የኢትዮጵያ ዋንጫ | የሁለተኛ ዙር የመጀመሪያ ቀን ውሎ

የኢትዮጵያ ዋንጫ ሁለተኛ ዙር ጨዋታዎች ዛሬ አዲስ አበባ ፣ አዳማ እና ሀዋሳ ላይ ተከናውነው ስድስት አላፊ ቡድኖች ተለይተዋል።

የ07:00 ጨዋታዎች

አዲስ አበባ አበበ ቢቂላ ስታዲየም ላይ ኮልፌ ቀራኒዮ ክ/ከተማ እና ኢትዮ ኤሌክትሪክ ሲገናኙ መጠነኛ ፉክክር በተደረገበት የመጀመሪያ አጋማሽ በመጀመሪያዎቹ 20 ደቂቃዎች ኤሌክትሪኮች በቀሪዎቹ 25 ደቂቃዎች ደግሞ ኮልፌዎች በኳስ ቁጥጥሩ ብልጫ መውሰድ ችለዋል። ሆኖም በሁለቱም በኩል ያን ያህል ፈታኝ የማጥቃት እንቅስቃሴ አልተደረገም።

ከዕረፍት መልስ ጨዋታው በተጀመረ በሴኮንዶች ውስጥ ኤሌክትሪኮች ግብ ለማስቆጠር እጅግ ተቃርበው የኮልፌው ግብ ጠባቂ በግሩም ቅልጥፍና ሲያመክንባቸው 48ኛው ደቂቃ ላይ ኮልፌዎች ጨዋታውን መምራት ጀምረዋል። ግቡንም በሳጥኑ የቀኝ ክፍል ኳስ ይዞ የገባው ቃለጌታ ምትኩ በተረጋጋ አጨራረስ ማስቆጠር ችሏል። ኤሌክትሪኮች ግብ ከተቆጠረባቸው በኋላ ተጭነው በመጫወት በርካታ የግብ ዕድሎችን መፍጠር ቢችሉም ሳይጠቀሙበት ቀርተው ጨዋታው በኮልፌ ቀራኒዮ ክ/ከተማ 1-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።

አዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርስቲ ሜዳ በተካሄደው ድሬደዋ ከተማ ከኢትዮጵያ መድን ያገናኘው ጨዋታ በሁለቱም በኩል አጀማመራቸው ጥንቃቄ የበዛበት በመሆኑ እንቅስቃሴያቸው ቀዝቀዝ ያለ ቢመስልም  ከ25ኛው ደቂቃ በኋላ ጨዋታው ወደ ጥሩ ፉክክር ተቀይሮ ጎል ሊቆጠርም ችሏል።

29ኛው ኢትዮጵያ መድኖች በጥሩ ቅብብል ሳጥን ውስጥ የተቀበለውን ኳስ አጥቂው ቹኩዌሜካ ጎድሰን ወደ ጎልነት በመቀየር ቡድኑን ቀዳሚ አድርጎል። ከዚህ ጎል መቆጠር በኋላ በተደጋጋሚ ወደ መድኖች የሜዳ ክፍል በመድረስ ጥቃት የሰነዘሩት ድሬዎች በ41ኛው ደቂቃ ከሳጥን ውጭ በጥሩ ዕርጋታ እና ዕይታ አንበሉ ዳዊት እስጢፋኖስ ግሩም ጎል አስቆጥሮ ቡድኑን አቻ በማድረግ ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።

በመጀመርያው አጋማሽ የመጨረሻው ደቂቃዎች በጥሩ ፉክክር ጎሎች ተስተናገደውበት መጠናቀቁን ተከትሎ በሁለተኛው አጋማሽ የተሻለ እንቅስቃሴ በሁለቱም ይኖራል ተብሎ ቢጠበቅም መሐል ሜዳ ላይ የተገደበ ብዙ የጎል ሙከራ ያልተደረገበት ሆኖ አልፏል። ሆኖም ውጤቱን በመፈለግ ወሳኝ ተጫዋቾቻቸውን ቀይረው ያስገቡት መድኖች በ85ኛው ደቂቃ ላይ በያሬድ ደርዛ አማካኝነት ጎል አስቆጥረው ወደ ሦስተኛው ዙር የጥሎ ማለፍ ጨዋታ ማለፋቸውን አረጋግጠዋል።

