የሴት እግርኳስ ተጫዋቾች ጤና –  ክፍል 2

ከእግርኳስ ጋር የተያያዙ የጤና መረጃዎችን በምናቀርብበት የሶከር ሜዲካል አምዳችን የዛሬ ትኩረታችን የሚሆነው በሴቶች እግርኳስ ውስጥ ያለው የአመጋገብ ስርአት ነው፡፡

በዶ/ር ብሩክ ገነነ

የሴቶች እግርኳስ ማደግ ጋር ተያይዞ የህክምና ሥርአቱም አብሮ እንዲዘምን ፊፋ የተለያዩ ጥናቶችን ሲያደርግ ቆይቷል፡፡ ጥናት ከተደረገባቸው ዘርፎችም መካከል አንዱ የስነ-ምግብ ዘርፍ ነው፡፡ እግርኳስ ተጫዋቾች መከተል ያለባቸው ራሱን የቻለ የአመጋገብ ሥርአት ሲኖር ይህ ደግሞ ከሴቶች ተፈጥሯዊ ሁኔታ አንጻር ለየት የሚልባቸው ሁኔታዎችም አሉ፡፡
የሴት ተጫዋቾች የምግብ አወሳሰድ ላይ ትኩረት ተደርጎ በተሰራ ጥናት ማወቅ እንደተቻለው ከወንድ ተጫዋቾች አንጻር ከጨዋታ አስቀድሞ የሚወስዱት የካርቦሃይድሬት መጠን አነስተኛ መሆኑን ነው፡፡ ከዚህ ጋርም ተያይዞ በጨዋታ ወቅት የሚረዳቸውን የኃይል መጠን በአግባቡ አያገኙም ማለት ነው፡፡ ለዚህም የተለያዩ ምክንያቶች ሲጠቀሱ ከእነዚህም መካከል በቂ ዕውቀት እና የባለሙያ ድጋፍ አለመኖር ይካተታሉ፡፡

ተጫዋቾች በውድድር ወቅት ያላቸውን ብቃት ማሳየት እንዲችሉ ከሚረዷቸው ነገሮች መካከል አንዱ ሳይንሳዊ የሆነ የአመጋገብ ዘይቤን መከተል ነው፡፡ ከእነዚህም መካከል ከጨዋታ በፊት የሚደረግ ካርቦሃይድሬት የያዙ ምግቦችን መመገብ (fueling) ወሳኝ ነው፡፡ ይህም ረጅም ደቂቃ በሚፈጀው የእግርኳስ ጨዋታ ወቅት ጠንክረው ግጥሚያውን ማጠናቀቅ እንዲችሉ እና ድካም ሳይሰማቸው መፎካከር እንዲችሉ ይረዳቸዋል፡፡ በተለይም ደግሞ በጥቂት ቀናት ልዩነት በሚደረጉ ውድድሮች ላይ ውጤታማ ለመሆን እንደዚህ ያለው አመጋገብ ስርዓት ወሳኝ ነው፡፡

እንደዚህ ያለው የአመጋገብ ሥርአት በአብዛኛው ተጫዋችም ሆነ አሰልጣኝ ላይ የግንዛቤ ክፍተት እንዳለ ጥናቱ ጠቁሟል፡፡ በአብዛኞቹ ዘንድ ካርቦሃይድሬት የበዛበትን ምግብ ከጨዋታ አንድ ቀን በፊት መመገብ እንዳለባቸው አያውቁም፡፡ ይልቁንም ከጨዋታ በፊት ከሚመገቡት የመጨረሻ ምግብ ጋርም የማምታታት ጉዳይ ይስተዋላል፡፡ ከጨዋታ በፊት የሚገባቸውን የካርቦሃይድሬት መጠን መውሰድ ያልቻሉ ተጫዋቾች ሜዳ ላይ ኃይል ከማጣት በተጨማሪ የወር አበባ በጊዜው አለመምጣትም ተያይዞ አጋጥሟቸዋል፡፡ አንዳንድ ተጫዋቾች ደግሞ ካርቦሃይድሬት የበዛበትን ምግብ መመገብ ውፍረት እንድጨምር ያደርገኛል የሚል ስጋት አድሮባቸዋል፡፡ በተለይም የውፍረት ጉዳይ ከሴት ተጫዋቾች ጋር መወያያ ርዕስ ሊሆን እንደሚችል ማሰብ እንችላለን፡፡ በተለይም በዚህ የማህበራዊ ሚዲያ ዘመን ተጫዋቾች ክብደት ጋር ተያይዞ ሊሰጡ የሚችሉ አስተያየቶች ጫና ውስጥ ሲከቷቸው ይስተዋላል፡፡ ከጨዋታ በፊት ብዙ ካርቦሃይድሬትን መጠቀምም ሆነ ከጨዋታ መልስ ከፕሮቲን ሼክ ጋር ካርቦሃይድሬትን ጨምሮ መጠቀም በብዙ ተጫዋቾች ዘንድ ተመራጭ ሳይሆን ሲቀር ተስተውሏል፡፡

ከምንም ነገር በላይ ተጫዋቾቹ በእውቀት ላይ የተመሰረተ የሥነ-አመጋገብ ስርአት እንዲከተሉ ለማስቻል የማያቀርጥ የባለሙያ ድጋፍ ያስፈልጋቸዋል፡፡ በባለሙያ የሚደረጉ ድጋፎች ከክለብ ክለብ የተለያዩ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ከዚህ ጋርም ተያይዞ ተጫዋቾች ለብሄራዊ ቡድን በሚመረጡበት ወቅት የሚያጋጥማቸው የሥነ-ምግብ ስርአት ከለመዱት ለየት ያለ ሊሆንባቸውም ይችላል፡፡