጣኝ ኒኮላ ካቫዞቪች በነገው ጨዋታ የተለመደውን አጨዋወት ይከተላሉ ተብሎም ይጠበቃል። ሆኖም እንደ ባለፈው ጨዋታ በርካታ ዕድሎች ላለማምከን የአጥቂዎቻቸው ስልነት ከፍ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል።

ዐፄዎቹ በነገው ጨዋታ የዮናታን ፍስሃ እና አማኑኤል ገብረሚካኤል መሰለፍ አጠራጣሪ ሲሆንባቸው ፤ ኢትዮጵያ ቡናዎች በአንፃሩ ከሮቤል ተክለሚካኤል ውጪ በጉዳት የሚያጡት ተጫዋች የለም።

ሁለቱ ክለቦች በሊጉ እስካሁን 12 ጊዜ የእርስ በእርስ ጨዋታዎች አድርገዋል። በውጤቱ ፋሲል ከነማ አራት ኢትዮጵያ ቡና ደግሞ ሦስት ድሎችን ሲያሳኩ ቀሪዎቹ አምስት ጨዋታዎች ነጥብ በመጋራት ተጠናቀዋል። በጨዋታዎቹ ሁለቱ ተጋጣሚዎች በተናጠል በአማካይ አንድ ጎል እያስመዘገቡ ለነገው 13ኛ ፍልሚያቸው ሲደርሱ እስካሁን በድምሩ ዕኩል 12 ግቦች አስቆጥረዋል።

ኢንተርናሽናል ዳኛ በላይ ታደሰ የሳምንቱን ተጠባቂ ጨዋታ በዋና ዳኝነት ለመምራት ተመድበዋል። ኢንተርናሽናል ረዳት ዳኛ ፋሲካ የኋላሸት እና ኤፍሬም ኃይለማርያም ደግሞ የጨዋታው ረዳት ዳኞች ናቸው። አራተኛ ዳኛ በመሆን ደግሞ ኢንተርናሽናል ዳኛ ኃይለየሱስ ባዘዘው ተመድቧል።

ወላይታ ድቻ ከ መቻል

ሁለት ጠንካራ የአማካይ ክፍል ያላቸውን ቡድኖች የሚያገናኘው ተጠባቂ ጨዋታ አራተኛውን ሳምንት ያገባድዳል።

ማግኘት ከሚገባቸው ዘጠኝ ነጥቦች ስድስቱን አሳክተው በሦስተኛ ደረጃነት የተቀመጡት የጦና ንቦች ሁለት እና ከሁለት በላይ ድል ካስመዘገቡ ሦስት ክለቦች መካከል ይገኛሉ። ወላይታ ድቻዎች ጠንካራ የሚባል የተከላካይ ክፍል አላቸው። ጠጣር አደረጃጀቱም ዝቅተኛ የግብ መጠን (1)  ያስተናገደ ጠንካራ ጥምረት ነው ። ሆኖም በሦስት ጨዋታዎች ሁለት ግቦች ብቻ ያስቆጠረ እና ዕድሎች ወደ ግብነት የመቀየር ችግር ያለበት የማጥቃት ጥምረት አላቸው።  ቡድኑ በአማካይ በጨዋታ 0.6 ግብ ማስቆጠሩም የዚያ ማሳያ ነው። በአብነት ደምሴ ፣ አበባየሁ ሀጂሶ እና ብዙአየሁ ሰይፈ የተገነባ ጨዋታ ለመቆጣጠር የማይቸገር የአማካይ ጥምረት ያለው ኳስ የሚቆጣጠር ቡድን የገነቡት አሰልጣኝ ያሬድ ገመቹ ዕድሎች በመጠቀም ረገድ ክፍተት የሚታይበትን የአጥቂ ጥምረታቸው ውጤታማነት ከፍ የማድረግ ትልቅ የቤት ሥራ ይጠበቅባቸዋል።

ከሦስት ጨዋታዎች በእኩሌታ አንድ አንድ የድል፣ ሽንፈት እና የአቻ ውጤት ያስመዘገቡት መቻሎች በአራት ነጥብ 8ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል። ቡድኑ በመጀመርያው ጨዋታ በአንፃራዊነት ከተጋጣሚው የተሻለ የኳስ ቁጥጥር ድርሻ ቢይዝም ከጨዋታ ጨዋታ ብልጫው እየቀነሰ መጥቷል። ከንግድ ባንክ ጋር ባደረጉት ጨዋታ ግን ይባስ ብሎ ሙሉ ብልጫ ተወስዶበታል። የከነዓን ማርክነህ አለመኖርም በአማካይ ክፍሉ ላይ ክፍተት ፈጥሯል ፤ ከዚህ ቀደም ከተጫዋቹ ጋር የሰመረ መናበብ የነበረው ሽመልስ በቀለ ያሳየው እንቅስቃሴም ለዚህ ማሳያ ነው። በዚህ ምክንያት የጠሩ በርካታ ዕድሎች አልፈጠሩም።

በሦስቱም ሳምንታት አምስት ግቦች አስተናግዶ በየጨዋታው በአማካይ 1.6 ግቦች ያስተናገደ ደካማ የሚባል የተከላካይ አደረጃጀት ያለው መቻል በተጠቀሰው ሂደት ያለውን ችግር በአፋጣኝ መቅረፍ አለበት። ከዚህ በተጨማሪ በሚፈለገው መጠን ግቦችን ማምረት ያልቻለው የአጥቂ ክፍሉ የውጤታማነት ደረጃው ከፍ ማድረግ ይጠበቅበታል። ቡድኑ ምንም እንኳ አምስት ግቦች ቢያስቆጥርም ሦስቱ ከፍፁም ቅጣት ምት የተቆጠሩ እና በክፍት የጨዋታ ሂደት የተቆጠሩ ግቦች ሁለት ብቻ መሆን ግብ የማስቆጠር ችግሩን ቁልጭ አድርጎ ያሳያል።

ወላይታ ድቻ በነገው ጨዋታ መልካሙ ቦጋለን በጉዳት ምክንያት አያሰልፍም ፤ የአናጋው ባደግ መሰለፍም አጠራጣሪ ነው። በመቻል በኩል ባለፈው ጨዋታ ላይ ጉዳት ያስተናገዱት አስቻለው ታመነ እና ግሩም ሐጎስ እንዲሁም ፍፁም ዓለሙ የነገው ጨዋታ የሚያልፋቸው ሲሆን ከነዓን ማርክነህ ግን ለጨዋታው እንደሚደርስ ታውቋል።

ሁለቱ ክለቦች በሊጉ 16 ጊዜ ተገናኝተው ወላይታ ድቻ 8 ጊዜ በማሸነፍ ቀዳሚ ሲሆን መቻል 3 ጊዜ አሸንፏል ፤ በቀሪዎቹ 5 ግንኙነቶች ደግሞ አቻ ተለያይተዋል። የጦና ንቦቹ 17 ፣ ጦሩ 12 ግቦችን በእርስ በእርስ ግንኙነታቸው ማስቆጠር ችለዋል።

የጨዋታው ዋና ዳኛ ኢንተርናሽናል ዳኛ አሸብር ሰቦቃ ሆነው ሲመደቡ ኢንተርናሽናል ረዳት ዳኛ ተመስገን ሳሙኤል እና አስቻለው ወርቁ በረዳት ዳኝነት፤ ባህሩ ተካ በበኩሉ በአራተኛ ዳኝነት ተሰይሟል።