ሀዋሳ ሰው ሰራሽ ሜዳ ላይ የጥሎ ማለፉ የሁለተኛ ዙር መርሀግብር የመጀመሪያ ጨዋታ ደብረብርሃን ከተማን ከጋሞ ጨንቻ ጋር ያገናኘ ነበር። አሰልቺ የሆኑ የሜዳ ላይ እንቅስቃሴዎችን ባስመለከተን የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ በመጀመሪያው የጨዋታ አጋማሽ ቡድኖቹ በተመሳሳይ የጨዋታ መንገድ ለጨዋታው የቀረቡ ሲሆን ደብረብርሃኖች ከቆሙ እና ከመሐል ሜዳ በሚደረጉ ሰንጣቂ ኳሶች ወደ ተጋጣሚ የሜዳ ክፍል ለመድረስ ጥረት ሲያደርጉ በአንፃሩ ጋሞ ጨንቻዎች በሽግግር ለመጫወት ጥረት ሲያደርጉ ብንመለከትንም በጨዋታው የተመለከትነው ሁለት ሙከራን ብቻ ነበር። 22ኛው ደቂቃ ላይ ከቀኝ ወደ ውስጥ የደረሰውን ኳስ ለገሠ ዳዊት ወደ ጎል ሲሞክር ተጫዋቹ ሀይል የለሽ በሆነ ምት ታምራት ዳኜን በቀላሉ አሳቅፎታል። በሌላ ሙከራ አጋማሹ ሊገባደድ በቀረው አንድ ደቂቃ ውስጥ ከቅጣት ምት ወደ ግብ ክልል ሲሻማ ኪሩቤል በቀለ በግንባር ገጭቶ ሲሞክር ግብ ጠባቂው ታምራት ዳኜ በጥሩ ቅልጥፍና ኳሷን ወደ ውጪ አውጥቶበታል።

ጨዋታው ከዕረፍት መልስም ተመልሶ ሲቀጥል አሁንም በተቀዛቀዙ እንቅስቃሴዎች በይበልጥ የታጀበ ከሙከራዎችም የተገደበ መሆን በመቻሉ የጠሩ ዕድሎችን ሳያስመለከትን መደበኛው ደቂቃ ያለ ጎል 0ለ0 ተቋጭቷል። ጨዋታውም ያለ ጎል መፈፀሙን ተከትሎ በተሰጠው የመለያ ምት ደብረብርሃን ከተማ በግብ ጠባቂው ታምራት ዳኜ አስደናቂ የሆነ ብቃት ታግዞ 4ለ2 በማሸነፍ ወደ ቀጣዩ ዙር ማለፉን አረጋግጧል።

የ09:30 ጨዋታዎች

አዲስ አበባ አበበ ቢቂላ ላይ ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ሀምበሪቾ ሲገናኙ ቀዝቃዛ በነበረው የመጀመሪያ አጋማሽ ፈረሠኞቹ 10ኛው ደቂቃ ላይ ጨዋታውን መምራት ጀምረዋል። ተገኑ ተሾመ ከሳጥኑ የግራ ክፍል ላይ ሆኖ ያሻገረው ኳስ በተከላካይ ተጨርፎ ያገኘው አማኑኤል ኤርቦ መረቡ ላይ አሳርፎታል። ከግቧ መቆጠር በኋላ በተጫዋቾች መካከል በሚደረገው ጉሽሚያ እና በዳኛው ተደጋጋሚ ፊሽካ ጨዋታው ይበልጥ እየተቀዛቀዘ ሲሄድ አጋማሹ ሊጠናቀቅ በተጨመሩ የባከኑ ደቂቃዎች ውስጥ ጊዮርጊሶች ተጨማሪ ግብ አስቆጥረዋል። ተገኑ ተሾመ እንደ መጀመሪያው ግብ ሁሉ ከሳጥኑ የግራ ጠርዝ ላይ ያሻገረውን ኳስ ናይጄሪያዊው አጥቂ ሞሰሰ ኦዶ ግብ አድርጎታል።

