ጎፈሬ ከጂቡቲ ሪፐብሊካን ጋርድ ክለብ ጋር ስምምነት ፈፀመ

ኢትዮጵያዊው የስፖርት ትጥቅ ብራንድ ጎፈሬ ከወቅቱ የጂቡቲ ሊግ ሻምፒዮን ሪፐብሊካን ጋርድ ክለብ ጋር የሦስት ዓመት ስምምነት ተፈራረመ።

ሀገር በቀሉ የስፖርት ትጥቅ ብራንድ ጎፈሬ ከኢትዮጵያ አልፎ በምስራቅ አፍሪካ ምርቶቹን ተደራሽ በማድረግ በዩጋንዳ፣ ታንዛኒያ፣ ኬኒያ፣ ሱማሊያ እና በሌሎች የቀጠናው ሀገራት መጠነ ሰፊ ስራዎችን እየሰራ እንደሚገኝ ይታወቃል። በዛሬው ዕለት ደግሞ ከጂቡቲ ክለብ ጋር ለሦስት ዓመታት የሚቆይ የትጥቅ አቅርቦት ስምምነት ተፈራርሟል።

ረፋድ 5 ሰዓት አዲሱ ገበያ አካባቢ በሚገኘው የጎፈሬ ዋና ሾ-ሩም በተከናወነው የፊርማ ስምምነት የጎፈሬ መስራች እና ባለቤት አቶ ሳሙኤል መኮንን፣ የሪፐብሊካን ጋርድ ክለብ ፕሬዝዳንት ሚስተር ዳህር ፋራህ ባሬ እንዲሁም የጂቡቲ ኢምባሲ ተወካዮች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች እና የሚዲያ አካላት ተገኝተዋል።

በቅድሚያ ንግግር ያደረጉት አቶ ሳሙኤል በጅቡቲ ታሪክ አንድ ክለብ ከታላቅ ብራንድ ጋር ያደረገው የመጀመሪያ ስምምነት መሆኑን አውስተው ለሦስት ዓመታት በሚቆየው ስምምነት ጎፈሬ 22 የተለያዩ የትጥቅ አይነቶችን እንዲሁም የደጋፊዎች ማሊያን በቅናሽ በስፖንሰር መልክ ለክለቡ እንደሚያቀርብ አስረድተዋል።

አቶ ሳሙኤል ጨምረው ተቋማቸው ጎፈሬ በምስራቅ አፍሪካ ያለውን ተደራሽነት ለማስፋት እያደረገ ካለው መጠነ ሰፊ ስራ አንድ እርምጃ የሚያራምድ ስምምነት እንደሆነ ጠቅሰው በቅርቡም ሌሎች አዳዲስ ብስራቶችን ለኢትዮጵያ ህዝብ እንደሚያደርሱ አመላክተዋል።

2005 ላይ ምስረታውን ያደረገው የጅቡቲው ሪፐብሊካን ጋርድ ክለብ የወቅቱ የሊጉ ዋንጫ አሸናፊ ሲሆን በጥሎ ማለፍ ጨዋታዎችም ዋንጫዎችን በማግኘት የተሻለ ታሪክ ያለው ነው። የዚህ ክለብ ፕሬዝዳንት ሚስተር ባሬ በበኩላቸው ጎፈሬ የሚያመርታቸው ምርቶች ጥራታቸውን የጠበቁ መሆናቸውን በማውሳት ስምምነቱን ለመፈፀም ውሳኔ እንደወሰኑ ተናግረዋል። ክለባቸው ከጂቡቲ ፕሪምየር ሊግ ውጪም በአህጉራዊ ውድድር እንዲሁም በአረብ የተለያዩ ውድድሮች ስለሚሳተፍ ጎፈሬን በአምባሳደርነት እንደሚያስተዋውቁ ገልፀዋል።

በመጨረሻ ሁለቱ አካላት ስምምነቱን በፊርማቸው አፅንተው የፎቶ መነሳት መርሐ-ግብር ተከናውኗል።