ከዕረፍት መልስ የጨዋታው ግለት ተሻሽሎ ሲቀጥል ሀምበሪቾዎች የተጫዋቾች ቅያሪ በማድረግ የማጥቃት እንቅስቃሴያቸውን አጠናክረዋል። የአጋማሹ የመጀመሪያ ለግብ የቀረበ ሙከራም 69ኛው ደቂቃ ላይ ሲደረግ በጨዋታው ማራኪ እንቅስቃሴ ማድረግ የቻለው ተገኑ ተሾመ በግሩም ክህሎት እየገፋ በወሰደው ኳስ ከሳጥን አጠገብ ያደረገውን ሙከራ በኳሱ አቅጣጫ የነበረው ግብ ጠባቂው ፖሉማ ፖጁ ሲይዝበት በአንድ ደቂቃ ልዩነት ሀምበሪቾዎች ግብ አስቆጥረው ወደ ጨዋታው ለመመለስ ጥረት አድርገዋል። በግራ መስመር ከማዕዘን የተሻገረው ኳስ በሌላ ተጫዋች ተገጭቶ ተቀይሮ የገባውን አፍቅሮት ሰለሞንን ገጭቶ ግብ ሆኗል። ሀምበሪቾዎች በኳስ ቁጥጥሩ ብልጫ በመውሰድ በፈጣን ሽግግሮች ወደ አቻነት ለመመለስ ጥረት ቢያደርጉም የግብ ዕድሎችን በመፍጠሩ በኩል ፈረሠኞቹ ብልጫ ወስደዋል። በዚህም 75ኛው ደቂቃ ላይ ዳዊት ተፈራ 78ኛው ደቂቃ ላይ ደግሞ አማኑኤል ኤርቦ ያደረጓቸውን ሙከራዎች ግብ ጠባቂው ፖሉማ ፖጁ አምክኖባቸዋል። ጨዋታውም በቅዱስ ጊዮርጊስ 2-1 አሸናፊነት ተጠናቋል።

አዳማ ላይ የዕለቱ ሁለተኛ ጨዋታ የነበረው ፋሲል ከነማን ከነቀምቴ ከተማ ዐፄዎቹ በነቀምቴ ተፈትነው አሸንፈው ወጥተዋል። 11ኛው ደቂቃ ከቅጣት ምት የተሻገረውን በተከላካዮች ተደርቦ የተገኘውን ኳስ ምኞት ደበበ አግኝቶ ወደ ጎልነት በመቀየር ፋሲል ከነማን ቀዳሚ በማድረግ ችሏል። ጎል ቢስተናገድባቸውም የፋሲልን የግብ ክልል በተደጋጋሚ እየተመላለሱ ሲፈትሹ የቆዮት ነቀምቴዎች በተለይ አቻ መሆን የሚችሉበትን አጋጣሚ ኢብሳ በፍቃዱ ብቻውን ከፋሲል ግብጠባቂ ጋር ተገናኝቶ ሚካኤል ሳማኪ ያዳነበት ኳስ የሚያስቆጭ ነበር።

በሁለተኛው አጋማሽ ወደ ጨዋታ የሚመልሳቸውን ጎል ፍለጋ ጥረት ማድረጋቸውን የቀጠሉት ነቀምቴዎች በተደጋጋሚ የፋሲልን ተከላካዮች ሲረብሽ በነበረው ሰለሞን ጌታቸው ነፃ የጎል አጋጣሚ አግኝቶ ግብጠባቂው ሚካኤል ሳማኪ አምክኖበታል። የጨዋታው ደቂቃ እየገፋ በሄደ ጊዜ መዳከም የታየባቸው ነቀምቴዎች በተከታታይ ደቂቃዎች ሁለት ጎሎችን ማስተናገዳቸው እንቅስቃሴያቸው እንዲወርድ ሆኗል።

71ኛው ደቂቃ ከመስመር የተላከለትን ፍቃዱ አለሙ በማስቆጠር የቡድኑን የጎል መጠን ወደ ሁለት ከፍ ያደረገ ሲሆን ከሦስት ደቂቃ በኋላ ሳጥን ውስጥ ፍቃዱ አለሙ በመቀስ ምት ለራሱ ሁለተኛ ለቡድኑ ሦስተኛ ጎል በማስቆጠር ዐፄዎቹን እፎይታ ውስጥ በመክተት በቀሩት ደቂቃዎች ጨዋታውን ተቆጣጥረው ተጨማሪ ጎሎች ማስቆጠር የሚችሉበትን ዕድሎች ቢፈጥሩም የተለየ ነገር ሳያደርጉ ጨዋታውን 3-0  በሆነ ውጤት በመርታት ወደ ቀጣዩ ዙር ማለፋቸውን አረጋግጠዋል።

ሀዋሳ ላይ የፕሪምየር ሊጉን ክለብ ወላይታ ድቻን ከደሴ ከተማ ጋር ያገናኘው መርሀግብር ጥሩ የሆነ ፉክክርን አስመልክቶን በወላይታ ድቻ ድል አድራጊነት ተፈፅሟል። ተመጣጣኝ የሚመመስል የጨዋታ ቅርፅን ነገር ግን የወላይታ ድቻ የተደራጀ የማጥቃት ቅርፅን በተመለከትንበት ጨዋታ በቀዳሚው የጨዋታ አጋማሽ ድቻዎች መሐል ሜዳውን በአግባቡ ተቆጣጥሮ በመጫወት እና በተለይ ደግሞ የደሴ ተከላካዮች የሚሰሩትን የቅብብል ስህተት በመጠቀም ግቦች ለማስቆጠር በድግግሞሽ ጫና ሲፈጥር ተመልክተናል። 21ኛው ደቂቃ ላይ የደሴ ተጫዋቾች ኳስን ሲቀባበሉ የፈጠሩትን ስህተት ቢኒያም ፍቅሬ በፍጥነት ነጥቆ ከፀጋዬ ብርሀኑ ጋር አንድ ሁለት ቅብብልን ካደረገ በኋላ ፀጋዬ በመጨረሻም ወደ ውስጥ ያሳለፈውን ኳስ ተጠቅሞ ቢኒያም ከመረብ አሳርፎ የጦና ንቦቹን መሪ አድርጓል። ደሴዎች ኳስን በመቀባበል ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል በመግባቱ ረገድ ቢሳካላቸውም በአንድ ሁለት ቅብብል ወቅት በሚፈጥሩት ስህተት መጋለጣቸው ያልቀረለት ቡድኑ ተጨማሪ ግብን ለማስተናገድ ተገደዋል። ጨዋታው ሊገባደድ 45+1 ላይ አብነት ደምሴ ለቢኒያም የሰጠውን ኳስ ፀጋዬ ብርሀኑ በግራ የግብ ክልል ገፋ ካደረገ በኋላ ሁለተኛ ጎል በማድረግ ወደ መልበሻ ክፍል በ2ለ0 ውጤት አምርቷል።

ከዕረፍት የተመለሰው የሁለቱ ቡድኖች መርሀግብር ቀጥሎ በንፅፅር የወላይታ ድቻ የበላይት የታየበት ነበር። መሐል ሜዳውን አሁንም ተቆጣጥረው ወደ መስመር በመለጠጥ ሲጫወት የነበረው ቡድኑ ከፍ ባለ ተገሳሽነት ሦስተኛውን ግብ አግኝተዋል። 58ኛው ደቂቃ ላይ ከራስ ሜዳ ኳስን ለማስጀመር ሲሉ ስህተቶቻቸው በጉልህ የሚታይባቸው ደሴዎች በተጠቀሰው ደቂቃ አብነት ደምሴ ነጥቆ ከብዙአየው ጋር ካደረገው ቅብብል በኋላ አበባየው አጂሶ ወደ ግራ የጣለውን ኳስ ፀጋዬ በቶሎ ነፃ ቦታ ለነበረው ዮናታን ኤልያስ አቀብሎት አማካዩ ሦስተኛዋን ጎል በማስቆጠር ጨዋታው ወደ 3ለ0 ተሸጋግሯል። ሦስት ጎልን ካስተናገዱ በኋላ ወደ ጨዋታ ቅኝት ውስጥ በይበልጥ የገቡት ደሴ ከተማዎች ከሽንፈት ያላዳናቸውን ኳስ 63ኛው ደቂቃ ላይ አስቆጥርዋል። በረጅሙ ከግራ በኩል የደረሰውን ኳስ በድቻ ተከላካዮች መሐል ሾልኮ በመውጣት ተቀይሮ የገባው ካሳሁን አስቆጥሮ ጨዋታው በወላይታ ድቻ የ3ለ1 ድል አድራጊነት ተቋጭቷል።